የኢትዮጵያ የቮሊቦል ንጉሥ

0
83

በስፖርቱ ዓለም ስማቸውን በወርቅ ቀለም ጽፈው ካለፉት ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ከሀገር አልፈው አህጉራችንን እና ዓለምን ማስደመም ችለዋል:: እነዚህ ታላላቅ የስፖርት ባለሙያዎች በህይወት ዘመናቸው የፈጸሙት ገድል እና ትተውት ያለፉት አሻራ በቀላሉ የሚዘነጋ አይደለም:: ከእነዚህ የኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ ምሰሶዎች መካከል አንዱ እና በቮሊቦል ስፖርት ወደር የማይገኝላቸው ባለሙያ ዓለማቀፉ ኢንስትራክተር ዓለማየሁ ሸዋታጠቅ ናቸው:: የኢትዮጵያ ቮሊቦል ስፖርት ስም ሲነሳ  የኚህ ታላቅ ሰው ስም አብሮ ይነሳል:: ዓለማየሁ ሸዋታጠቅ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ከፍ አድርገው ያስጠሩ የክብር ማህደር መሆናቸውን የዓለም አቀፉ የቮሊቦል ፌዴሬሽን መረጃ ያስነብባል::

ዓለም አቀፉ ኢንስትራክተር ዓለማየሁ ሸዋታጠቅ በአዲስ አበባ ከተማ ነው ተወልደው ያደጉት:: በልጅነት ጊዜያቸው አዲስ አበባ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ መነቃቃት የታየባት ወቅት ላይ ነበረች:: ገና በልጅነታቸው በቀድሞው ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወ.ወ.ክ.ማ) ግቢ ውስጥ ከስፖርቱ ጋር መተዋወቃቸውን የግል የታሪክ ማህደራቸው ያስነብባል:: በዚህ ግቢ ውስጥ ወጣቱ ዓለማየሁ የቮሊቦል ስፖርትን መሰረት በመጣል ኳስን አየር ላይ የመቆጣጠርን ጥበብ ተምረዋል:: ገና በወጣትነት ዕድሜያቸውም በዘርፉ የብዙዎችን ትኩረት መሳብ ችለዋል:: የቮሊቦል ስፖርት አካላዊ ጥንካሬን እንዲሁም ከፍተኛ የአዕምሮ ንቃትን እና የቡድን መንፈስን የሚጠይቅ በመሆኑ ዓለማየሁ እነዚህን ክህሎቶች ገና በለጋ ዕድሜያቸው ማዳበር ችለዋል:: ስፖርቱ ለእሳቸው የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ብቻ ሳይሆን የህይወታቸው ዋነኛ ፍልስፍና እና የትኩረት ማዕከል እየሆነ መጥቷል::

የዓለማየሁን የተለየ የስፖርት ችሎታ እና አካላዊ ብቃት በቅርበት የተመለከተው የኢትዮጵያ ባህር ሀይል ወጣቱን በእጩ ባህር ሀይልነት በመመልመል ወደ ተቋሙ እንዲቀላቀሉ አድርጓቸዋል:: ወታደራዊው ዓለም እና ስፖርት እጅግ የተቆራኙ በመሆናቸው በባህር ሀይል ውስጥ በነበራቸው ቆይታም ያላቸውን የስፖርት ክህሎት በመጠቀም ተቋሙን በስፖርቱ ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ አገልግለዋል::

ወታደራዊ ዲሲፕሊን በህይወታቸው ውስጥ ጠንካራ ሰብዕናን እና የማይበገር የሥነልቦና ጥንካሬን እንዲያዳብሩ ረድቷቸዋል:: በውትድርናው እና በስፖርቱ ዘርፍ የነበራቸውን ሀገራዊ ግዴታ በብቃት ከተወጡ በኋላ ወደ አደጉበት እና ስፖርታዊ መሰረት ወደጣሉበት ወ.ወ.ክ.ማ ተመልሰዋል:: ወደ አደጉበት ማህበር መመለሳቸው ያካበቱትን ወታደራዊ እና ስፖርታዊ ልምድ ለተከታዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሰፊ በር ከፍቶላቸዋል:: በማህበሩ ውስጥም ከፕሮግራም መሪነት ጀምሮ በልዩ ልዩ ዘርፎች በሀላፊነት፣ በአሰልጣኝነት እና በአስተባባሪነት ሠርተዋል::

