ከሞት ወደ ሕይወት

0
114

በህንድ ኡታር ኘራዴሽ ግዛት ቤቷ ውስጥ ወድቃ ራሷን የሳተች የ50 ዓመት ሴት ሪፈራል ሆስፒታል  ገብታ ልትነቃ ባለመቻሏ  ህይወቷ ማለፉ የተነገራቸው ቤተሰቦቿ በአምቡላንስ ይዘዋት ወደ መኖሪያ ቤቷ በማምራት ላይ ሳሉ ጐዳና ላይ በደረሰባት መንገጫገጭ ነፍስ ስለመዝራቷ ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል::

ቬኒታ ሹክላ የተሰኘች ሴት በፒልቢሂት ከተማ የካቲት 22 በመኖሪያ ቤቷ ውስጥ በስራ ላይ ሳለች ወድቃ ራሷን በመሳቷ ቤተ ዘመዶቿ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ሆስፒታል ያስገቧታል:: በተደረገላት ምርመራም የደረሰበት ጉዳት ከባድ ሆኖ በመገኘቱ ባርሌ ከተማ ወደሚገኝ ሪፈራል ሆስፒታል ያስገቧታል::

በሪፈራል ሆስፒታሉ በተደረገላት ተከታታይ ምርመራ እና  እገዛ ለውጥ አላገኙም- ሀኪሞቹ:: በመጨረሻም  ከባለቤቷ ጋር ከተወያዩ በኋላ የአንጐሏ የንቃት ደረጃ ሦስት ነጥብ ብቻ እንደነበር ይረዳሉ- የጤነኛ ሰው የንቃት ደረጃ 15 መሆኑን በመገንዘብ:: በዚህም ተስፋ እንደ ሌላት ይነግሩታል:: የሴትዮዋ ቤተሰቦች የቀብር ስነ ስርዓቷን ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ የቬኒታን “አስከሬን” በአምቡላነስ ጭነው መጓዛቸውን ይያያዙታል::

የካቲት 24 ቀን ሃፊዝጋንጅ በተሰኘ ከተማ አቅራቢያ አባጣ ጐርባጣ የበዛው የተጐዳ አውራ ጐዳናን እንዳለፉ ባጋጠማቸው መንገጫገጭ ቪንታ ሹክላ ነቅታ መተንፈስ መጀመሯን ያስተውላሉ- ቤተሰቦችዋ:: ከአንድ ቀን በፊት የት? እንዴት? የቀብር ስነ ስርዓቷ ይፈፀም እያሉ ሲያስላስሉ የነበሩ ቤተሰቦቿ ሴትዮዋ ነቅታ ማውራት ስትጀምር ክስተቱን እንደተአምር ማየታቸውን አስነብቧል- ድረ ገጹ::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here