‘‘በእጅ የያዙት ወርቅ…’’

0
69

በዓለም ላይ በባህላዊ ሕክምና ሕንድ እና ቻይና ተጠቃሽ ናቸው:: በሕንድ  የባሕል ሕክምና ከተጀመረ ከአምስት ሺህ ዓመታት በላይ እንዲሁም  በቻይና ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ ማስቆጠራቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል:: በቻይና እና በሕንድ ያለው የባሕል ሕክምናም ሆነ ለባሕል ሐኪሞቹ የሚሰጣቸው ትኩረት ከፍተኛ ነው::

ቻይና በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅበት የባህል ሕክምና  /Traditional chinese medicine/ ዛሬ ላይ ብዙ ሀገራት አብነት የሚያደርጉት ወይም የተለያዩ ሀገራት ለራሳቸው የባሕል ሕክምና እና መድኃኒቶች የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡ መነቃቃትን የፈጠረ ነው::

በሰውነት ላይ በቀጭን መርፌ  የሚሰጠው የቻይናዎች የባሕል ሕክምና (አኩፓንክቸር) ዛሬ ላይ በብዙ የዓለም ሀገራት ተስፋፍቶ ይገኛል፤ ይሄው ሕክምና በኢትዮጵያም በተወሰኑ ቦታዎች መሰጠት ተጀምሯል::

ሕንድ ከተለያዩ ዕጽዋት በምታዘጋጀው  “አዩርቬዳ” ብላ የምትጠራው የባሕል መድኃኒቷን   ለዓለም ገበያ በማቅረብ  ከዘመናዊው ሕክምና የሚገዳደር ማድረግ አልተሳናትም::

መረጃው እንደሚያመላክተው እነዚህ ሁለት ሀገራት (ሕንድ እና ቻይና) በባሕል ሕክምናዎቻቸው በዓለም ላይ ታዋቂ ለመሆን፣ የባሕል ሐኪሞቻቸው ከበሬታ እንዲያገኙ ለማድረግ፣ በባሕል ሕክምናው ዘርፍ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር እና የባሕል ሕክምናዎቻቸው ለጤና ቱሪዝም እንዲያገለግል ብዙ ሥራዎችን ሠርተዋል::

ቻይና እና ሕንድ የባሕላዊ ሕክምናን ከዘመናዊ ሕክምና ጋር ለማስተሳሰር ብዙ ርቀቶችን ተጉዘዋል:: ለአብነትም የመንግሥታቸውን ሕግ እና መመሪያ እስከማስለወጥ ደርሰዋል:: ባሕላዊ ሐኪሞቻቸውም በሰፊው እንዲታወቁ አድርገዋል:: ሁለቱ ሀገራት ባሕላዊ ሕክምናን በዩኒቨርሲቲዎቻቸው ያስተምራሉ፤  ተማሪዎቻቸውም  ምርምሮችን እንዲያካሂዱ ድጋፍ ያደርጋሉ::

በቻይና እና ሕንድ እንደ ዘመናዊ መድኃኒት ቤቶች የባሕል መድኃኒት መሸጫ ቦታዎችንም አቋቁመዋል:: ለምሳሌ በቻይና የባሕል መድኃኒቶቻቸው በሆስፒታል ውስጥ ከዘመናዊ መድኃኒቶች እኩል ለአገልግሎት  ይቀርባሉ::

በሁለቱ ሀገራት ውስጥ ለዘመናዊ መድኃኒቶች የሚደረገው የደኅንነት እና ጥራት ቁጥጥር በባሕላዊ መድኃኒቶቻቸውም ላይ ይተገበራል:: በሁለቱም ሀገራት በባሕላዊ መንገድ የተመረቱ ብዙ የዕጽዋት መድኃኒቶች ወደ ዘመናዊ መድኃኒትነት ተቀይረዋል:: በጥቅሉ ቻይና እና ሕንድ ባሕላዊ ሕክምናቸውን ከዘመናዊ ሕክምና ጋር፣ በሕግ፣ በትምህርት፣ በምርምር እና ከጤና ተቋሞቻቸው ጋር በማስተሳሰር የባሕል ሕክምናቸውን አዘምነውት ይገኛሉ::

