“ለሰዎች ፍቅር መስጠት ትልቁ  ‘ርካታ ነው”

0
351

በውቢቱ ባህር ዳር ከተማ የቄስ ትምህርት ቤት ፊደል ከመቁጠር ጀምሮ በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) በተለያየ የሥራ ኃላፊነት ላይ እስከመድረስ የተዘረጋው የሽመልስ ከበደ የሕይወት ጉዞ፤ በውጤታማነት፣ በጽናትና ለወገን በመቆርቆር የተሞላ ነው። ሽመልስ ለብዙዎች በጋዜጠኝነትና በአርታኢነት ሙያው የሕዝብን ብሶትና ችግር ነቃሽ ሆኖ ለዓመታት ቢታወቅም ከሙያው አጥር ባሻገር ደግሞ “መስጠት መታደል ነው” በሚለው የሕይወት ፍልስፍናው በብዙዎች ልብ ውስጥ የነገሰ ስም አለው።

ገና በለጋ ዕድሜው በሰባትና ስምንተኛ ክፍል በንባብና በስነ-ጽሁፍ የጀመረው የፈጠራ ዝንባሌው በኋላም ወደ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት አድጎ አሚኮ በክልሉ ቀዳሚ ተቋም እንዲሆን ለማስቻል ሌሊትና ቀን ለሥራው የሰጠው መስዋዕትነት የሚደነቅ ነው። ይሁን እንጂ የሽመልስ ትልቁ ስኬት በሥራ ገበታው ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፤ በሥራ ጫና እና በቤተሰብ ኃላፊነት መካከል ሆኖም እንኳን ከ21 ጊዜ በላይ ደም በመለገስ ያሳየው ቆራጥነት፣ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርና በተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ውስጥ ለዓመታት ያበረከተው የላቀ አመራርና አገልግሎት ሰብአዊነትን በተግባር የገለጸበት ታላቅ አሻራው ነው።

በዚህ ልዩ ቆይታችን፤ ስለ ልጅነት ትዝታዎቹ፣ ስለ ትዳር ሕይወቱና ስለ ሥራው ፈተናዎች እንዲሁም የሰውን ልጅ እንባ ለማበስ ስላደረገው የዘመናት ጉዞ ከአቶ ሽመልስ ከበደ ጋር በበኩር ጋዜጣ ያደረግነውን ቆይታ እንድታነቡ እምጋብዛለን። መልካም ንባብ!!!

ስለ አስተዳደግህና  ትምህርትህ እስኪ አጫውተን?

የተወለድኩትና ያደግኩት በዚህች በውቢቷ ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ነው። ትምህርቴንም ቢሆን ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ የተከታተልኩት እዚሁ ባሕር ዳር ነው። ትምህርት የጀመርሁት በሕጻንነቴ በአካባቢው ባለው የአብነት ትምህርት ቤት ነው፡፡  ከዚያም ወደ መደበኛ ትምህርት ስገባ በትምህርቴ በጣም ጎበዝ ስለነበርኩ ደረጃ አገኝ ነበር፤ ክፍሎችን እየዘለልኩ (Double) የመማር ዕድልም አጋጥሞኛል። ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍልን ፋሲሎ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሬያለሁ።

ወደ ጋዜጠኝነት እንዴት ገባህ?

በጣና ሐይቅ ትምህርት ቤት በነበረኝ ቆይታ በቲያትር ክበብ ውስጥ እሳተፍ ነበር፤ በአጫጭር የስነ-ጽሁፍና የቲያትር ስክሪፕት ዝግጅት መወዳደር ላይም ተሸላሚ መሆን ችያለሁ። እነዚህ ነገሮች ወደ ሙያው  እንድገባ ስለረዱኝ በ1991 ዓ.ም በአሚኮ (የቀድሞው የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት) የሥራ ውድድር ወጥቶ ተወዳድሬ የምዕራብ ጎጃም ዞን ሪፖርተር ሆኜ በማለፌ ወደ ጋዜጠኝነቱ በይፋ ገብቻለሁ።

በአሚኮ ውስጥ ለረጅም ዓመታት በቆየህባቸው ጊዜያት የሥራ ፍቅርህና ቁርጠኝነትህ ምን ይመስል ነበር?

አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ላይ ባለኝ ቆይታ መጀመሪያ በበኩር ጋዜጣ፣ በኋላም በሬዲዮ ክፍል ሰርቻለሁ። ለሥራዬ ያለኝ ፍቅር በጣም ከፍተኛ ስለነበር ጠዋት ገብቼ እስከ ምሽት ድረስ እቆይ ነበር። ምክንያቱም አሚኮ ሁልጊዜ አዳዲስ ዜናዎችን በማቅረብ ከሁሉም ቀዳሚ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ።

በተለይ አዳዲስ ዜናዎችን ለማግኘትና ሌሎች ሳይቀድሙን ለጠዋት ዝግጁ ለማድረግ የጊዜ መስዋዕትነት መከፈል አለበት። በትዳር ህይወቴም ቢሆን “ለቤት ጊዜ ስጥ” የሚሉ ምክሮች ይመጡልኝ ነበር፤ ልክ ነው መሰጠት አለበት። ነገር ግን የተቋሙ ውጤታማ መሆንና የህብረተሰቡን ችግር ነቃሽ መሆን ትልቁ ዓላማዬ ነበር። ተመድቤባቸው በነበሩ ቦታዎች ሁሉ ሳላሰልስ፣ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳልል ለማገልገል ሞክሬያለሁ። ዝም ብሎ ጋዜጠኛ መባል ብቻ ሳይሆን፣ እንደው ለህብረተሰቡ ለውጥም የእውነት እንደ ከልቤ ጥረት አደርግ ነበር።

ሌላው ብዙዎችን የሚያስደንቀው ከሰዎች ጋር ያለህ ግንኙነት ነው። ሰዎችን እንዴት ነው የምታየው?

ልክ ነው ለሰዎች ፍቅር መስጠት ደስ ይለኛል። ፍቅር ስትሰጥ መጀመሪያ የምትረካው አንተ ራስህ ነህ። እኔ በተቻለኝ መጠን ሁሉንም ላለማበላለጥ እሞክራለሁ፤ ቤተ ክርስቲያን ያስተማረችን ያ ስለሆነ። የኢየሱስ ክርስቶስን አርአያነት መከተል የምትችል ከሆነ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ድሃን አልመረጠም፤ ሀብታምን አልመረጠም። ስለዚህ ሁሉንም በእኩልነት ማየት አስፈላጊ ነው። በቢሮዬ ውስጥ ሁሉንም ሠራተኞች እኩል ለማየት እና እኩል ፍቅሬን ለመስጠት እፈልጋለሁ። ሌላው ቀርቶ በበዓላት ወቅት በስልኬ ላይ ያሉትን ሰዎች በሙሉ እየደወለወኩ እንኳን አደረሳችሁ እላለሁ። ይህን የማደርገው ከሰዎች ምላሽ ፈልጌ ሳይሆን፣ ፍቅር መስጠት በራሱ ስለሚያረካኝ ነው። ከሰዎች ምንም ካልጠበቅህ እርካታህ ሙሉ ይሆናል።

ደም በመለገስ ረገድ ትልቅ አርአያ ነህ። ይህን ተግባር እንዴትና መቼ ጀመርከው?

አዎ! ደም መለገስ የጀመርኩት ሚያዝያ  8 ቀን 1988 ዓ.ም ነበር። በወቅቱ በሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪ እያለን እሁድ እሁድ ወደ ፈለገ ህይወት ሆስፒታል ሄደን ህሙማንን እንጠይቅ ነበር። እጃችን ላይ ያለችንን ጥቂት ሳንቲም አጠራቅመን ዘመድ ለሌላቸው ታካሚዎች ሙዝ ገዝተን እንሰጥ ነበር። “እግዚአብሔር ይማራችሁ” ብለህ ስትጠይቃቸው ተስፋ ይሰንቃሉ።

በአጋጣሚ አንድ ቀን አንዲት እናት ለልጃቸው የሚሆን ደም አጥተው ሲጨነቁ አየሁ። በወቅቱ ደም ይሸጥ ነበር፤ እኔ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በነጻ ደሜን ሰጠሁ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ወደ 21 ጊዜ ደም ለግሻለሁ። ምንም እንኳን በመሀል በጤናና በሥራ ጫና ምክንያት ክፍተቶች ቢፈጠሩም፣ መስጠት ትልቅ ርካታ እንዳለው ተረድቻለሁ። አሁን ደግሞ አሚኮ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ደም እንዲለግሱ አርአያ ለመሆንና መንገድ ለማሳየት ጥረት እያደረግሁ ነው።

ከደም ልገሳ በተጨማሪ ማህበራዊ ተሳትፎህና ኃላፊነትህ ምን ይመስላል?

