ዕድገትን የሚያፀኑት የዕውቀት ቤቶች

0
72

ዙሪያ ገባዋን በውኃ የተከበበችው ትንሿ ሀገር ሲሸልስ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ፣ ሁሉም የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን ተደራሽነትን እና አሳታፊነትን  ባካተተ መልኩ የዘረጋችው የትምህርት አቀራረብ ዘዴ ከአፍሪካ ተጠቃሽ አድርጓታል:: የሲሼልስ ትምህርት ስርዓት እና የጥራት ማሻሻያ ሪፖርት እንደሚያመላክተው በተለይም የአቅም ችግር ያለባቸው ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርት ርቀው እንዳይቀሩ በመሥራት ትምህርትን ፍትሐዊ እና የሁሉም መብት እንዲሆን አድርጋለች::

የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ከፍተኛ የፖሊሲ ትኩረት የሚፈልግ ሲሆን ሲሸልስ ይህን በተግባር ማሳየት ችላለች::

ሀገሪቱ በዩኔስኮ የሚተገበሩ መመሪያዎችን በመከተል “ሁሉም ልጅ ትምህርቱን በት/ቤት ውስጥ ይካተታል” የሚለውን መርህ በትክክል ፈጽማለች:: በተግባር ይህን ለማሳካት ሲሸልስ በት/ቤቶች ውስጥ የልዩ ፍላጎት መምህራንን በመመደብ፣ ለተማሪዎች የማማከር  አገልግሎቶችን በመስጠት እንዲሁም የመማሪያ መርጃ መሳሪያዎችን በማሟላት ተማሪዎችን በእያንዳንዱ ፍላጎታቸው መሰረት እያገዘች ትገኛለች:: ይህ የግል ድጋፍ አቀራረብ ተማሪዎች የሚያጋጥሟቸውን እንቅፋቶች እንዲቀንሱ እና በትምህርታቸው እንዲበረታቱ ያግዛል::

ሀገሪቱ በመምህራን ብቃት ላይም ትልቅ ትኩረት አድርጋለች:: ለመምህራን ተጨማሪ ሥልጠና በመስጠት የተማሪዎችን አቅም መሰረት አድርገው ማስተማር እንዲችሉ አድርጋለች:: ይህ ደግሞ የመማር ማስተማሩን ሂደት   እንዲሻሻል አድርጎታል::

ሲሸልስ የትምህርት ቤት አካባቢን  እና መሰረተ ልማትን በማሻሻል እንዲሁም አስፈላጊ ግብአቶችን በማሟላት ምቹ  እና ተስማሚ መዋቅሮችን አዘጋጅታለች:: በተጨማሪም ወላጆችና ማኅበረሰቡ በትምህርት ሂደት እንዲካተቱ የተለያዩ መንገዶችን ፈጥራለች:: ይህ ደግሞ ተማሪዎችን ለመደገፍ አጠቃላይ አካባቢያዊ የኔ ባይነት እንዲፈጠር ያግዛል:: በትምህርት ጥራትና በአካቶ አቀራረብ ያሳየችው ተሞክሮም ለሌሎች ሀገራት ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ነው::

በሀገራችንም የተለያዩ ሞዴል ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ፤በመገንባት ላይም ናቸው:: ለአብነት በአማራ ክልል ከሁለት  ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ አራት ሞዴል ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ ነው:: እነዚህ  ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ተስፋ ሰጭ ናቸው ተብሏል::

ከሚገነቡት መካከል በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማ በስድስት ነጥብ ስምንት ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባው ሞዴል ትምህርት ቤት የክልሉን የትምህርት መሠረተ ልማት ለማዘመን የተዘጋጀ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኀይለገብርኤል አድማሱ ገልፀዋል::  እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ ግንባታው በ2018 ዓ.ም መስከረም 10 ቀን የተጀመረ ሲሆን እስከ  (የካቲት የመጨረሻ ሳምንት)  42 ነጥብ 09 በመቶ ደርሷል:: ግንባታው በተያዘው ዓመት መጨረሻ ተጠናቆ በ2019 ዓ.ም መስከረም ወር ለአገልግሎት እንደሚበቃ  ተናግረዋል::

ትምህርት ቤቱ የአስተዳደር ሕንጻ፣ ሁለት ዘመናዊ ላብራቶሪዎች፣ አራት የመማሪያ ብሎኮች (እያንዳንዳቸው 10 ክፍሎች ያላቸው)፣ ላይበራሪ፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ ካፍቴሪያ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ክሊኒክ፣ የስፖርት ሜዳዎች (እግር ኳስ፣ እጅ ኳስ እና ባስኬት ቦል) እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ክፍሎችን  ያካትታል:: ትምህርት ቤቱ ተጠናቆ የመማር ማስተማር ሥራውን  ሲጀምር በአንድ ክፍል 40 ተማሪዎችን በመቀበል እስከ አንድ ሺህ 600 ተማሪዎች የመያዝ አቅም እንዳለውም ጠቁመዋል::

እንደ አቶ ኀይለገብርኤል ማብራሪያ በቀጣይ የትምህርት ዘመን በመጀመሪያው ዙር አንድ ሺህ የሚደርሱ የ9ኛ ክፍል ተማሪዎችን በመቀበል ሥራ እንደሚጀምርም ዕቅድ ተይዟል::

