የሱስ ዳፋ እና መፍትሔዎቹ

0
79

ሱስ (Addiction) አንድን ግለሰብ ጤናውን፣ ማህበራዊ ሕይወቱን፣ ሥራውን የሚጎዳ  እፅ ወይም ድርጊትን  ደጋግሞ የመጠቀም ወይም የመፈጸም አስገዳጅ ፍላጎት ነው። ይህም ለሞት፣ ለከባድ የጤና እና የስነ-ልቦና ችግር የሚዳርግ እንደሆነም የዓለም ጤና ድርጅት (World Health Organization) መረጃ ያመላክታል።

የአሜሪካ የሥነ- አእምሮ ማሕበር (American Psychiatric Association – APA) ስለ ሱስ ያስቀመጠው አንኳር መረጃ ደግሞ ሱስ የሥነ-ምግባር ጉድለት ሳይሆን ውስብስብ የአእምሮ (የጭንቅላት) በሽታ መሆኑን ነው። ግለሰቦች በሱስ ምክንያት ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይከውኑ ከማድረግ ባሻገር አካላዊ፣ አእምሯዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጫናው ከፍተኛ መሆኑን መረጃው አመላክቷል::

ለሱስ አጋላጭ ምክንያቶችም የአቻ (የጓደኛ) ግፊት፣ ከቤተሰብ ጋር የሚፈጠሩ አለመግባባቶች፣ ከፍቅረኛ እና ከትዳር ጓደኛ ጋር የሚፈጠር ግጭት፣ አካባቢያዊ ሁኔታ፣ ከባድ የሥነ-ልቦና ጠባሳ፣ ጭንቀት፣ ድብርት እና መሰል ተያያዥ ጉዳዮች እንደሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ። ሆኖም ሱስ የሞራል ውድቀት ሳይሆን ሊታከም የሚችል የጤና ችግር እንደሆነም ተመላክቷል::

ሕክምናው እንደ ሱሱ አይነቱ የሚለያይ ቢሆንም ከአጋላጭ ሁኔታዎች መራቅ፣ የጤና ባለሙያዎችን እርዳታ ማግኘት፣ የሥነ-ልቦና ሕክምና ማድረግ፣ በማገገሚያ ማዕከላት (Rehabilitation Centers) ውስጥ ክትትል ማድረግ፣ የመድኃኒት ሕክምና ማድረግ፣ ጤናማ ልማዶችን መከተል፣ የቤተሰብ እና ማህበራዊ ድጋፍ ማግኘት እና መሰል ጉዳዮች ከሱስ ለመውጣት የሚረዱ ዋና ዋና መፍትሔዎቹ ናቸው።

የአሜሪካ የሥነ አእምሮ ማሕበር (APA) ትልቁ መልዕክትም ማሕበረሰቡ ሱስ ያለባቸውን ሰዎች ማግለል እና መኮነን ትቶ የሕክምና ድጋፍ እና ርህራሄ የሚያስፈልጋቸው መሆናቸውን እንዲገነዘብ በፅሑፉ አስፍሯል። በሱስ የተጠቁ ሰዎችን የሱስ ማገገሚያ ማዕከላትን በማስፋፋት እና የሥነ- ልቦና ምክር በመስጠት፣ በመድኃኒት እና በማሕበራዊ ድጋፍ ከገቡበት ሱስ ወጥተው  እንዲያገግሙ እና ጤናማ ሕይወት እንዲመሩ ማድረግ እንደሚቻልም ማሕበሩ አስገንዝቧል::

“ሱስ የሞራል ውድቀት ሳይሆን ሊታከም የሚችል የጤና ችግር” እንደሆነ ጥናቶች ጠቁመዋል:: በኵር ጋዜጣም ለዚህ አባባል   ማሳያ ለ14 ዓመታት ያህል በሱስ ውስጥ ከቆየ ወጣት  ጋር ቆይታ አድርጋለች:: ባለታሪካችን ዳንኤል ያየውሰው ይባላል። ወጣቱ ወደ ሱሱ የገባው የ12ኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት እንደሆነ ያስታውሳል። “ሱስ የጀመርኩትም እንደቀልድ ነበር:: ያኔ አወዋሌ ጥሩ አልነበረም” የሚለው ወጣቱ፤ የጀመረው ሱስም ብዙ ነገሮችን እንዳሳጣው ነው ዛሬ በቁጭት የሚናገረው።

ዳንኤል የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና  የከፍተኛ ትምህርት  መግቢያ ውጤት  አስመዝግቦ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተመደበ:: 12ኛ ክፍል ላይ  የተጠናወተው ሱስ  ዩኒቨርሲቲ ዘልቆ  የመጠጥ እና የአደንዛዥ እጽ ተጠቃሚነቱ ተባብሶ ቀጠለ።

