ያዩ የጫካ ቡና በኦሮሚያ ክልል በኢሉባቡር እና በቡኖ በደሌ መካከል ከአዲስ አበባ 564 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው:: የደኑ ስፋት 167 ሺህ 21 ሄክታር ወይም 1 ሺህ 670 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል::
በተፈጥሯዊ ደኑ ውስጥ ከለማው የቡና ተክል የሚለቀመው የቡና ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂና ተፈላጊነት ያለው ነው:: ቀጣናው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ የሚያገኝ በመሆኑም ጌባ፣ ዶጊ፣ ሳኪ እና ሴሴን የመሳሰሉ ወንዞች ከዚያው ተነስተው ወደየአቅጣጫው ይፈሳሉ::
ተፈጥሯዊ ደኑ በዓለማችን የተመራጩ “ኮፊ አረቢካ” የቡና ዝርያ መገኛ ነው:: ከዚህ ባሻገር የመጥፋት አደጋ ያንዣበበባቸው እፅዋት እና እንስሳት ዝርያዎችም በቀጣናው መገኘታቸው ተጠቁሟል::
በደኑ ውስጥ ከሚገኙ 51 የእንጉዳይ ዝርያዎች 21ዱ ለምግብነት የሚዉሉ መሆናቸው ተረጋግጧል::
በያዩ ተፈጥሯዊ ደን ውስጥ ሀምሌ እና ነሃሴ ከፍተኛ ዝናብ የሚጥልባቸው ወራት ናቸው:: ተፈጥሯዊ ደኑ በቀጣናው የሚገኙ ስድስት ወረዳዎች የተካለለ ነው:: በ2010 እ.አ.አ ያዩ ተፈጥሯዊ ደን ውስጥ ቡና መጠበቂያ በዓለም አቀፍ የአካባቢ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በተፈጥሯዊ ቅርስነት ተመዝግቦ ጥበቃ እንደሚደረግለትም ድረ ገፆች አስነብበዋል::
በደኑ 450 የእፅዋት፣50 የአጥቢ እንስሳት እንዲሁም 20 በየብስ እና በውኃ አካላት ውስጥ የሚኖሩ “አምፊቢያንስ “ዝርያዎች መገኘታቸው ለንባብ በቅቷል::
በያዩ ተፈጥሯዊ የደን ውስጥ ቡና መጠበቂያ ምድረ ገነት የደን መጨፍጨፍ፣ ልቅ ግጦሽ፣ የእሳት ቃጠሎ እና ህገ ወጥ ሰፈራ ለቀጣይነቱ ስጋት መሆናቸውም ተጠቁሟል::
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ያዩ ባዮስፌር፣ ኦሮሚያ ቱሪዝም ዶት ኦርግና ዮኔስኮ ዶት ኦርግ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


