ኢትዮጵያ ሀገራችን ወንዛችን ዓባይ
ሴቱ ቀጭን ፈታይ ወንዱ ተጋዳይ!
በኢትዮጵያ የሕዝብ ዘፈኖች ውስጥ የሴት ልጅ ጥጥ ፈታይነት ከወንዱ ጀግንነት ጋር እኩል በሚዛን የሚቀመጥ የክብር መገለጫ ነው::
ለዚህም ከጥንት ጀምሮ በአባቶችና እናቶች ሲዜም የኖረው ይህ የሕዝብ ስንኝ ትልቁ ማሳያ ነው:: የሴት ልጅ ክብር እና ጀግንነቷ በሙያው ውስጥ ነው፤ ለዚያውም ቀጭን መፍተል መቻሏ:: መፍተሉንማ ማንም ሴት ይፈትላል:: ባለሙያዋ ግን ቀጭን ትፈትላለች::
የኢትዮጵያ ዘፋኞች፣ አዝማሪዎች እና የሕዝብ ዜማዎች “ጥጥ ፈታይ” ሴትን በተመለከተ ጥልቅ እና ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን አቅርበዋል:: በሙዚቃዎቻችን ውስጥ ጥጥ ፈታይዋ ሴት ዝም ብላ ክር የምታዘጋጅ ሰራተኛ ሳትሆን የሀገር ምሰሶ፣ የፍቅርና የውበት ተምሳሌት እንዲሁም የትዕግስት መገለጫ ሆና ነው የሚዘፈንላት::
መግቢያ ባደረግነው ስንኝ ውስጥ የኢትዮጵያ ሴት “ቀጭን ፈታይ” ተብላ መሞገሷ ሀገር የምትገነባው፣ ባህል የሚጠበቀው እና ቤተሰብ የሚተዳደረው በእሷ ጥበብና ትጋት መሆኑን ለማሳየት ነው:: ወንዱ በጦር ሜዳ ሀገር ሲጠብቅ ሴቷ በእንዝርቷ ባህልን፣ ፍቅርንና ቤተሰብን ታቆማለች::
በማሲንቆ በሚታጀቡ የአዝማሪ ጨዋታዎች ላይ “ፈታይ” የፍቅር እና የውበት ተምሳሌት ነች። አዝማሪው የሴቷን ጣቶች ልስላሴ፣ የሰውነቷን አቋም እና የፍቅር አያያዟን ከእንዝርት እና ከጥጥ ጋር እያመሳሰለ ይዘፍናል::ለአብነት ያህል ታዋቂው የማሲንቆ ተጫዋች አለማየሁ ተስፋዬ እና ፈንታ በሌ “ሸማኔ እና ፈታይ” በሚለው ድንቅ የባህል ዘፈናቸው የፈታይዋን እና የሸማኔውን የፍቅር ትስስር፣ ሙያ እና መስተጋብር በሚገርም ዜማ አቅርበውታል:: ሁለቱ ዘፋኞች ጥጥ ፈታይዋን ክር ብቻ ሳይሆን የሰውን ልብ ጠልፋ የምታስር (የፍቅር እንዝርት የምታሾር) አድርገው በዜማቸው ይገልጿታል::
ድምጻዊት እጅጋየሁ ሺባባው (ጂጂ) ስለ ሀገር እና ስለ ኢትዮጵያዊነት ስትዘፍን የኢትዮጵያን እናት እና ሴት “ቀጭን ፈታይ እመቤት” እያለች ከፍ አድርጋ ትጠራታለች:: የሴት ልጅ ቁንጅና ከፈትል ሙያዋ ጋር ተደምሮ “እመቤትነትን” እንደሚያጎናጽፋት ዘፋኞች በዜማዎቻቸው ይመሰክራሉ:: ሙያ አዋቂ፣ ክብሯን እና ጥንካሬዋን የምትጠብቅን ሴት ለመግለጽ ቀጭን ፈታይ ሴት የሚለው ገለጻ ጥቅም ላይ ይውላል::
ድምጻውያን እና ገጣሚያን ፈታይዋ ሴት ጥጥ ስትነድፍ፣ ስታዳውር፣ በእንዝርት ስታሾር የምታሳየውን ትዕግስት ከእናትነት ርህራሄ ጋር ያመሳስሉታል:: ጥጡን ከፍሬው ለይታ፣ ነድፋ፣ አባዝታ ወደ ውብ ክርነት እንደምትቀይረው ሁሉ እናትም ልጇን በመከራ አሳድጋ፣ አቅንታና ኮትኩታ ለቁምነገር የምታበቃ “የህይወት ፈታይ” መሆኗ በዜማዎቻችን ደጋግሞ ይንጸባረቃል::
በተመስገን ታፈሰ “ሳብየ” ዘፈን ውስጥ ኢትዮጵያዊ የሸማ ጥበብ በፍቅር ተዋዝቶ በቅኔ ቀርቧል::
ሳባ ጥበብ ለብሰሽ ውበት ያዘነብሽው
ከዳመናው ነው ወይ ጥጡን ያስነደፍሽው::
ወየው ጥበበኛን ስሙን ያቀለለ
አንቺን አስከትሎት ሲያባዝተው ዋለ::
አስልኬ ነበር ጥጥና ድውር
ብየ ላዳራችን ጋቢ ላስሞክር
ብየ ላዳራችን ኩታ ላስሞክር::
ብርድ አንሰፈሰፈኝ ገላየም ሳሳልሽ
ይላኩልኝ ባንቺ ከቋጩት እናትሽ::
በዚህ ዘፈን ግጥሞች ውስጥ የሚንጸባረቀው ከፍቅር በስተጀርባ የሸማ ጥበባችን እንደሚሞቀን፣ ፍቅር እና ትዳር እንዲሁ ሙቀት እና ጥንካሬ እንደሚሰጥ ነው:: እናትሽ ተሰርቶ የተቋጨ ጋቢ ይላኩልኝ የሚል ቢመስልም አንቺ ነይልኝ ነው የሚላት::