በወቅቱ በሱሱ ምክንያት የተፈጠረ ችግር ለእስር ዳረገው:: ከእስር እንደተለቀቀም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አቋረጠ፤ በመመለስ  የቤተሰብ ጥገኛ ለመሆን ተገደደ። እየቆየ ሲሄድ ደግሞ ከቤተሰብ ጋር  ግጭት ውስጥ ገባ። ከማኅበራዊ ሕይዎትም ተገለለ።

ለአሥራ አራት ዓመታት ከሌሎች ሰዎች ጋር መጋጨት፣ መሳደብ፣ “ግጠሙኝ!” ማለት፣ ሲከፋው ራሱን የመጉዳት ባሕሪያትን ማሳየት የእለት ተዕለት መገለጫው ሆነ:: ችግሩም እየባሰ ሲሄድ በቤተሰብ እና በጓደኛ ምክር እና እርዳታ  አማካይነት በደብረ ታቦር ከተማ በሚገኘው የሱስ ማገገሚያ  ማዕከል ሕክምና እንዲከታተል ተደረገ። በማዕከሉ ከአንድ ወር በላይ  የሥነ ልቦና እና አካላዊ ሕክምና እንደተደረገለትም ነግሮናል።

ዳንኤል በማዕከሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል፤ ከስፖርት በኋላ በተለያዩ መዝናኛ ቦታዎች ጊዜውን ያሳልፋል፣ መጽሐፍትን ያነባል፤ የተለያዩ ሥዕሎችንም  ይስላል።  አሁን ላይ ወጣቱ በተደረገለት ሕክምና “ሰላም ይሰማኛል፤ ጥሩ እንቅልፍም እተኛለሁ” በማለት ደስታውን በፈገግታ ነግሮናል::

በማዕከሉ የሚገኙ ዶክተሮች እንደ ጓደኛ እና ቤተሰብ ሆነው ክትትል እና ድጋፍ እንደሚያደርጉለትም ተናግሯል። አሁን ላይ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛል፤ ወደ ነበረበት ጤናማ ሕይወት ተመልሶ  መደበኛ ሥራውን ለማከናወን ራሱን አዘጋጅቷል:: “ሱስ ራስን ይጎዳል፣ ማህበራዊ ሕይወትን ያመሰቃቅላል፣ ያናጋል፣ ኢኮኖሚያዊ ችግር ያስከትላል እንዲሁም በራስ መተማመንን ያሳጣል:: ስለሆነም ነገን የተሻለ ለመኖር ነገሮችን በጥልቀት ማየት፣ መመርመር፣ ራስን  መግዛት እና የአቻ ግፊትን መቆጣጠር  ይገባል” በማለትም ለወጣቶች ምክረ ሐሳቡን አጋርቷል። በተለይም ቤተሰቦቹን በሱስ ምክንያት ሲያስቀይማቸው እና ሲያሰቃያቸው እንደነበር አሁን ላይ በቁጭት ይናገራል። ከነበረበት ሱስ አውጥተው ወደ ደብረታቦር ከተማ የሱስ ማገገሚያ ማዕከል እንዲመጣ ላረጉት በሙሉ ወጣት ዳንኤል  ምስጋናውን አቅርቧል።

በአማራ ክልል በተለያዩ ሱሶች የተጠቁ ዜጎችን ሕክምና ለመስጠት የሚያስችል የሱስ ማገገሚያ ማዕከል አቋቁሞ አገልግሎት እየሰጠ ያለው በደብረ ታቦር ከተማ የሚገኘው የሱስ ማገገሚያ ማዕከል ብቸኛ መሆኑ ይጠቀሳል። አንዳንድ የሱስ ተጠቂዎች አገልግሎቱን ፈልገው የሚሄዱትም በሱስ ውስጥ ቆይታቸው የደረሰባቸውን ጫና ተረድተው በራሳቸው ፍላጎት ሲሄዱ ሌሎቹ ደግሞ በቤተሰብ፣ በጓደኛ እና በሥራ ባልደረባ አማካኝነት እንደሆነ  የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን በመስክ ምልከታው ማረጋገጥ ችሏል።

ማዕከሉን እንደገቡ  ለሁለት ወር እና ከዚያ በላይ የግል እና የቡድን የሥነ ልቦና እና የመድኃኒት ሕክምና እንደሚሰጡ  የተናገሩት ደግሞ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የሱስ ማገገሚያ ማዕከል የአዕምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት ጋሻው ምህረት ናቸው። እንደ ዘርፉ ባለሙያ ማብራሪያ የሱስ ተጠቂዎች ወደ ማዕከሉ እንደመጡም ሁለንተናዊ ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ   የሱሱ ዓይነት፣ ሱሱ ያለበት ደረጃ ይለያል። ከሱስ ሕይወት ለመውጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተረጋግጦ “ከሱስ ሕይወት መውጣት እፈልጋለሁ፣ አካላዊ፣ አእምሯዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር አምጥቶብኛል፣ ማህበራዊ ሕይወቴን አናግቶታል ግን መውጣት አልቻልኩም፤ አቃተኝ፤ እርዱኝ” ብለው ለመጡ አገልግሎት ፈላጊዎች አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ ወደ ማገገሚያው እንደሚገቡም  አስገንዝበዋል::

