የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን አሉ?

0
49

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል፤ ይህን መነሻ በማድረግ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ የመገናኛ አማራጮች ሐሳባቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ፤ ከሰሞኑ ደግሞ በፖለቲካ እና የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ያላቸውን ርዕዮተ ዓለም በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ክርክር አድርገው ነበር:: እኛም ለአንባቢዎቻችን ይደርስ ዘንድ እንዲህ አሰናድተነዋል፤ መልካም ንባብ!

ብልጽግና ፓርቲ

ብልጽግና ፓርቲን በመወከል የድርጅቱን ማኒፌስቶ ያቀረቡት መስፍን አበጀ( ዶ/ር) ናቸው፤ እርሳቸው እንዳሉት  ብልጽግና የሚሠራው ያለፈውን ስህተት በማረም የወደፊቱን ብሩህ ተስፋ በመተለም ነው:: ሂደቱም የሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚነት ያረጋገጠች ሕብረ ብሔራዊ አንድነቷን የጠበቀች ኢትዮጵያን ለመገንባት ያለመ ነው:: ፓርቲው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሥርዓት ምን ይሁን? የሚለውን ካጋጠመው የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ስብራት ተነስቶ የራሱን ሀገር በቀል አዲስ ብያኔ ይዞ የመጣ ነው::

ዶክተር መስፍን እንዳሉት የብልጽግና  የፖለቲካ ፓርቲ መሠረቱ መደመር ነው:: ይህ የፖለቲካ እሳቤ እና ፍልስፍና “እኛ እና እነሱ” የሚለውን መፈራረጅ አስቀርቶ መሀል መንገድን የሚከተል ነው::

ብልጽግና ፓርቲ ሁሉንም ያካተተ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለመገንባት ለጸና ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት ነው ብሎ እንደሚያምንም አንስተዋል:: በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዘመናት በአሃዳዊ እና በብሔር ፖለቲካ ጫፎች መካከል ሲላተም መቆየቱን በመጠቆም “ብልጽግና ይዞት የመጣው የመደመር ፍልስፍና ደግሞ እነዚህን ጫፎች በማስታረቅ የሁሉንም ማንነትና ሀገራዊ አንድነት ሚዛን የጠበቀ ወርቃማ መንገድ ነው:: ብልጽግና ይህ መንገድ ለኢትዮጵያ የሕልውና መሠረት ነው ብሎ ያምናል” ብለዋል::

የብልጽግና ፓርቲን ስለ ዴሞክራሲ ግንባታ መንገዶች እና ተግባራዊ ምላሾችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ  ፓርቲያቸው ዴሞክራሲን ከመጠፋፋት ወደ መግባባት ማሸጋገር የሚል አቋም እንዳለው ነው ያቀረቡት:: “ዴሞክራሲ የሕልውናችን መሠረት ነው:: ዴሞክራሲ በሀገራችን  የዘመናት የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ያልተመለሰ የሕዝብ ጥያቄ ነው ብለን እናምናለን:: ስለሆነም የማግባባት ዴሞክራሲ የሀገራችን የዴሞክራሲ ሥብራት መዳኛ መንገድ ነው:: ይህን ፖለቲካ ከመጠፋፋት እና ከመጠላለፍ መንፈስ አውጥተን  በውይይት እና በሐሳብ ተቀባይነት የተመሠረተ አዲስ ምዕራፍ እንጀምራለን:: ብልጽግና ፓርቲ ዴሞክራሲን በመገንባት ሂደቱ በግለሰቦች ፍላጎት ሳይሆን በተቋማት ነጻነት ላይ መቆም አለበት ብለን እናምናለን” ነው ያሉት::

