ስቴቨን ኮቪ፣ ሮጀር ሜሪል እና ሬቤካ ሜሪል በጋራ የጻፉት “First Things First” የተሰኘው መጽሐፍ፣ ጊዜን ስለማስተዳደር ከተጻፉ መጻሕፍት ሁሉ ቀዳሚና ተጽዕኖ ፈጣሪ ተብሎ ይታመናል::
መጽሐፉ በጣም በተጣደፈ ዓለም ውስጥ ትክክለኛውን ነገር በትክክለኛ ጊዜ ስለማድረግ ነው የሚመክረው:: በመጽሐፉ ውስጥ በሰዓት እና በኮምፓስ መካከል ያለው ልዩነት ቀርቧል::
ሰዓት ፍጥነታችንን፣ ቀጠሮዎቻችንን እና የዕለት ተዕለት ሥራዎቻችንን ወክሎ ቀርቧል:: “ምን ያህል ፈጣን ነን?” የሚለውን ይለካል:: በአንጻሩ ኮምፓስ ራዕያችንን፣ እሴቶቻችንን እና የሕይወት አቅጣጫችንን ይወክላል:: “ወዴት እየሄድን ነው?” የሚለውን ይጠቁመናል::
መጽሐፉ በጣም በፍጥነት መሮጥህ ፋይዳ የለውም፤ የምትሮጥበት አቅጣጫ (ኮምፓስህ) የተሳሳተ ከሆነ ትርፉ ድካም ነው ይላል:: ከፍጥነት ይልቅ ለአቅጣጫ ቅድሚያ እንድንሰጥ ያስተምረናል::
መጽሐፉ ተግባራትን በሁለት ወገን ይከፍላቸዋል፤ አስፈላጊ እና አስቸኳይ ብሎ:: እነዚህንም በአራት ክፍሎች ያስቀምጣቸዋል::
የመጀመሪያው ተግባር አስቸኳይ እና አስፈላጊ ነው:: ቀውሶች፣ የደረሱ ቀጠሮዎች፣ ድንገተኛ አደጋዎች በዚህ ውስጥ አሉ:: በዚህ ሁኔታ ውስጥ ስንኖር ውጥረት ይከበናል::
ሁለተኛው ተግባር አስፈላጊ ግን አስቸኳይ ያልሆነ ነው:: ይህ የጥራት እና የውጤታማነት ክፍል ነው:: እቅድ ማውጣት፣ መማር፣ ጤናን መጠበቅ፣ ግንኙነትን ማጠናከርን ያካትታል:: ኮቪ እንደሚለው ስኬታማ ሰዎች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት እዚህ ክፍል ላይ ነው::
ሦስተኛው አስቸኳይ ግን አስፈላጊ ያልሆነ ተግባር ነው:: የሌሎች ሰዎች ጉዳይ፣ አላስፈላጊ ስልኮች፣ ስብሰባዎች በዚህ ውስጥ ይካተታሉ:: እዚህ ክፍል ላይ የምናጠፋው ጊዜ “ስራ የበዛብን” እንዲመስለን ያደርጋል እንጂ ውጤት የለውም::
አራተኛው አስቸኳይ ያልሆነ እና አስፈላጊ ያልሆነ ተግባር ነው:: ጊዜ ገዳይ ነገሮች፣ ከመጠን ያለፈ ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም፣ ወሬ፣ ሐሜት፣ ዜና ማየትን ያካትታል:: ይህ የብክነት ክፍል ነው::
ኮቪ የሚሰጠን ታዋቂ ምሳሌ አለ:: “አንድ ባዶ ማሰሮ ቢሰጥህና በትላልቅ ድንጋዮች፣ በጠጠር፣ በአሸዋ እና በውኃ እንድትሞላው ቢነገርህ፤ መጀመሪያ አሸዋውን እና ጠጠሩን ካስገባህ ትላልቆቹ ድንጋዮች አይገቡልህም” ይላል::
በትላልቆቹ ድንጋዮች የተመሰሉት በሕይወት ውስጥ ትልቁን ዋጋ የምንሰጣቸው ነገሮች (ጤና፣ ቤተሰብ፣ ትልቅ ፕሮጀክቶች) ናቸው:: አሸዋ እና ጠጠር የተባሉት ደግሞ ጥቃቅንና ትርጉም የሌላቸው የዕለት ተዕለት ሥራዎች ናቸው:: ትላልቆቹን ድንጋዮች (First Things) መጀመሪያ ካላስገባህ ሕይወትህ በትናንሽ እና ዋጋ በሌላቸው ነገሮች ትሞላለች የሚለው የመጽሐፉ ዋና ሐሳብ ነው::
