ራስ ደጀን – የስሜን ኩራት

0
325

የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ በ120 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከደባርቅ ከተማ በምሥራቅ አቅጣጫ በ32 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ከባህር ወለል በላይ ከ1900-3926 ሜትር ከፍታ ላይ በ412 ኪሎ ሜትር ሜትር ስኩዌር ስፋት ላይ ያረፈው ስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዓለማችን ካሉት እጅግ አስደናቂና ማራኪ ተፈጥሯዊ የመስህብ ስፍራዎች አንዱ ነዉ፡፡ በአስደማሚ መልካምድራዊ አቀማመጡና በውስጡ በያዘው በርካታ ብዝሃ ህይወት ምክንያት የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስብ ድንቅ ስፍራ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ እንስሳት መኖሪያም ነው፡፡ እንደ ዋልያ አይቤክስ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ የምኒልክ ድኩላ፣ ቀይ ቀበሮ የመሳሰሉት ብርቅዬ እንስሳት ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ከ1ሺህ 200 በላይ የተለያዩ የዕፅዋት ዝርያዎችን አቅፎ ይዟል፡፡ በፓርኩ ውስጥ በርካታ የአዕዋፍ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን ፓርክን መጠለያ ካደረጉት እና ከ200 ከሚበልጡት የአዕዋፍ ዝርያዎች መካከል አምስቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸዉ፡፡

በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት በ1978 ዓ.ም በተመዘገበው በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እምብርት ላይ የኢትዮጵያ ከፍተኛው ጫፍ ይገኛል። ይህ ግዙፍ ተራራ የኢትዮጵያ “ጣሪያ” ተብሎ መጠራቱ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ አህጉርም አሥረኛው ከፍተኛው ተራራ ነው። ለተመልካች የሚሰጠው ስሜት ከተራ የቱሪስት መዳረሻነት በላይ ነው፤ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጽናት የብዝሃ ሕይወት መገኛና የመልክዓ ምድር ድንቅ ተፈጥሮ መገለጫ ነው፤ ራስ ደጀን ተራራ።

ራስ ደጀን ተራራ ከባህር ጠለል በላይ 4ሺህ 533 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ የኢትዮጵያ “ጣሪያ” እየተባለም የሚታወቅ አስገራሚ የተፈጥሮ ትንግርት ነው። የሀገሪቱ የጥንካሬ፣ የጽናትና የተፈጥሮ ውበት ተምሳሌት ነው። ራስ ደጀን ለጎብኚው የሚሰጠው ስሜት ከእይታ ባለፈ፣ ወደ ውስጠ ማንነት የሚጓዝ የነፍስ እርካታ ምንጭ ነው።

“ራስ ደጀን” የተራራው ትክክለኛ መጠሪያው ነው። የታሪክ ተመራማሪዎችና የአካባቢው ሊቃውንት እንደሚስማሙት “ራስ” የሚለው ቃል በተራራማ ስፍራዎች አጠራር ከፍተኛውን ጫፍ ወይም “ራስን” ሲያመለክት፣ “ደጀን” የሚለው ቃል ደግሞ ለጦርም ሆነ ለሌላ አስቸጋሪ ሁኔታ መጠጊያ፣ መመኪያና የጀርባ አጥንት የሚሆንን ኃይል ይገልጻል።

በጥንታዊው አጠራር “ራስ ዳሸን” ተብሎም የሚታወቀው ይህ ተራራ በታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንደ ምሽግ ሆኖ አገልግሏል። በአካባቢው የሚነገሩ ትረካዎች እንደሚጠቁሙት፣ በጦርነት ወቅት የሀገር መከላከያ ኃይሎችና መሪዎች ተራራውን እንደ ስልታዊ ምሽግና የደህንነት “ደጀን” ይጠቀሙበት ነበር። የማይደፈር ተፈጥሯዊ ምሽግ በመሆኑም፣ ወራሪ ኃይሎች ወደዚህ ተራራማ ምድር ለመዝለቅ እጅጉን ይፈሩ ነበር። ከዚህም ባለፈ ተራራው በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ እንደ ትልቅ የጸሎትና የቅድስና ስፍራ የሚታይ ሲሆን “ደጀን”ነቱም ከምድራዊ ጥበቃ አልፎ ሰማያዊ ረድኤት የሚገኝበት ስፍራ ተደርጎ ይቆጠራል።