መስፍን አበጀ (ዶ/ር) እንደሚሉት የብልጽግና ፓርቲ ዋነኛው ግብ ሕብረ ብሔራዊት ሀገራዊ አንድነትን መገንባት ነው:: ፓርቲው ሕብረ ብሔራዊነትን እንደ አፍራሽ የሚያዩ ወይም ደግሞ ሀገራዊ አንድነትን እንደ ሥጋት የሚመለከቱ ዋልታ ረገጥ ዕይታዎችን  በሐሳብ ይሞግታል:: የሀገሪቱን ሥርዓት ወለድ ታሪካዊ ቁርሾዎች በውይይት ለመፍታት የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን በማቋቋም እና ባለፉት ጊዜያት የነበሩ ቁስሎችን በበቀል ሳይሆን በሽግግር ፍትሕ በመፈወስ የዴሞክራሲ ግንባታ ታሪክ አካል ነው ብሎ ያምናል::

የፖለቲካ ምሕዳር ማስፋትን በተመለከተ የብልጽግና ፓርቲ አቋምን መስፍን አበጀ (ዶ/ር) ሲናገሩ ፓርቲው “ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሀገር አጋር እንጂ የጥፋት ኃይል አይደሉም ብሎ ያምናል” ብለዋል:: ብልጽግና በኢትዮጵያ  ከመገዳደልና ከመጠፋፋት ፖለቲካ ወደ ውይይት እና  የሐሳብ የበላይነት ለማምጣት ታሪካዊ እርምጃዎችን እየወሰደ ያለ ፓርቲ ነው:: ይህ ሕጎችን በማሻሻል የሐሳብ አውድን በማስፋት ሁሉም ፓርቲዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ምቹ መደላደል እየፈጠረ ያለ የተግባር ፓርቲ ስለመሆኑ ጠቁመዋል::

የፍትሕ እና የዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኛነትን በተመለከተም ብልጽግና  የዴሞክራሲ ተቋማት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ፍርድ ቤቶች፣ የጸጥታ እና ሌሎች ተቋማት ከማንኛውም የፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ ሆነው በገለልተኝነት እንዲሠሩ  ታላላቅ የሪፎርም (የማሻሻያ) ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል:: በአማራ ክልልም ከለውጡ ማግስት የተለያዩ የሪፎርም ሀሳቦችን አንስተዋል፤ ለአብነትም በፍርድ ቤቶች፣ በፖሊስ እና በሌሎች የጸጥታ ተቋማት መዋቅሮች አዳዲስ የሪፎርም ሐሳቦችን  በመፍጠር አዳዲዲስ እርምጃዎችን ስለመወሰዱ ጠቅሰዋል:: የዳኝነት አስተዳደር ጉባዔ በአዲስ መልክ እንዲዋቀር ተደርጓል:: “በአጠቃላይ ፍትሕ  ለጥቂቶች  ሳይሆን ለሁሉም እኩል ተደራሽ በማድግ ተቋማት ለፖለቲካ ሳይሆን ለሕግ ብቻ እንዲገዙ እናደርጋለን” ብለዋል::

አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

አቶ መልካሙ ጸጋዬ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አብን ዴሞክራሲ ለአማራ ሕዝብ የሕልውና ጥያቄ ነው የሚል መርህ እንዳለው አስገንዝበዋል:: የአማራ ሕዝብ ቁጥሩንና ታሪካዊ ሚናውን የሚመጥን ፖለቲካዊ ውክልና ያጣው ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊ ባለመሆኑ ነው ብሎ ፓርቲያቸው ስለሚያምን መሆኑንም ለዚህ በምክንያትነት አንስተዋል:: የሚገነባው የዴሞክራሲ ሥርዓትም “አግላይነትን የሚቀብር እና አብላጫው ድምጽ አናሳውን የማያጠቃበትን የሀሳብ ብዝኃነት የሚከበርበት ይሆናል” ነው ያሉት:: “ዴሞክራሲ ለእኛ የሕዝባችንን የዳር ድንበር ሰላም እና የዜጎቻችንን በሕይወት የመኖር ዋስትና የምናረጋግጥበት መሣሪያችን ነው” ያሉት አቶ መልካሙ ሕገ መንግሥትን በተመለከተም “አብን ግልጽ አቋም አለው:: አሁን ያለው ሕገ መንግሥት የአማራን ሕዝብ ባለቤት ያላደረገ እንዲያውም በጨቋኝነት የፈረጀ እና ለጥቃት ያመቻቸ ሰነድ ነው:: እኛ የምንታገለው ሁሉን አቀፍ እና ዜጋ ተኮር ለሆነ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ነው”ብለዋል::