ወደ አንድ የሸማኔ ጎጆ ብቅ ብንል አየሩን ሞልቶት የሚቀበለን “ጠቅ… ጠቅ… ሹር… ጠቅ…” የሚል የሙዚቃ ምት (ሪትም) ነው:: ሸማኔው ማጉን ከግራ ወደ ቀኝ ያለ ማቋረጥ ያመላልሳል:: መወርወሪያዋ በድር እና በማጉ መካከል እንደ ነጻ ወፍ ስትበር፣ የሸማኔው እግሮች ርካቡን ሲረግጡ፣ ነጭ ጥጥ ከዓይን በሚሰወር ፍጥነት ወደ ውብ ጨርቅነት ይቀየራል:: የኢትዮጵያ የሸማ ጥበብ ከዕለት ተዕለት የሰውነት መሸፈኛነት ባሻገር በሀዘንም በደስታም ማህበረሰቡን የሚያስተሳስር ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈ የሀገር ብሔራዊ ቋንቋ ነው::
ከሸማኔው ጉድጓድ አስቀድሞ የሸማ ጥበብ የሚጀምረው በእናቶች እና እህቶች የትዕግስት መዳፍ ላይ ነው:: ጥጡ ሲነደፍ፣ በእንዝርት ሲፈተል ጥልቅ የሆነ ማህበራዊ ፍልስፍና አለው:: የሀገራችን የፎክሎር ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የእንዝርት ፈትል የሴት ልጅን ሰብዕና እና የትዳር ዓለም ትጋት የሚለካበት ትልቅ ማህበራዊ መስፈርት ነበር::
በነባሩ የገጠር ማህበረሰብ ቀጭን ፈታይ ሴት ናት ከተባለ ሙያ እንዳላት ታስቦ ጥሩ ባል ያጫታል:: ባሏን ፈትላ ካላለበሰች፣ ጠላ ጠምቃ ካላጠጣች ሴትነቷ ጥያቄ ውስጥ ይገባል:: ባሏ እሷ የፈተለችውን ለብሶ አደባባይ ሲወጣ ‘ነጭ ኩታ ወይም ጋቢ አለበሰችው’ ይላል ባላገሩ:: በዚህ አባባል ውስጥ ፈትል ከጥጥ ብቻ ሳይሆን ከሴት ልጅ ፍቅር፣ አክብሮት እና ለቤተሰቧ ካላት ከለላ ጋር አብሮ የሚፈተል መሆኑን እንረዳለን::
ከሴቷ እጅ የደረሰው ክር ወደ ሸማኔው ሲተላለፍ ሌላ ሳይንሳዊ እና ጥበባዊ መልክ ይይዛል:: ባህላዊው የሸማ አሠራር ቀላል ቢመስልም እጅግ ውስብስብ የሂሳብ ስሌት ይጠይቃል:: ይህን በተጨባጭ ለማሳየት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (EiTEX) ምሁራን የሆኑት ዶ/ር ብሩክ ፈንታሁን አዳሙ እና ደረጀ በሪሁን ስጦታው በ2021 እ.ኤ.አ. ያሳተሙትን ጥናታዊ ምርምር መመልከት በቂ ነው::
እነዚህ አጥኚዎች በመመረቂያ እና የምርምር ወረቀታቸው ላይ እንዳረጋገጡት የኢትዮጵያ ሸማኔዎች እንደ “የሸረሪት ድር”፣ “የንግስት ጫማ” እና “የአልማዝ ቅርጽ” የመሳሰሉትን የጥበብ ንድፎች በሀበሻ ቀሚስ ላይ ለማስፈር በክሮቹ መካከል የሚያደርጉት ትክክለኛ የቁጥር ስሌት እና የንድፍ አመዳደብ የዘመናችንን የኮምፒውተር ኮዲንግ የሚያስንቅ የፈጠራ ጥግ ነው::
የሸማ ጥበብ በአገራችን መቼ ተጀመረ ለሚለው ጥያቄ ምሁራን የረጅም ዘመን ታሪክን ያነሳሉ:: አንጋፋው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት “የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ታሪክ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ በጥልቀት እንዳብራሩት የኢትዮጵያ የጥጥ ልማትና የሸማ ስራ ታሪክ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከአክሱም ስልጣኔ ዘመን ጀምሮ የነበረ ነው:: ጥበቡ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር በተለይም እንደ ዶርዜ ያሉ ማህበረሰቦች በእንዝርት፣ በድር እና በማግ መካከል የህይወት ፍልስፍናቸውን ሰፍተውበት ኖረዋል::