በወቅቱ የነበረው የስፖርት አደረጃጀት ሲቀየር እና ወ.ወ.ክ.ማ ከስፖርት ኮሚሽን ጋር ሲቀላቀል ዓለማየሁ ወደ ሚወዱትና ህይወታቸውን ሙሉ ወደሰጡለት የቮሊቦል ፌዴሬሽን ተመልሰዋል:: የፌዴሬሽኑ ዳይሬክተር የጽሕፈት ቤት ሀላፊ እንዲሁም የወንዶች እና ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ በመሆንም አገልግለዋል:: በዚህ ሀላፊነታቸው ወቅት የኢትዮጵያ ቮሊቦል ስፖርት አዲስ መልክ እንዲይዝ እና ዘመናዊ አሰራርን እንዲከተል ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል:: ተጫዋቾችን በመምረጥ እና በማሰልጠን ብሎም የውድድር መንፈስን በማሳደግ የቮሊቦል ስፖርት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳጅነትን እንዲያተርፍ ያደረጉት አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚገመት አይደለም:: ቮሊቦል በሕዝቡ ዘንድ በስፋት እንዲታወቅ እና ተተኪ ስፖርተኞች እንዲፈጠሩ ያደረጉት ጥረት የህይወታቸው ትልቁ ስኬት ነው::

የስፖርት ሳይንስ በየጊዜው የሚያድግ እና የሚሻሻል መሆኑን በሚገባ የተረዱት ዓለማየሁ ያላቸውን የተፈጥሮ ተሰጥኦ እና የሥራ ልምድ በዘመናዊ የትምህርት እውቀት ለማዳበር ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው:: እናም የቀድሞው ስፖርት ኮሚሽን ከቀድሞዋ ምዕራብ ጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ (ምሥራቅ ጀርመን) ጋር ባደረገው የስፖርት ፕሮቶኮል ስምምነት የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ ጀርመን አቀኑ:: በጀርመን ሌይፒዝግ  (Leipzig) ከተማ በሚገኘው ታዋቂው የአካል ብቃት ማሰልጠኛ እና የስፖርት ኮሌጅ ገብተው በቮሊቦል ስፖርት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በከፍተኛ ማዕርግ ተመርቀው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ:: በወቅቱ ሌይፒዝግ በስፖርት ሳይንስ እና በአሰልጣኝነት የዓለም ቁንጮ ከነበሩት ከተሞች አንዷ ነበረች:: ዓለማየሁ ይህንን ወርቃማ ዕድል በሚገባ በመጠቀም የተትረፈረፈ ዕውቀት እና ልምድ ይዘው ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ በመመለስ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ችለዋል::

የትምህርት ደረጃቸውን በማሳደግ ብቻ ያላበቁት እኚህ ብርቅዬ ባለሙያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን የመጨረሻውን እና ከፍተኛውን የሦሰተኛ ደረጃ ዓለማቀፍ የአሰልጣኝነት ስልጠና ተከታትለው በከፍተኛ ውጤት አጠናቀዋል:: ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፖርቱ ከፍተኛ እውቅናን ያስገኘላቸው ትልቅ ስኬት ነበር:: በአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን ውስጥ ኢንስትራክተር እና በዓለም አቀፉ ቮሊቦል ፌዴሬሽን (FIVB) ሲኒየር ዓለም አቀፍ ኢንስትራክተር የሚለውን እጅግ የላቀ ማዕርግ ለመቀዳጀት በቅተዋል:: ይህ ስኬት ለእሳቸው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ እና ለመላው አፍሪካ ትልቅ የኩራት ምንጭ በመሆን በታሪክ ማህደር ውስጥ ደምቆ ይታያል::

ኢንስትራክተር ዓለማየሁ ሸዋታጠቅ ያልሰሩበት እና ያላገለገሉበት የስፖርት ተቋም የለም ማለት ይቻላል:: በቀድሞው የስፖርት ኮሚሽን የሸዋ ክፍለ ሀገር የቴክኒክ ሀላፊ በመሆን፣ በባህር ሃይል፣ በምድር ጦር፣ በወ.ወ.ክ.ማ፣ በኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን እና በኦሎምፒክ ኮሚቴ ውስጥ በተለያዩ ከፍተኛ የኃላፊነት እርከኖች   ሀገራቸውን አገልግለዋል:: ዕውቀታቸውን ለራስ ሀብት ማከማቻነት ሳይሆን አገርን ለመገንባት እና ትውልድን ለመቅረጽ ተጠቅመውበታል:: በ1990 ዓ.ም የወጣው ብሔራዊ የስፖርት ፖሊሲ ሲረቀቅ የጥናት ቡድኑ አባል በመሆን ሙያዊ አሻራቸውን አስቀምጠዋል:: የስፖርት ፖሊሲው ኢትዮጵያ በስፖርቱ ዘርፍ የረጅም ጊዜ ዕቅድ እንዲኖራት  በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ አበርክቷል::