አቶ መልካሙ  ፌደራሊዝምን በተመለከተ እንዳብራሩት አሁን ያለው የጎሳ ፌደራሊዝም ሀገርን እያፈረሰ እና ወንድምን ከወንድም እያጋጨ ይገኛል::  ነገር ግን  አብን የሚያራምደው እውነተኛ ፌደራሊዝም የማንነት ጭቆናን የሚያስወግድ፣ በጎሳ አጥር ዜጎችን የማይከፋፍል፣ በዜጎች ፈቃድ ላይ የተመሠረተ እና ለአስተዳደር የተመቼውን ይሆናል:: ይህም ለአማራ ሕዝብ እና ለመላው ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፈውስ የሚሰጥ ነው ብሎ አብን ያምናል::

የዴሞክራሲ እና የፍትሕ ተቋማትን በተመለከተ የአብንን አቋም ሲያብራሩም አብን ተቋማት ከግለሰብ እና ከፓርቲ ተጽዕኖ ነጻ ካልሆኑ ዴሞክራሲ ዋጋ የለውም ብሎ ያምናል::  አብን ስልጣን ሲይዝ የምርጫ ሥርዓቱን፣ የምርጫ ቦርድን እና  የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ከፖለቲካ ፓርቲዎች እጅ ያወጣል:: ዳኞች እና የደኅንነት ተቋማት ለአንድ ብሔር ወይም ለአንድ ፓርቲ ሳይሆን ለሕግ ብቻ ተገዢ እንዲሆኑ ያደርጋል:: በተለይም  በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸሙ የዘር ማጥፋት እና የጅምላ መፈናቀል ወንጀሎችን የሚመረምርና ፍትሕ የሚሰጥ ገለልተኛ የፍትሕ አካል መገንባት ቀዳሚ አጀንዳው ይሆናል” ብለዋል::

ተቀቋማት ሲጠነክሩ ሕዝብ በሕግ ፊት እኩል ይሆናል የሚል መርህ እንዳለው የገለጹት የአብን ተወካይ   የሀገሪቱ  የዴሞክራሲ ፋና  የሚበራው ሕገ መንግሥቱ የሁሉም ሲሆን እና ተቋማት   ፍትህን ሲያነግሱ ብቻ ነው:: አብን የሚታገለውም በሕግ ፊት ሁሉም እኩል የሚሆንባትን ፍትህ እንደ ሰዓት ቀመር ትክክለኛ የምትሆንበትን እና ተቋማት ከፖለቲካ ነጻ የሚሆኑበትን  ኢትዮጵያን ለመገንባት ነው::

የአማራ ዴሞክራሲ ኃይሎች ንቅናቄ

አዴኃንን በመወከል የፓርቲያቸውን ማኒፌስቶ ያስተዋወቁት ደግሞ አቶ ራስወርቅ መላኩ ናቸው:: አዴኃን ከዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አኳያ  የሕገ-መንግሥት ሽግግር ወደ ዜግነት ፌደራሊዝም እንዲመጣ እንደሚሠራ አንስተዋል፤ ዋና ግቡም አሁን ያለውን የአስተዳደር መዋቅር ሙሉ በሙሉ በማሻሻል ብሔር ላይ የተመሠረተውን የፌደራሊዝም ሥርዓት ወደ አካባቢያዊ እና የዜግነት ፌደራሊዝም  መቀየር መሆኑን ነው የጠቆሙት::