የፍኖተ ሰላም ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ ታደሰ በበኩላቸው በከተማው ከአምስት  ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የሚገነባው ሞዴል ትምህርት ቤት በዞኑ ላሉ ሌሎች ትምህርት ቤቶች ልምድ የሚወስዱበት  እንደሚሆን ገልጸዋል:: ትምህርት ቤቱን በቀጣይ ዓመት ሥራ ለማስጀመር የመምህራን እና የሌሎች ተጨማሪ የሰው ኀይሎች ለማሟላት የቅጥር በጀት ለማስያዝ ዝግጅት መጀመሩንም አመልክተዋል::

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ በዘመናዊ የትምህርት እድገት  ትምህርትን በጥራት መስጠት ከሀገራዊ እድገት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ጉዳይ ነው። በዚህ አስፈላጊ ተግባር ውስጥ ሞዴል ትምህርት ቤቶች የሚጫወቱት ሚና ደግሞ ታላቅ ነው:: የትምህርት ጥራትን ለማሻሻልም ቀዳሚ መስፈርት ናቸው።

ሞዴል ትምህርት ቤቶች በመሠረታዊነት ግብአቶችን ያሟሉ  ናቸው። የተሻለ የመምህራን ብቃት፣ ዘመናዊ የመማሪያ መሳሪያዎች፣ ቤተ-መጻሕፍት፣ የሳይንስ ላብራቶሪዎች እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ የተሟሉባቸው እነዚህ ት/ቤቶች የመማር እና የማስተማር ሂደትን ወደ አዲስ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ናቸው።

በሞዴል ትምህርት ቤቶች በሚገኙ መምህራን በኩል የሚታየው ለውጥ እጅግ ታላቅ ነው። የተሻለ ሥልጠና እና ተሞክሮ ያላቸው መምህራን ተማሪዎችን በማነቃቃት፣ በማነሳሳት እና በአስተሳሰብ በማበረታታት ተማሪዎች እውቀትን በቀላሉ እንዲያገኙ ያግዛሉ። እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ትምህርት በአንደኛው ወገን ከመጽሐፍ ብቻ ወጥቶ ወደ ተግባራዊ ልምድ ሲያመራ ተማሪዎች ያገኙት እውቀት የተጠናከረ እና የማይረሳ ይሆናል። በተማሪዎች ዘንድ  የሚታየው ልዩነትም ግልጽ ነው። በእነዚህ ት/ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች በአካዳሚክ ውጤታቸው ላይ ግልጽ እድገት ያሳያሉ፤ ከዚህ በላይ አእምሯቸው መፍትሔ በማፈላለግ፣  በፈጠራ እና በአስተሳሰብ ይጎለብታል።  በክፍል ውስጥ ንቁ ተሳታፊዎች ይሆናሉ፤ ይህም የመማር ፍላጎታቸውን እና የራሳቸውን እምነት ያጠናክራል።

ሞዴል ትምህርት ቤቶች ለሌሎች ት/ቤቶች እንደ ምሳሌ በመሆን በአጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱን ያነሳሳሉ። ከእነዚህ ተሞክሮዎች በመማር ሌሎች ት/ቤቶችም የጥራት ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ዕድል ይፈጠራሉ።

በአጠቃላይ ሞዴል ትምህርት ቤቶቹ የተሟላ ግብአት በመኖራቸው የመማር ሂደትን ያበረታታሉ፣ የመምህራን አቅምን ያጎልብታሉ፣ በተማሪዎችም ላይ አዎንታዊ እና ዘላቂ ተፅእኖ ያሳያሉ። ይህም  ለሀገር እድገት  መሠረት ይሆናል።

በክልሉ ባሉ አራት ከተሞች ጥራታቸውን የጠበቁ ሞዴል ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ የሲቪል ምህንድስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል ንብረት  ናቸው:: እንደ ዳሬክተሩ ገለጻ በፍኖተ ሰላም ከተማ ከሚገነባው ሞዴል ትምህርት ቤት   በተጨማሪ በደብረ ማርቆስ ከተማ  በ486 ሚሊዮን ብር ወጪ ሞዴል ትምህርት ቤት እየተገነባ ነው:: በአሁኑ ወቅት ግንባታው 30 ነጥብ 8 በመቶ ደርሷል::

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም የአለላ ሞዴል 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ግንባታም በ561 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተከናወነ ሲሆን አሁን ላይ ግንባታው 38 ነጥብ 78 በመቶ ላይ ደርሷል፤ በተመሳሳይ በ501 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ ያለው በደቡብ ወሎ ዞን መቅደላ ከተማ የማሻ ሞዴል 2ኛ ደረጃ ት/ቤት 42 ነጥብ 1 በመቶ ተከናውኗል::

የሞዴል ትምህርት ቤቶች አጠቃላይ ወጭ በፌዴራል መንግስት ድጋፍ  መሆኑን አቶ ሚካኤል ጠቁመዋል:: ሞዴል ትምህርት ቤቶቹ የተሟላ መሠረተ ልማት እና ዘመናዊ መገልገያዎችን በመያዝ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ትልቅ አቅም እንደሚሆኑ ተናግረዋል::

ከአካባቢው ማህበረሰብ የሚደረገው ክትትልና ድጋፍም የግንባታ ጥራትን ለማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ ይህንን በማጠናከር መሻሻል አለባቸው የሚሏቸውን ሀሳቦች በመስጠት ትብብራቸው እንዲቀጥል   አቶ ሚካኤል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::

 

ግእዝ በአማርኛ

ሦር  —   በሬ

ላሕም– ላም

ቴፈን — ወይፈን

ሐርጌ —  ጊደር

ጣዕዋ —  ጥጃ

በግዕ —  በግ

ጠሊ —  ፍየል

(ሰናይት በየነ)

በኲር የመጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here