በሀገር ውስጥ ባህር ሀይልን፣ ምድር ጦርን እና የተለያዩ ክለቦችን በማሰልጠን እና በማማከር፣ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ወንድ እና ሴት ብሄራዊ ቡድንን በመገንባት እንዲሁም ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ተጫዋቾችን በማፍራት ለሀገራቸው ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል:: በርካታ ወጣቶች የእሳቸውን ፈለግ በመከተል በቮሊቦል ስፖርት ስኬታማ መሆን ችለዋል:: የዛሬዎቹ የቮሊቦል ባለሙያዎች እና አሰልጣኞች አብዛኛዎቹ የእሳቸው የዕውቀት ፍሬዎች ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም:: የእሳቸው ታታሪነት እና ለሥራ ያላቸው ክብር በስፖርቱ ማህበረሰብ ዘንድ ሁሌም የሚታወስ እና ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆን ነው::

የዓለም አቀፉ ኢንስትራክተር ዓለማየሁ ሸዋታጠቅ አበርክቶ ከሀገር ድንበር ተሻግሮ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ደማቅ አሻራ ያሳረፈ ነው:: በስፖርቱ ዓለም ባካበቱት እውቀት እና ክህሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ160 በላይ ጉዞዎችን ማድረጋቸውን የዓለም አቀፉ የቮሊቦል ፌዴሬሽን መረጃዎች አመልክተዋል:: በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በደቡብ አሜሪካ እና የአፍሪካ ሀገራት በመዘዋወር ስልጠናዎችን ሰጥተዋል:: አንድ ኢትዮጵያዊ ባለሙያ በተለያዩ አህጉራት እየተዘዋወረ የቮሊቦል ሳይንስን ሲያስተምር መመልከት ሀገርን ከመገንባትም በላይ የኢትዮጵያውያንን አቅም ለዓለም ያሳየበት ልዩ ክስተትም ነበር::

በአፍሪካ ደረጃ በተለያዩ አህጉራዊ የአሰልጣኝነት ስልጠናዎች ላይ ዋና አሰልጣኝ በመሆን መርተዋል:: የአፍሪካ ሀገራት የቮሊቦል አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል:: ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የተለያዩ ሀገራት የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ የዓለም አቀፍ አሰልጣኝነት ስልጠናዎችን በመስጠት በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ የቮሊቦል ባለሙያዎችን አፍርተዋል:: በዓለም አቀፍ የቮሊቦል ጉባኤዎች ላይም ኢትዮጵያን ወክለው በመሳተፍ የሀገራቸውን ስም አስጠርተዋል:: በእነዚህ መድረኮች ላይ የሚያቀርቡት ጥናታዊ ጽሁፍ እና ሀሳብ በዓለም አቀፍ የስፖርት ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት ነበረው::

ዓለም አቀፉ ኢንስትራክተር ዓለማየሁ ሸዋታጠቅ በተወለዱ በ82 ዓመታቸው የካቲት አምስት ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ተለይተዋል:: የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የኚህን ታላቅ ሰው ውለታ ለመዘከር እና ትኩረት የተነፈገውን የቮሊቦል ስፖርት ለማነቃቃት ታላቅ የመታሰቢያ ውድድር በስማቸው አዘጋጅቶላቸዋል::

ይህ የመታሰቢያ ውድድር ወጣቶች የእሳቸውን አርአያነት እንዲከተሉ እና ለስፖርቱ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳድጉ የሚያስችል ትልቅ አጋጣሚ ነው:: የኢንስትራክተር ዓለማየሁ ሸዋታጠቅ ራዕይ እና ትጋት አሁንም በኢትዮጵያ ቮሊቦል ስፖርት ውስጥ ብርሃን እየፈነጠቀ ይገኛል::

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የመጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here