“ደኅንነት ለሁሉም በሚል መርህ ከዘላቂ ጦርነት ዝግጅት ወደ ዘላቂ ሰላም መሸጋገር እንፈልጋለን:: ይህንንም አዴኃን አበክሮ ይሠራል:: ለዚህ ይረዳን ዘንድ የደኅንነቱን ዘርፍ በባለሙያዎች መገንባት እና ለሁሉም ወታደራዊ ዘርፍ በሲቪል የሚመራ  የቁጥጥር ሥርዓት እናቋቁማለን:: በዚህም የፍትሕ ሥርዓቱን ገለልተኛነት እናረጋግጣለን” ብለዋል::

አቶ አቶ ራስወርቅ በንብረት ባለቤትነት ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያም  ፓርቲያቸው አዴኃን  የግለሰቦች የመሬት ባለቤትነትን በሕግ እንደሚያጸድቅና ለሕዝቡ የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ መስጠትን ግቡ ያደርጋል:: “በግብርናው ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር ማድረግ፣ ለአነስተኛ ንግድ የብድር እና አቅርቦቶችን ማመቻቸት፣ ያለ ካሳ በመንግሥት የሚደረግን ማፈናቀልን ማስቆምም ዓላማው ነው ብለዋል::

በአሁኑ ሰዓት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በግጭት ላይ ያለውን ማሕበረሰብ ወደ ሰላም እና መልሶ ማቋቋም፣ በተለያየ መንገድ በትጥቅ ትግል ተሰማርተው ያሉ ኃይሎችን በማነጋገር  ወደ ሰላም እና ፍትሕ እንዲመጡ ማድረግ እና በክልሉ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ዋነኛ የፓርቲው ግብ መሆኑን ነው ያስረዱት::

የአዴኃንን በብሔራዊ እርቅ ላይ ያለውን አቋም ተወካዩ ያስረዱ ሲሆን በዚህም  በሐሰት የተፈጠሩ ትርክት ላይ በተለይም እንደ ሀገር በአማራ ሕዝብ ላይ ተዘርቶ የቆየውን ጥላቻ በማስቀረት እውነተኛ እና ሀቀኛ ኢትዮጵያዊነትን በእርቅ እንዲቋጭ እንደሚያደርግ፣ በቀጣይነትም የአማራ ሕዝብ በመላው ኢትዮጵያ በዜግነቱ ተከብሮ የሚኖርበትን ሀገር እንደሚያረጋግጥ ገልጸዋል:: “ይህንን ለማረጋገጥም ርዕዮተ ዓለማችን ሶሻል ሊበራሊዝም ነው:: ይህ ሶሻል ሊበራሊዝም በግለሰቦች መብት ላይ የተመሠረተ ሆኖ ግለሰቦች በነጻነት በሀገራቸው ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚኖሩባት እና በተለይም የአማራ ሕዝብ ሰፊ እና በመላው የሀገሪቱ ክፍል ተበትኖ ያለ በመሆኑ በነጻነት እንዲኖር ሊበራል ዴሞክራሲ በሀገራችን ውስጥ ያስፈልጋል ብለን እናምናለን” ብለዋል::

አዴኃን የፍትሕ ሥርዓቱን በተመለከተ በተወካዩ በኩል ባጋራው ሐሳብ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት፣ ዐቃቢያነ ሕጎች እንዲሁም የደኅንነት ተቋማት በአሁኑ ጊዜ በተለያየ መንገድ በተለይም ከደመወዝ ማነስ የተነሳ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እና  የሙያ (ፕሮፌሽናሊዝም) መበረዝ በሰፊው የሚታይባቸው ተቋማት መሆናቸውን ጠቅሰው  ፓርቲያቸው ግን ይህን  ሥርዓት በማስተካከል  ሕገ መንግሥት እና የፍትሕ ተቋማት እንዲከበሩ የበኩላን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል::

 

መረጃ

 

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ይካሄዳል፡፡

በጠቅላላ ምርጫው 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች ይወዳደራሉ፡፡

የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 26 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ነው፡፡

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የመጋቢት 21  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here