የባሕል ማድኃኒቶች ልማት በብዙ ሀገራት ለገቢ ማግኛ እና የሥራ ዕድል ለመፍጠር አስፈላጊ ዘርፍ ሆነዋል:: ከዚህም አንጻር እንደ አብነት ስማቸው ቀድሞ የሚጠራው ሀገራት ቻይና እና ሕንድ ናቸው:: በእዚህ ሀገራት ገበሬዎች ከመደበኛው ሥራቸው ጎን ለጎን ለመድኃኒትነት አገልግሎት የሚውሉ  ዕጽዋትን በማምረት ከፍተኛ ገቢ ያገኛሉ:: የባሕላዊ መድኃኒቶች ምርት በበዛ ቁጥር የመድኃኒት ማቀናበሪያ ኢንዱስትሪዎች በብዛት ይቋቋማሉ፤ በቻይና እና በሕንድ እየሆነ ያለውም ይሄው ነው::

ለመድኃኒትነት የሚጠቅሙ ዕጽዋት በስፋት ሲመረቱ ዕጽዋቱን ወደ ዱቄት (ፓውደር) ፣ ሻይ እና የመድሀኒት ማሸጊያ / ካፕሱል/ ቀረጢት የሚያመርቱ እና የሚያቀነባብሩ  ፋብሪካዎች ይፈጠራሉ፤ ይህ በፋብሪካ ደረጃ እና በትናንሽ የጎጆ ኢንዱስትሪዎች ደረጃ ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድልን ይፈጥራል::

በአፍሪካ የባሕላዊ ሕክምና ተጠቃሚነት በጣም ከፍተኛ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎች ያመለክታሉ:: በአፍሪካ ከሚኖረው ሕዝብ ከ70 እስከ 80 በመቶው  የመጀመሪያ ምርጫቸው የባሕል ሕክምና እንደሆነም መረጃው ይጠቁማሉ:: ለዚህ እንደ ምክንያት የሚነሳው ደግሞ በብዙ የአፍሪካ ገጠራማ አከባቢዎች ዘመናዊ የሕክምና ማዕከላት ካለመስፋፋታቸውም በተጨማሪ የባሕል ሐኪሞችን በአቅራቢያቸው እና በቀላሉ ማግኘት ስለሚችሉ ነው:: ሌላው እንደምክንያት የሚጠቀሰው ባሕላዊ መድኃኒቶች ብዙውን ጊዜ ከዕጽዋት ወይም ከሌሎች ተፈጥሯዊ ነገሮች ስለሚዘጋጁ ዋጋቸው ማኅበረሰቡን የማይጎዳ በመሆናቸው ነው::

በአፍሪካ ውስጥ ብዙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሕመምን ከባሕላዊ እምነትና መንፈሳዊ ጉዳይ ጋር ስለሚያያይዙት መዳኛቸውም ባሕላዊ ሕክምና እንደሆነ ለውስጣቸው ነግረውታል:: የባሕል ሕክምና ለብዙ ሕመሞች ለአብነትም ለውስጥ ደዌ፣ ለቆዳ፣ ለአጥንት፣ ለወሊድ እና ሌሎች ሕመሞችም ስለሚሰጥ ከላይ ከተዘረዘሩት አመክንዮች ጋር ተደማምሮ በአፍሪካም የባሕል ሕክምና ከተጀመረ ብዙ ሺህ ዓመታት እንደተቆጠሩ መላ ምቶች አሉ::