አሁን በአሚኮ ውስጥ ከባልደረቦቼ ጋር በመሆን ገንዘብ እያሰባሰብን አረጋውያንን እንረዳለን። በዚህ መልኩ እያገለገልኩ ነው። በተጨማሪም በባህር ዳር ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ማህበራት ውስጥ፣ ለምሳሌ በድጋፍና ልማት ማህበራት ውስጥ እሳተፋለሁ። ይህ ሁሉ የሚሆነው ከስራ ጎን ለጎን ሲሆን አላማውም በህይወት እስካለን ድረስ ለወገናችን የሚጠቅም አሻራ ጥሎ ማለፍ ነው። መልካም ስራ ስትሰራ የህይወት መስመርህ በደግነት ይሞላል፤ እንቅፋቶችን እግዚአብሔር እየቀደመ ያነሳልሃል።

ደም በመለገስም ሆነ በማስተባበር  ያጋጠመህ ልዩ አጋጣሚ ወይም ርካታ ካለህ ብትነግረን?

አንድ ጊዜ ቢሮአችን ውስጥ ያለች አንዲት ሠራተኛ ደም አስፈልጓት ነበር። ደም የሚለግሳት ሰው በመጥፋቱ እኔ ሄጄ ሰጠሁ። ዛሬም ድረስ ስታየኝ፣ “ደምህን ለግሰህ ያዳንከኝ ወንድሜ ነህ” ትለኛለች። እኔ ግን ይህን የማየው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፤ አንተ ምክንያት ነህ። እርግጥ ነው የእግዚአብሔር ፈቃዱ እንዲሆን ያንተ መልካምነት መጨመር አለበት። የአንዲትን እናት እንባ ማበስ ትልቅ በረከት ነው። ደም ስትሰጥ ህይወት ነው የምትሰጠው፤ ይህን ደግሞ በገንዘብ ልትገዛው አትችልም። ሰዎች የምንሰጠው የለንም ብለው ሊሸማቀቁ አይገባም፤ ደም መለገስ እያንዳንዱ ጤነኛ ሰው ሊያደርገው የሚችለው ታላቅ ስጦታ ነው። ወደ መንፈሳዊነት ስታመጣው ሌላ ሰውን የማዳን ዕድል ማግኘት ታላቅ ጸጋ ነው።

በመጨረሻም ለህብረተሰቡ በተለይም ለወጣቱ ጋዜጠኛ የምትለው ካለ?

ጋዜጠኛ መረጃ አቅራቢ ብቻ ሳይሆን ቀዳሚ የህብረተሰብ ችግር ፈቺ መሆን አለበት። በአሚኮ ውስጥ ያሉ ወጣት ጋዜጠኞች ሮጠው ያልጠገቡ በመሆናቸው በበጎ ተግባር እንዲሳተፉ ማነሳሳት ይገባል። ጋዜጠኛው እናቶች በደም እጥረት ሲሞቱ ያያል፤ ዜናውንም ይሠራል፤ ያነባል። ስለዚህ ለዚህ ችግር መፍትሔ ለመሆን መነሳሳት አለበት። ደም መለገስ ጤነኛ ለሆነ ሰው ምንም ጉዳት የለውም፤ ደቂቃውም ከ30 አይበልጥም። ይልቁንም ለራስ ጤንነት እና ለህሊና ርካታ ይጠቅማል። እኔም ወደፊት ጤናዬ ሲስተካከል ልገሳዬን እቀጥላለሁ፤ ጡረታ ብወጣ እንኳ ደም የሚለግሱ ሰዎችን የማስተባበሩን ሥራ አላቆምም። መስጠት መታደል ነው፤ ለሰዎች ስትሰጥ ነው የምትኖረው። መልካምነት ደግሞ ዋጋው አይጠፋም፤ ነገ ከነገ ወዲያ በህይወትህ ውስጥ በበረከት ተመልሶ ታገኘዋለህ።

ጋዜጠኛ ሽመልስ ስላካፈልኸን ሀሳብ እናመሰግናለን!

እኔም  አመሰግናለሁ!።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here