የመኸር እርሻ ዝግጅት እና የግብዓት አቅርቦት

0
72

አርሶ አደር አሥራት አሸናፊ  በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አየሁ ጓጉሳ ወረዳ ሦስቱ ጀበላ ቀበሌ  በእርሻ ሥራቸው ጠንካራ እና ታታሪ ከሚባሉት ግንባር ቀደም ናቸው:: ለዚህ ማሳያውም ለ2018//19   የምርት ዘመን ማሳቸውን አፅድተው የእርሻ ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑን በስልክ በነበረን ቆይታ መረዳት ችለናል። በተለይም በዚህ ዓመት የእርሻ ሥራቸውን በትራክተር እንደሚያርሱም ነው የተናገሩት።

አርሶ አደሩ በመጭው መኸር በአንድ ሄክታር ተኩል ማሳ ላይ በቆሎ፣ በሁለት ሄክታር በርበሬ እና ስንዴ፣ በግማሽ ሄክታር ዳጉሳ እና ሌሎች ሰብሎችን ለመዝራት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ ነው። በአሁኑ ወቅት ማሳን ማፅዳት፣ ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች የእርሻ ቦታን አርሶ ማለስለስ እና ግብዓት የማሰባሰብ ሥራ እያከናወኑ ነው። ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ (መጋቢት መጨረሻ ሳምት) ድንች እንደሚዘሩም ነው የተናገሩት።

አርሶ አደሩ በመጭው መኸር ለሚያከናውኑት የእርሻ ሥራ አሥር ኩንታል ዳፕ፣ አሥር ኩንታል ዩሪያ እና ሦስት ከረጢት የበቆሎ ምርጥ ዘር እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል። ለዚህም ወረዳው ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ እያስገባ በመሆኑ እርሳቸውም ቀድመው ለሚዘሩት ሁለት ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ገዝተዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ለ2018/19 የምርት ዘመን ለአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ እያሰራጨ መሆኑን አስታውቋል። በጽ/ቤቱ የግብርና ግብዓት አቅርቦት እና ገጠር ፋይናንስ ቡድን መሪ አቶ መሠረት አንጀት ለበኵር ጋዜጣ እንደተናገሩት አርሶ አደሩ ከበሬ ጫንቃ ተላቆ ወደ ዘመናዊ ግብርና እንዲሸጋገር እና በኩታ ገጠም እንዲያለማ በትኩረት እየተሠራ ነው። በአሁኑ ወቅት በወረዳው 34  ትራክተር፣ 132 የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፕ፣ ስምንት የበቆሎ መፈልፈያ እና ሁለት ኮምባይነር ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን አስረድተዋል። እንዲሁም አርሶ አደሩ የብድር አቅርቦት ተመቻችቶለት ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን እንዲገዛ እየተደረገ ነው። በዚህ ዓመትም ተጨማሪ ሰባት ትራክተሮችን ለመግዛት መታቀዱን ነው የተናገሩት።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምርታማነትን ለማሳደግም ለ2018/19 የምርት ዘመን ዳፕ እና ዩሪያን ጨምሮ 196 ሺህ 652 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ታቅዷል። ከዚህ ውስጥ በአሁኑ ወቅት 79 ሺህ 235 ኩንታል ወደ ወረዳው መጋዝን ገብቷል፤ ሰባት ሺህ 120 ኩንታሉ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል። በቀጣይ ሦስት ሺህ 200 ኩንታል በቆሎ፣ 270 ኩንታል ጤፍ እና 320 ኩንታል አኩሪ አተር  ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት መታቀዱንም አብራርተዋል። አርሶ አደሩ ምርታማነታቸው የተሻሻሉ የበቆሎ ዝርያዎች እንዲቀርቡለት  የሚያነሳውን ጥያቄ ለመመለስ  የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ቡድን መሪው ጠቁመዋል::

በተመሳሳይ የሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ለመጭው የምርት ዘመን በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል። የመምሪያው የግብዓት አቅርቦት ቡድን መሪ አቶ አምደወርቅ ልየው እንደገለጹት በዞኑ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እና የግብዓት አቅርቦቱ በፍጥነት ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ከግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በምርጥ ዘር፣ በአፈር ማዳበሪያ፣ በሜካናይዜሽን፣ በፀረ አረም እና ፀረ ተባይ ኬሚካል አቅርቦት በቅንጅት እየተሠራ ነው።

ለ2018/19 የመኸር ሰብል ልማት የሚያገለግል አንድ ሚሊዮን 220 ሺህ ኩንታል ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ እና 35 ሺህ ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል። ይህንን ለማሳለጥም የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በጥሩ ሁኔታ ድጋፍ እና ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል። በተለይ የስንዴ፣ የጤፍ እና የቦሎቄ ምርጥ ዘሮችን ኮርፖሬሽኑ ለዞኑ እያቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል። እስካሁን በተደረገው ጥረት ከ420 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዞኑ መግባቱን ነው መምሪያው ያስታወቀው።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እና የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካትም የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በግብርና ግብዓት አቅርቦት እና አገልግሎት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር መጋቢት 11 ቀን 2018 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አካሂዷል። የውይይት መነሻ ፅሑፍ ቀርቦም ሐሳቦች ተንሸራሽረውበታል።