በየቀኑ ጠዋት ስንነቃ አእምሯችን በሺዎች በሚቆጠሩ የአማራጭ ማዕበሎች ይጥለቀለቃል:: “ምን ልልበስ? የትኛውን ስልክ ልመልስ? የትኛውን ሥራ ላስቀድም?” የሚሉ ጥቃቅን ውሳኔዎች የአእምሯችንን ጉልበት ይመጥጡታል:: አብዛኞቻችን ሕይወታችንን የምንመራው እንደ ንቁ ካፒቴን ለመሆን በማሰብ ቢሆንም በተግባር ግን ለሚጮኸውና ለአስቸኳዩ ነገር እንጂ ለሚጠቅመውና ለዋናው ነገር ቦታ ስንነፍግ እንታያለን:: ሕይወታችንን በውሳኔዎች ካልመራናት በሁኔታዎች እንመራለን:: ደራሽ ችግር እና እሳት በማጥፋት ለሌሎች መልስ በመስጠት እንኖራለን::
የነርቭ ሳይንስ ምሁራን እንደሚነግሩን የሰው ልጅ አእምሮ ውሳኔ ሰጪ ክፍል (Prefrontal Cortex) በቀን ውስጥ ሊያስተናግደው የሚችለው የውሳኔ መጠን ውስን ነው:: ዳንኤል ካህነማን “ቲንኪንግ ፋስት ኤንድ ስሎው” በሚለው መጽሐፉ እንደሚገልጸው አእምሯችን ብዙ ጥቃቅን ውሳኔዎችን ሲያደርግ የውሳኔ ዝለት ይገጥመዋል:: ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች አስቀድሞ አለመለየት አእምሮአችን ዋና ለሆኑ ጉዳዮች የሚሆን ጉልበት እንዲያጣ ያደርገዋል:: ስለዚህ ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች መለየት ለስኬት ብቻ ሳይሆን ለአእምሮ ጤናም ወሳኝ ነው::
በነርቭ ሳይንስ እይታ ጤና ለሁሉም ነገር መሠረት ነው:: ማቲው ዎከር ዋይ ዊ ስሊፕ በሚለው መጽሐፉ እንቅልፍ ማጣት የአንጎልን የመማርና የማስታወስ ብቃት በ40 በመቶ እንደሚቀንስ ይገልጻል:: ጤናን (አካላዊ እና አእምሯዊ) ቅድሚያ አለመስጠት ማለት ሌሎች ስኬቶችን የምናጣጥምበትን መሣሪያ መስበር ማለት ነው:: የተመጣጠነ ምግብ፣ ስፖርት እና በቂ እንቅልፍ የቅድሚያ ዝርዝራችን አናት ላይ መሆን አለባቸው ይላል:: ምክንያቱም ያለ እነዚህ አእምሮ ወደ የመከላከል ስሜት (Survival Mode) ይገባና የፈጠራ ብቃቱ ይሞታል::
ብዙዎች መንፈሳዊነትን ከሃይማኖት ጋር ብቻ ያያይዙታል:: ነገር ግን በሳይንሱ እይታ መንፈሳዊነት ከራስ እና ከፈጣሪ ጋር ያለው ግንኙነት ውስጣዊ መረጋጋት ይሰጣል:: አዘውትረው የሚጸልዩ ወይም የሚያሰላስሉ ሰዎች ጭንቀትን የሚቆጣጠረው የአንጎላቸው ክፍል (አሜግድላ) ሰላማዊ እና የተረጋጋ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ:: የሕይወት መርሆዎች እና እሴቶች ላይ መጽናት በውጫዊ ማዕበል እንዳንናወጥ የሚረዳን መልሕቅ ሆኖ ይጠቀሳል::
አእምሯችን እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ የመለወጥ እና የመማር ብቃት አለው:: አዳዲስ ክህሎቶችን መማርና ማንበብ አእምሮ አዳዲስ የነርቭ መስመሮችን እንዲዘረጋ ያደርገዋል:: ጄምስ ክሌር “አቶሚክ ሀቢትስ” በሚለው መጽሐፉ በየቀኑ 1 በመቶ ራስን ማሻሻል በዓመት መጨረሻ 37 እጥፍ የተሻለ ሰው እንደሚያደርገን ጽፏል::
