ጠባቧ መኖሪያ ቤት

0
40

በፔሩ ሰሜናዊ ግዛት ኦካላማ ከተማ አስፈላጊ መገልገያዎችን አብቃቅቶ የያዘው ስፋቱ 63 ሴንቲ ሜትር የተለካው መኖሪያ ቤት የዓለማችን ጠባቡ ቤት ሊሆን መቻሉን የኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ዘገባ ያስረዳል::

ባለፉት በርካታ ምዕተ ዓመታት ጠባብ ቤቶች መሰራታቸውን ያስነበበው ድረ ገጹ በያዝነው ዘመን የህዝብ ብዛት በመጨመሩ፣ የግንባታ ቦታ በማነሱ ወዘተ. ጠባብ መኖሪያ ቤቶች መስራት አስገዳጅ እየሆነ መምጣቱ ተጠቁሟል- በድረ ገጹ::

በፔሩ ሁዋረል ቀጣና ኦካላማ አውራጃ ኗሪዉ ፋቢዮሞሬኖ የተሠራው የጠባቧ ወይም ቀጭኗ ቤት ግንባታ ንድፍ (ፕላን) “ደስታ የቤት መጠንን መሠረት ያደረገ ሣይሆን ቦታን በአግባቡ መጠቀም ነው” የሚል መሠረታዊ ጭብጥን ለማስተላለፍ ያለመ መሆኑ ነው የተጠቆመው::

በዚሁ መነሻ ሃሣብ ተነድፎ በ63 ሴንቲ ሜትር ስፋት የተሰራችው ባለሶስት ፎቅ መኖሪያ ቤት በደማቅ ቀለሟ እና ጠባብ ጠርዞችዋ በሺህ ለሚቆጠሩ ጐብኚዎች መስህብ ሆናለች::

ጠባቧ መኖሪያ ቤት ከውጭ ለሚመለከታት ለትርኢት የቀረበች የኪነ ጥበብ ውጤት ብትመስልም  በእውን እንደማንኛውም መኖሪያ ቤት፣ መታጠቢያ ክፍል፣ ማእድ ቤት፣ የመመገቢያ ክፍል፣ መተላለፊያ (ኮሪደር)፣ መኝታ ቤት፣ የጥናት ክፍል፣ የልብስ ማጠቢያ እና ወደ ፎቅ መውጫ መውረጃ ደረጃን አካታ ይዛለች::

በኦካላማ ከተማ ከአደባባይ ፊት ለፊት የተሰራችውን ጠባቧን መኖሪያ ቤት ለመጐብኘት በአንድ ጊዜ ከሁለት ሰው በላይ ማስተናገድ አትችልም- በቦታዋ ጠባብነት:: የቤቷ ባለቤት ፋቢዮ ሞሬኖ ለዓለም አቀፉ የድንቃ ድንቅ መዝጋቢ ድርጅት  “ጦባቧ መኖሪያ ቤት” የሚለውን ማእረግ ለመጐናፀፍ አመልክቶ በመጠባበቅ ላይ መሆኑ በማደማደሚያነት ለንባብ በቅቷል::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here