በውይይት መድረኩ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን እና መደገፍ፣ ሜካናዜሽንን ማስፋፋት፣ የተሻሻሉ የምርጥ ዘር ዓይነቶችን ማቅረብ፣ ዘመናዊ የአመራረት ዘዴ መከተል፣ ጥራቱን የጠበቀ የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር በወቅቱ ማቅረብ እንደሚገባም ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ ከ224 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በላይ የውኃ ሃብት፣  35 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ የእርሻ መሬት እና በርካታ አምራች የሰው ኀይል ያላት ሀገር መሆኗን የተናገሩት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ የሺመቤት ነጋሽ ናቸው። እነዚህን ጸጋዎች በአግባቡ ተጠቅሞ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ የተቋሙ ዋነኛ ግብ መሆኑንም አስረድተዋል።

ኮርፖሬሽኑ በ2008 ዓ.ም በሚኒሥትሮች ምክር ቤት የተቋቋመ ሲሆን በዋናነት የግብርና ምርት አቅራቢ፣ የሜካናይዜሽን አገልግሎት እና ቴክኒክ እንዲሁም የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦትን ጨምሮ አምስት ድርጅቶችን በማቀናጀት ግብርናውን ለማዘመን እና የግብዓት እሴት ሰንሰለትን በየደረጃው ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ነው ያስረዱት። በቀጣይ ከተደራሽነት፣ ቅርንጫፎችን ከማስፋፋት፣ ምርታማነታቸው እየቀነሰ የመጡትን የዘር ዓይነቶች በአዲስ የመተካት ሥራ በትኩረት የሚሠራባቸው ነጥቦች ናቸው ብለዋል። ይህን ለማድረግ ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ተቋሙ በአሁኑ ወቅት  የሀገሪቱን 30 በመቶ የምርጥ ዘር አቅርቦት ፍላጎት እየሸፈነ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አሥፈጻሚዋ የሺመቤት ነጋሽ ጠቁመዋል። እንደየ አካባቢው ሥነ ምህዳር (አግሮ ኢኮሎጂ) በ22 የሰብል ዓይነት እና 90 ዝርያዎችን እያባዛ  ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ መሆኑንም ነው ያብራሩት።

በየዓመቱ እስከ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ (ዳፕ እና ዩሪያ) በሀገሪቱ ለሚገኙ ክልሎች ለማቅረብ አቅዶ እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል። እስካሁንም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ግዥ ተፈጽሞ ለክልሎች የማሰራጨት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

ለአማራ ክልል የሚያስፈልገውን ስምንት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ሲሆን እስካሁንም ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታሉ ወደ ክልሉ ገብቶ በመሰራጨት ላይ ነው። 600 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደብ ላይ መድረሱንም ተናግረዋል።

እንደ ኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ የሺመቤት ነጋሽ ገለጻ ከአፈር ማዳበሪያ ባሻገር በየዓመቱ 460 ሺህ ኩንታል የክልሎችን ሥነ-ምህዳር ያገናዘበ ምርጥ ዘር እየቀረበ ነው። ለአማራ ክልልም እንደ አኩሪ አተር፣ ሩዝ፣ በቆሎ እና ጤፍ ያሉ ምርጥ ዘሮች በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሮች እንዲደርሱ ተደርጓል::

ዋና ሥራ አሥፈጻሚዋ እንዳብራሩት ኮርፖሬሽኑ ዘርፉን ለማዘመን የሚያስችለውን ግብዓት በስፋት ተደራሽ የማድረግ ሥራ በትኩረት እየሠራ ነው።  ግብርናውን ከሞፈር እና ቀንበር ለማላቀቅ የሚደረገው የሜካናይዜሽን ሽግግር የዘርፉ ማዕከል መሆኑንም አንስተዋል። ይህን ሂደት ዘላቂ ለማድረግም ኮርፖሬሽኑ በሦስት ዋና ዋና ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል።

እነዚህም በጥገና ምክንያት የቆሙ ትራክተሮችን እና መሰል መሳሪያዎችን የጥገና ማዕከላትን በማደራጀት እና የመለዋወጫ እቃዎችን በማቅረብ አገልግሎቱን ማስቀጠል፣  በሀገር ውስጥ የመገጣጠም ሥራ እስከሚጀመር ድረስ ጥራታቸውን የጠበቁ፣ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ የተለያዩ የእርሻ መሳሪያዎችን የደንበኛውን ፍላጎት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ከውጭ በማስገባት ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም  የሜካናይዜሽን መሣሪያዎችን በኪራይ በማቅረብ ከመሬት ዝግጅት እስከ ምርት ስብሰባ ያለውን ሂደት ማዘመን  እንደሆነ  ዋና ሥራ አሥፈጻሚዋ አስረድተዋል።

መረጃ

የግብርና ግብዓቶች (Agricultural Inputs) ማለት በግብርናው ዘርፍ ምርትን እና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ጥራትን ለመጠበቅ እና የግብርና ሥራን ለማቀላጠፍ የምንጠቀምባቸው ቁሳቁሶች፣ ቴክኖሎጂዎች እና አገልግሎቶች ናቸው።

እነዚህም ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ የሰብል ጥበቃ ኬሚካሎች፣ የግብርና መሳሪያዎች እና ማሽነሪዎች፣ የኤክስቴንሽን አገልግሎት እና መሰል ግብዓቶች ተጠቃሽ ናቸው።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የመጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here