ይህ ሁሉ የጥበብ ልዕልና እና የሂሳብ ቀመር እያለ ነባሩ ማህበረሰብ ለሸማኔው የነበረው ዕይታ ግን የተዛባ ነበር:: ሸማኔዎች፣ አንጥረኞችና የሸክላ ባለሙያዎች የሁሉንም ገላ አልብሰው ማህበረሰቡን አስውበው፣ እነሱ ግን “ባለእጅ” እየተባሉ መገልል ደርሶባቸው ኖረዋል:: በዚህም ከጋብቻ፣ ከእድር እና ከማህበራዊ ተሳትፎ ይገለሉ ነበር::
ቀድሞ አዝማሪ እያዝናና፣ ታሪክ እየሰነደ፣ ጦር እያዘመተ ሲገለል የኖረበት ታሪክ እንዳበቃ ሁሉ ዛሬ ዘመኑ ተቀይሮ የሸማኔዎች ሙያ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ እና የሀገርን ባህል የሚያስተዋውቅ የክብር ሞያ ለመሆን በቅቷል፤ ሸማኔም ተከብሯል።
ኢትዮጵያውያን ሸማን ዝም ብለው አይለብሱም፤ ይነጋገሩበታል:: የፎክሎር እና ስነ-ጽሑፍ ምሁሩ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ በቃል ስነ-ጽሑፍ እና ባህል ጥናቶቻቸው ላይ በተደጋጋሚ እንዳነሱት እያንዳንዱ የሸማ አለባበስ የራሱ መዝገበ ቃላት አለው:: ነጠላን ዘነፍ አድርጎ መልበስ የጀብዱ እና የኩራት፣ ጠልፎ መልበስ የጥልቅ ሀዘን፣ ማቅ መልበስ የጸጸት፣ ነጭ ኩታ ደግሞ የንጽህና እና የሃይማኖታዊ ክብር ምልክቶች ናቸው:: ወፍራሙ ጋቢ ለሽማግሌዎች የሞገስ ካባ ነው:: የተንቆጠቆጠው ጥበብ የኢትዮጵያዊት ሴት የውበት ጣሪያ ነው::
ከቻይና እና ከህንድ የሚገቡ ርካሽ እና የሀበሻ ጥበብን አስመስለው በፋብሪካ የሚታተሙ የፖሊስተር ጨርቆች በሸማኔው የገበያ ድርሻ እና ህልውና ላይ ከባድ የኢኮኖሚ አደጋ ደቅነዋል:: ሽፎን የሚባል በፋብሪካ የሚመረት የውጪ ሀገር ልብስ በርካሽ ዋጋ ገበያውን ለመቆጣጠር እየሞከረ ነው።
በሌላ በኩል ግን ተስፋዎች አሉ:: የዘመናችን የኢትዮጵያ ፋሽን ዲዛይነሮች የሸማ ጥበብን ወደ ዘመናዊ አለባበስ በመቀየር ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ይዘውት መውጣታቸው ለጥበቡ ትልቅ የቱሪዝም መስህብነት እና የእውቅና በር ከፍቶለታል::
አሁንም በሀገራችን የባህል አልባሳትን መልበስ በጣም በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው:: በበዓላት፣ በሀይማኖታዊ ክብረ በዓላት እና ዝግጅቶች ላይ በጋራ ደምቆ መታየት ፋሽን ሆኗል:: ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ደግሞ በሀገር ውስጥ የሚተኩበት ጊዜ ይመጣል:: አምራቾች የሚገጥሟቸው ችግሮች ሲፈቱ በስፋት እና በጥሩ ዋጋ ማምረት ይጀምራሉ::
አንድ ቀን እንደ ሕንዶች ከሀገራችን ልብስ ውጪ ሌላ ግን ልብ ስም ብለን በሄድንበት ሁሉ “በኢትዮጵያ የተመረተ” የሚል ልብስ መልበስ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ሆኖ ይሰማን ይሆናል።
መረፊያ
ወንዝ
ጓዝ እንደተጫነ አህያ፤ ዘላለም ጀርባ ተልጦ
እንደተመረዘ አካል ስጋ፤ እንደ ጊንጥ መርዝ ተቆርጦ
የላይ የላዩን እየሳቀ፤ ፍቅርን ከኋላ አስከትሎ
ህይወት እንደ ውሀ ይጎርፋል፤ የእድሜ ጅረት ላይ ታዝሎ፡፡
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የመጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