የተፈጥሮ አቀማመጥና ልዩ ገጽታው

የራስ ደጀን ተራራ አፈጣጠር ከሚሊዮኖች ዓመታት በፊት በነበረ እሳተ ገሞራ ፍንዳታ የተከሰተ እንደሆነ የጂኦሎጂ ጥናቶች ያመለክታሉ። ተራራው ሰፊና ድንጋያማ ጫፎች ያሉት ሲሆን፣ በአካባቢው የሚገኙት ጥልቅ ሸለቆዎችና ገደላማ ስፍራዎች ለተራራው ልዩ ግርማን ሰጥተውታል።

በተራራው ላይ ስንወጣ የምናገኘው የአየር ንብረት ከታችኛው የደጋ ክፍል በእጅጉ የተለየ ነው። ከፍተኛ ቅዝቃዜ፣ ብርቱ ንፋስና አልፎ አልፎ የሚታይ በረዶ የተራራው መለያዎች ናቸው። በንጋት ጊዜ የተራራውን ጫፍ የሚሸፍነው ጉም እና የፀሐይ መውጫው ደማቅ ብርሃን ሲገናኙ የሚፈጥሩት ትዕይንት፣ ተራራውን የወርቅ ዘውድ የደፋ ያሰኘዋል።

የብዝሃ ሕይወትና ብርቅዬ እንስሳት

ራስ ደጀን የሚገኝበት የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በ1978 ዓ.ም በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በተራራው አካባቢ የሚገኙ ብርቅዬና በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ዝርያዎች ናቸው።

ዋሊያ አይቤክስ (Walia Ibex) አንዱ እና ዋነኛው የራስ ደጀን ድንቅ መገለጫ ነው። ራስ ደጀን ሲነሳ ዋሊያን ሳያነሱ ማለፍ አይቻልም። ራስ ደጀን ለዋሊያዎች ዋነኛ መጠለያና መኖሪያ ነው። ይህ ብርቅዬ የዱር ፍየል ዝርያ የሚገኘው በእነዚህ ገደላማ ተራሮች ላይ ብቻ ነው።

ጭላዳ ዝንጀሮ ከራስ ደጀን ቤተሰቦች ሌላኛው ነው። በደረቱ ላይ ባለው ቀይ ምልክት የሚታወቀውና በሣር ተመጋቢነቱ የሚለየውን ይህን ዝንጀሮ፣ በራስ ደጀን አናት ላይ በትላልቅ መንጋዎች ተሰባስቦ ማየት የተለመደ ነው።

በዓለም ላይ ካሉ ቀበሮዎች ሁሉ ብርቅዬ የሆነው የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮ፣ በዚህ ቀዝቃዛማ ከፍታ ላይ ሲዘዋወር ማየት ለጎብኚዎች እንደ ልዩ ዕድል ይቆጠራል።

በተራራው ላይ ከሚበቅሉ ዕፅዋት መካከል እንደ ሻማ ቀጥ ብላ የምትወጣው ጂባራ፣ የመልክዓ ምድሩን ውበት ወደ ሌላ ዓለም ከፍ ታደርገዋለች።

ለቱሪዝም እና ለጎብኝዎች ያለው ፋይዳ

ራስ ደጀን ለጀብዱ ፈላጊዎችና ለተፈጥሮ አፍቃሪዎች የህልም መዳረሻ ነው። ተራራውን ለመውጣት የሚደረገው ጉዞ በራሱ ትልቅ ትምህርትና ተሞክሮ ነው። ጉዞው የሚጀምረው ከደባርቅ ከተማ ሲሆን በእግር የሚደረገው የብዙ ቀናት ጉዞ በሳንቃ በር፣ በጊችና በጨነቅ በኩል አልፎ ራስ ደጀን ይደርሳል።

መንገዱ ፈታኝ ቢሆንም፣ በጉዞው ወቅት የሚታዩት “የስሜን ግንቦች” (The Walls of Simien) የሚባሉት ግዙፍ ገደላማ ተራሮችና በየሸለቆው የሚፈሱት ምንጮች የድካምን ስሜት ያጠፋሉ። የተራራው ጫፍ ላይ ሲደረስ የሚታየው እይታ ወደር የለውም፤ የአማራ ክልል ሰፋፊ መሬቶች ከእግሩ ስር የተነጠፉ ይመስላሉ።

