ሕብረት ሥራ ማሕበራት ገበያን ለማረጋጋት!

0
22

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የሚታየው የኑሮ ውድነት እና የገበያ አለመረጋጋት በማሕበረሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከባድ ጫና እየፈጠረ ይገኛል:: ከዋጋ ንረቱ በተጨማሪም የምርት አቅርቦት እጥረት ችግርም ይታያል::

በመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች እና ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ ኾነ የገበያ አለመረጋጋት በተለይም በታችኛው እና በመካከለኛው የገቢ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች ፈተና ሆኗል:: እነዚህ ዜጎች ገቢያቸው ከወጫቸው ጋር ባለመጣጣሙ  ኑሯቸውን መምራት አዳጋች ሆኖባቸዋል::

ስለሆነም ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ አማራጮችን  መፈለግ ግድ ይላል:: ከነዚህ አማራጮች መካከል የሸማች ሕብረት ሥራ ማሕበራትን ማጠናከር እና ማስፋፋት የችግሩ ሁነኛ መፍትሄ ተደርጎ ሲተገበር ቆይቷል፤ እየተተገበረም ነው::

የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማሕበራት የግብይት ሰንሰለትን በማሳጠር ለሸማቹ ማሕበረሰብ ጤናማ  የግብይት ሥርዓት በመዘርጋት እና ሸማቹ ካወጣው ገንዘብ ጋር ተመጣጣኝ  ምርት     ወይም አገልገሎት እንዲያገኝ በማስቻል የዋጋ ንረትን በመቀነስ ረገድ ሁነኛ ሚና ይጫወታሉ::

እነዚህ ማሕበራት ከአምራቾች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር ለዋጋ መናር ምክንያት የኾኑ ነጋዴዎችን ሲቀንሱ የምርት ዋጋ መናር እንዲገታ፣ ብሎም የገበያ መረጋጋት እንዲፈጠር  ያግዛሉ:: በዚህም ምርቶች ለሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ  እንዲደርሱ ያስችላሉ:: በተጨማሪም ማሕበራቱ የምርት ክምችቶችን በማስተዳደር የገበያ ውጣ ውረድን ማስተካከል ይችላሉ::

የሕብረት ሥራ ማሕበራት የምርት እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅትም ምርት በማቅረብ ዋጋው እንዳይጨምር ያደርጋሉ፤ በተቃራኒው በቂ ምርት ሲኖር በማከማቸት ሊከሰት የሚችል እጥረትን ይቆጣጠራሉ:: ይህ ተግባር በተለይ በምግብ እና በመሠረታዊ እቃዎች ገበያ ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት በመቀነስ የገበያ መረጋጋትን እንዲኖር ያደርጋል::

የዋጋ ግልጽነትን ማስፈንም ማሕበራቱ የሚጫወቱት ሌላው እጅግ አስፈላጊ ሚና ነው:: ግልጽ የዋጋ መዋቅር ሲኖር ሕገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ እና ማጭበርበር አይኖርም::

ሸማቾች እንደሚገልጹት ከሸማቾች ሕብረት ሥራ ማሕበራት የገዙት  ዕቃ ዋጋ  ከግል ሱቆች ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ትልቅ ቅናሽ አለው:: የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማሕበራት ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከመሸጥ ባለፈ ሸማቾች የክፍያ እፎይታ እንዲያገኙ እያስቻሉ ነው:: ሸማቾች በኣንድ ጊዜ ክፍያ ይገዙት የነበረውን ጤፍ ከሸማቾች ሕብረት ሥራ ማሕበራት በሁለት እና በሦስት ዙር ክፍያ መግዛታቸው የኑሮ ውድነት ጫናውን የሚቀንስ ርምጃ  ነው:: ይህ የክፍያ ሥርዓት በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎች በእጅጉ ተጠቃሚ  ያደርጋል::

ከአማራ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን የተገኘ መረጃ እንደሚጠቁመው በአማራ ክልል ከ31 ሺህ በላይ መሠረታዊ የሕብረት ሥራ ማሕበራት አሉ:: ከእነዚህም የሸማቾች ማሕበራት በተለይ ገበያን በማረጋጋት ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው:: በገጠር እና በከተማም በመደራጀት አቅርቦትን ለማረጋጋት እየሠሩ ስለመሆኑም ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል::

ማሕበራቱ የኢንዱስትሪ ምርቶችን  በማቅረብ የምርት እጥረት ችግርንም እያቃለሉ ነው:: በተጨማሪም የግብርና ምርቶችን በማቅረብ በዋጋ መረጋጋት ላይ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ::

ይህ ርምጃ ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ገበያው አንፃራዊ መረጋጋት እንዲያሳይ አስችሏል:: መንግሥትም ትኩረት በመስጠት  ከሕብረት ሥራ ማሕበራቱ ጋር በመሥራት የዋጋ መቆጣጠር ዘዴዎችን ተፈጻሚ ለማድግ እየሠራ ነው::

በተጨማሪም የማሕበራትን አቅም የማጠናከር ሥራም ተከናውኗል:: ይህም የማሕበራቱ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም የአቅርቦት አቅም  እንዲሻሻል አድርጓል:: ነገር ግን አሁንም በአቅርቦት መጠን፣ በአደረጃጀት እና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክፍተቶች ይስተዋላሉ:: ስለሆነም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት  ከንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮዎች እንዲሁም ከሌሎች አጋር አካላት ጋር መሥራት ያስፈልጋል::

በአጠቃላይ የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማሕበራት ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕዝቡ በማቅረብ የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ፣ የገበያ መረጋጋትን ለመፍጠር የማይተካ ሚና እየጫወቱ ናቸው:: ማሕበራቱ እያበረከቱት ያለው የኑሮ ውድነት ጫናን የመቀነስም ኾነ የገበያ መረጋጋትን የመፍጠር ጥረት ችግሩ እስኪፈታ ድረስ በዘላቂነት ይቀጥል ዘንድ እነዚህን ማሕበራት  የመደገፍ፣ የማስፋፋት እና ከአምራቾች ጋር ቀጥተኛ ግብይት የሚያደርጉበትን ሥርዓት የማጠናከር ጥረት  የበለጠ  ተጠናክሮ መቀጠል አለበት::

በኲር የመጋቢት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here