ሥራ የሕይወታችን ዓላማ መገለጫ መሆን አለበት:: ካል “ኒውፖርት ዲፕ ወርክ” በሚለው መጽሐፉ ትኩረትን ሳይከፋፍሉ በአንድ ትልቅ ነገር ላይ መስራት ብርቅዬና ውድ ችሎታ መሆኑን ይገልጻል:: ይህን ተከትሎ የምናገኘው የገንዘብ ነፃነት ደግሞ ለምንወዳቸው ነገሮች ጊዜ እንድንሰጥ ዕድል ይሰጠናል:: ነገር ግን ሥራ ከቤተሰብና ከጤና በላይ ቅድሚያ ሲሰጠው ውጤቱ የጉልበት መሟጠጥ ይሆናል::
ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ማከናወን አይቻልም:: ለዚህ ነው ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች እንዴት እንለይ? የሚለው ቀጥሎ ጥያቄ የሚመጣው::
የአይዘንሃወር “ማትሪክስ” የሚባል መርህ አለ:: ነገሮችን “አስቸኳይ” እና “አስፈላጊ” በሚል መክፈል ነው:: ለምሳሌ ጤና አስፈላጊ ነው፤ ግን አስቸኳይ ላይሆን ይችላል:: ስልክ መመለስ ግን አስቸኳይ ነው:: ግን ደግሞ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል:: ይህ መርህ መቅደም እና መዘግየት ያለባቸው ጉዳዮቻችንን የሚለይልን ነው::
ሌላው የ 20/80 ሕግ (ፓሬቶ መርህ) ይባላል:: 20 በመቶ የሚሆኑት ጥራት ያላቸው ተግባራት 80 በመቶ የሚሆነውን ውጤት እንደሚያመጡ መረዳት ነው::
ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች እንዳናሳካ የሚከለክሉን ዋና ዋና እንቅፋቶች አሉብን:: ሰዎችን ደስ ለማሰኘት መሞከር ቀዳሚው ነው:: ለሌሎች “እሽ” ስንል ለራሳችን “እምቢ” እያልን መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል::
የማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ ሁለተኛው እንቅፋት ነው:: አእምሯችንን ርካሽ በሆነ ዶፓሚን (አነቃቂ ሆርሞን) በመሙላት ትልልቅ ግቦች ላይ እንዳያተኩር ያደርገዋል:: ነገሮችን ማሳደር (ነገ እሠራዋለሁ ማለትም) ዛሬ መደረግ ያለበትን ለነገ በማስተላለፍ የጭንቀት ክምችት እንዲፈጠርብን የሚያደርግ እንቅፋት ነው::
ቅድሚያ የሚሰጡ ነገሮች ቋሚ አይደሉም፤ እንደ ሕይወት ዘመን (በወጣትነት፣ በወላጅነት፣ በሽምግልና) ሊቀያየሩ ይችላሉ:: ሆኖም ግን ዛሬ በምንሰጠው ትኩረት ልክ ነገን እንቀበላለን:: ስቲቨን ኮቪ እንዳለው ጊዜውን የሚያስተዳድር ሕይወቱን ያስተዳድራል:: “ዛሬ የማደርጋቸው ነገሮች ወደምፈልገው ማንነት እየወሰዱኝ ነው ወይስ ካለሁበት ወደ ኋላ እየጎተቱኝ?” ብለን መጠየቅ አለብን::
(አቢብ አለሜ)
በኲር የመጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