በቤተሰብ እና በጓደኛ ድጋፍ አማካኝነት የሚመጡትን ደግሞ ግንዛቤው ብዙም ስለማይኖራቸው በመጀመሪያ ደረጃ አገልግሎቱን ለማግኘት እንዲዘጋጁ፣ እንዲነሳሱ፣ ፍላጎቱ እንዲኖራቸው ግንዛቤ ይፈጠርላቸዋል:: የምክር አገልግሎትም ይሰጣቸዋል። በየሳምንቱም ተመላላሽ ሕክምና ይሰጣቸዋል። ወደ ማገገሚያ ማዕከሉ የሚገቡ የሱስ ተጠቂዎች የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲያከናውኑ ይደረጋል ነው ያሉት።  አጠቃላይ ስለሱስ ምንነት፣ ስለጉዳቱ፣ ከሱስ አገግመው ሲወጡ ሊያጋጥማቸው ስለሚችሉ ጉዳዮች ትምህርት ይሰጣል።

ሱስ ሰዎች በአንድም  ሆነ በሌላ ምክንያት አነቃቂ እና አደንዛዥ ንጥረ ነገሮችን እንዲሁም ዕፆችን ሲጠቀሙ እና የመጠቀም ልማዳቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲመጣ የሚከሰት ነው::  የሚጠቀሙት ሱስ አምጭ እጽ አካላዊ፣ አእምሯዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና ሲያመጣባቸው  ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን አለመቻል ጉዳቱ ነው።

ሱስ በሁለት አይነት እንደሚከፈልም ባለሙያው አስገንዝበዋል። እነዚህም የንጥረ ነገር (የዕፅ) ሱስ የሚባሉት እንደ አልኮል መጠጥ፣ ጫት መቃም፣  ሲጋራ ፣ ትምባሆ፣ ሺሻ)ማጨስ እና አደንዛዥ ዕፆች (እንደ ኮኬይን፣ ሄሮይን፣ ካናቢስ /ሀሺሽ/) መጠቀም መሆኑን ባለሙያው አስገንዝበዋል። ሌላው የባሕሪ (የድርጊት) ሱስ ሲሆን ይህም ቁማር፣ የቪዲዮ ጌም እና ማህበራዊ ሚዲያን (ኢንተርኔትን) ከልክ በላይ መጠቀም እና መሰል ድርጊቶች ናቸው።

ባለሙያው እንዳብራሩት ሱስ እንደ ሌሎች በሽታዎች ታክሞ የሚድን ቢሆንም በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ ህመም አለመቁጠር፣ ቀለል አድርጎ መመልከት እና ተጠቂዎችን ወደ ሕክምና የማምጣት ችግር ይስተዋላል። ነገር ግን ሱስ ህመም መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያው ይዞት የሚመጣው ውስብስብ ችግርም ከፍተኛ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ወደ ማገገሚያ የሚገቡት የማልማት አቅም ያላቸው ወጣቶች መሆናቸው  ደግሞ ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል ነው ያሉት ባለሙያው።  ሱስ ከግለሰብ ችግር ባለፈ በሀገር ላይ  የሚያደርሰው ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ኪሳራው ከፍተኛ በመሆኑ ቤተሰብ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እና መንግሥት በተቀናጀ መንገድ መሥራት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል። ማዕከሉ ከክልሉ አልፎ ከአጎራባች ክልሎች እየመጡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ  በመሆናቸው ማዕከሉን በማስፋፋት የቅበላ አቅሙን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያስረዱት ባለሙያው፤ ለዚህም ቅን አሳቢዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

 

መረጃ

የሱስ ጠባሳዎች

 

አካላዊ ጠባሳዎች፦ የውስጥ አካላት እና የአእምሮ ህዋሳት መጎዳት።

ስነ-ልቦናዊ እና አእምሯዊ ጠባሳዎች፦ ድብርት እና ጭንቀት፣ በራስ መተማመን ማጣት እንዲሁም የትኩረት እና የማስታወስ ችግር።

ማህበራዊ እና ቤተሰባዊ ጠባሳዎች፦ የእምነት መጓደል፣ መገለል እና የቤተሰብ መበተን።

ኢኮኖሚያዊ ጠባሳዎች፦ ሱስ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ግለሰቦች ያፈሩትን ንብረት ሊያጡ፣ በእዳ ሊዘፈቁ እና ስራቸውን ሊያጡ ይችላሉ። ከሱስ ሲያገግሙ  ሕይወትን ከዜሮ መጀመር ትልቅ ፈተና ይሆናል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የመጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here