በኛስ ሀገር

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው በኢትዮጵያ ከስድስት ሺህ በላይ የሚሆኑ የእጽዋት ዝርያዎች ለባሕላዊ ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ በሚል ተለይተዋል:: ሕዝቡም  የባሕል ሐኪሞቻችን በቻይና እና በሕንድ እንዳሉት ከፍተኛ ቦታ ባይሰጣቸውም  በርካታ ተጠቃሚ አላቸው::  ጦስኝ፣ ዳማከሴ፣ ኮሶ፣ ጤና አዳም፣ ዝንጅብል፣ ነጭ ሽንኩርት እና ሞሪንጋ የመሳሰሉ ዕጽዋትና ተክሎች በሀገራችን ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ለመድኃኒትነት አገልግሎት ይውላሉ::

በሀገራችን  ለባሕል ሐኪሞች እየተሰጠ ያለው ዕውቅና እና ከዘመናዊው ሕክምና ጋር ተቀናጅተው እንዲሠሩ እየተደረገ ያለው ጥረት ይበል ቢያሰኝም የባሕል ሐኪሞችን እና ባሕል መድኃኒቶችን እንደ ቻይና እና ሕንዶች ለመጠቀም ግን አልተደረሰም::

ኢትዮጵያ ከቻይና እና ሕንድ የባሕል ሕክምና ምን ትማር ካልን የባሕል ሕክምናችንን ከዘመናዊ ሕክምና ጋር አቀራርቦ መጠቀምን፣ የመድኃኒት ቅመማዎችን እና የማዘዣ መንገዶችን ማዘመንን፣ ለባሕላዊ ሕክምናና ሐኪሞች የሚሰጠውን ዝቅተኛ ግምት ማስወገድ፣ የባሕል ሕክምናን ለሥራ አጥ ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ጭምር ማመን ያስፈልጋል::

ለመድኃኒትነት የሚውሉ የብዙ ዕጽዋት ባለቤት በሆነችው ሀገራችን ውስጥ አርሶ አደሮችን የመድኃኒት ዕጽዋትን እንዲያመርቱ ማበረታታት፣ በርካታ ባሕላዊ መድኃኒቶቻችን በፋብሪካ ደረጃ ተመርተው ለዓለም ገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ የውጪ ምንዛሪ ማግኘትን፣ በጤና ቱሪዝም ዘርፍ ወደ ሀገራችን የሚገቡ የባሕል ሕክምና ፈላጊዎችን ቁጥር ማብዛትና ሌሎችንም በጎ ነገሮች መቅሰም ይገባል::

ጤና አዳም

የጤናአዳም  የጤና በረከቶች

በኢትዮጵያ የባሕል ሕክምና ጤናአዳም ለሆድ፣ ለተቅማጥ፣ ለጆሮ፣ ለልብ፣ ለኪንታሮት፣ ለኢንፍልዌንዛ እና ከአንጀት መታወክ ጋር ለተያያዙ ህመሞች አገልግሎት ላይይውላል::

ጤናአዳም በጡንቻ ላይ የሚያጋጥም፣ ውጥረትንና በወር አበባ ወቅት የሚያጋጥም ሕመምንም ያስታግሳል::  መጠቀም ያለብን ግን የእፅዋት ባለሙያን በማማከር መሆን አለበት::

በሻይ መልክ መጠቀም ለሽንት ቧንቧ፣ ለአንጀትና በአጠቃላይ ለደንዳኔ ኢንፌክሽን ፈዋሽነው::

ጤናአዳም ለምግብ መመረዝ በተለይ ደግሞ ሳልሞኔላ የተባለውን ባክቴሪያና ሌሎች አደገኛ ተህዋስያንን ይከላከላል:: ከዚህ በተጨማሪ ጤናአዳም የፀረ ባክቴሪያ ባሕሪ ስላለው ልንጠቀመው እንችላለን:: ነርቮችን የማረጋጋት ኀይል  እንዳለውም ጥናቶች የሳያሉ፤ በመሆኑም የእንቅልፍ ማጣት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ጤናአዳምን መጠቀም ያረጋጋል::

ምንጭ፦ዶክተር አለ

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር የመጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here