 

 

ተግዳሮቶች እና ጥበቃ

ምንም እንኳን ራስ ደጀን እና የሰሜን ተራሮች ፓርክ ትልቅ ሀብት ቢሆኑም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የተለያዩ ተግዳሮቶች እየገጠሟቸው ይገኛሉ። የሰፈራ መስፋፋት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የመሠረተ ልማት እጥረት በፓርኩ  ከሚስተዋሉ ተግዳሮቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

የአካባቢው ማህበረሰብ ከተራራው እና ከፓርኩ ከሚገኘው የቱሪስት ገቢ ተጠቃሚ በማድረግ፣ የተፈጥሮ ሀብቱን በባለቤትነት እንዲጠብቁ ማድረግ ወሳኝ ተግባር ነው። ራስ ደጀን የኢትዮጵያ ኩራት ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስ በመሆኑ ጥበቃው የሁላችንም ኃላፊነት መሆን አለበት።

በአጭሩ ራስ ደጀን ተራራ የኢትዮጵያ ከፍታ ተምሳሌት፣ የብርቅዬ እንስሳት መጠጊያ እና የተፈጥሮ ድንቅ ጥበብ ማሳያ ነው። ተራራውን መጎብኘት ስለ ሀገራችን ተፈጥሮአዊ ሀብት ያለንን ግንዛቤ ከማሳደጉም በላይ፣ ይህንን ታላቅ ስጦታ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ እንዳለብን ያስታውሰናል።

እንደ ሀገር ራስ ደጀንን በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት በማስተዋወቅ እና አካባቢውን በመጠበቅ፣ ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ ይገባል። ራስ ደጀን ሁልጊዜም በኩራት እንደቆመ ይኖራል፤ እኛም ይህን ግርማ ሞገስ ያለው ተራራ በአካል በመሄድ ልንጎበኘው እና ልንከባከበው ይገባል እንላለን!

ምንጭ፣ የስሜን ተራሮች ፓርክ ፓምፕሌት፣ የአማራ አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ድረ ገፅ፣ እና ሌሎችንም ተጠቅመናል።

አጫጭር እውነታዎች

  • የአፍሪካ ጣሪያ: የኢትዮጵያ ከፍተኛው ተራራ ራስ ዳሽን (4,550 ሜትር) መጓጓዣ በዚህ ሰንሰለታማ ተራራ ውስጥ ነው። ይህ ተራራ በአፍሪካ በአሥረኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ከፍተኛ ቦታ ነው።

 

  • የዩኔስኮ ቅርስ – የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ቡድን በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው የተፈጥሮ ውበትና ብርቅዬ እንስሳት ምክንያት እ.ኤ.አ. በ1978 በዩኔስኮ ከተመዘገቡት መካከል አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል።

 

  • ብርቅዬ እንስሳት- በዓለም ላይ በሌላ ቦታ የማይገኙ (Endemic) ዋልያ አይቤክስ ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ እና የቀይ ቀበሮ መገኛ።

 

  • ኦፊሳዊ አመጣጥ፦ ተራራዎቹ የተፈጠሩት ከሚሊዮን ዓመታት በፊት ከፍተኛ የእርስ በርስ ገሞራ ፍንዳታና ቅድመ ዝግጅት (Erosion) ምክንያት። ይህም አካባቢው ጥልቅ ሸለቆዎችና ገደላማ ቦታዎች እንዲኖሩት አድርጎታል።

 

  • መታሰቢያ ባር (ጂንባር ፏፏቴ)፡- በአፍሪካ ካሉ ረጅም መለያዎች አንዱ ነው።

 

  • የአየር ንብረት- ከፍታው በጨመረ ቁጥር የአየር ሁኔታው በጣም ቀዝቃዛና በረሃማ ሊሆን ይችላል። በተለይ በሐምሌና ነሐሴ ወራት ከፍተኛ ዝናብና ጭጋግ ይስተዋላል።።

አጫጭር እውነታዎች

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here