የፓን አፍሪካኒዝም ምንጭ

0
70

የአምስቱ ዓመታት የኢትዮጵያ እና የጣሊያን ጦርነት በታሪካችን ውስጥ እጅግ አስቸጋሪ፤ የሀገሪቱን የመኖር እና ያለመኖር ህልውና የወሰነ ወቅት ነበር። ጦርነቱ በይፋ የጀመረው በ1928 ዓ.ም የፋሽስት ጣሊያን ጦር መረብ ወንዝን ተሻግሮ ወረራ በፈጸመበት ወቅት ነው:: ይህ ወረራ በወቅቱ የነበረውን ዓለም አቀፍ ሕግ እና የሊግ ኦፍ ኔሽንስ ስምምነቶችን የጣሰ ነበር። በመጀመሪያዎቹ ወራት በሰሜን እና በደቡብ ግንባሮች ከፍተኛ የመደበኛ ጦርነት የተካሄደ ቢሆንም የጠላት ጦር በዘመናዊ የጦር መሣሪያ እና በተከለከለው መርዝ ጋዝ በመታገዙ የኢትዮጵያ መደበኛ ጦር ማፈግፈግ ጀመረ። መጋቢት 22 ቀን 1928 ዓ.ም የተካሄደው የማይጨው ጦርነት የመደበኛው ውጊያ ማብቂያ እና የአምስት ዓመቱ መራራ የአርበኝነት ትግል መጀመሪያ ሆኖ ተመዝግቧል በማለት ጳውሎስ ኞኞ “የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት” በሚለው መጽሐፋቸው ጽፈዋል።

ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ለዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ወደ አውሮፓ ካቀኑ በኋላ ሀገሪቱ ሙሉ በሙሉ በፋሽስት ቁጥጥር ስር የወደቀች ቢመስልም የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን እጁን አልሰጠም። በየክፍለ ሀገሩ የተነሱት አርበኞች የደፈጣ ውጊያን ስልት በመጠቀም ወራሪውን ኃይል ፋታ ነስተውታል። በሸዋ እነ ራስ አበበ አረጋይ እና ደጃዝማች ኃይለ ማርያም ማሞ፣ በጎጃም እነ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ በደቡብ እነ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ እና ራስ ደስታ ዳምጠው ጠላትን ክፉኛ ተፈታትነዋል። በዚህ ወቅት እንደ ጥቁር አንበሳ ያሉ ድርጅቶች ተመስርተው የተቀናጀ ትግል ለማድረግ ሙከራ የተደረገ ሲሆን ጀግኖች አርበኞች የጠላትን የመገናኛ እና የትራንስፖርት መስመሮችን በመቁረጥ የጣሊያንን ወታደራዊ እንቅስቃሴ አዳክመዋል።

በእነዚህ አምስት ዓመታት ውስጥ ፋሽስት ጣሊያን በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመው ግፍ እጅግ አሰቃቂ ነበር። በተለይም በ1929 ዓ.ም የካቲት 12 ቀን በግራዚያኒ ላይ የተሰነዘረውን የግድያ ሙከራ ተከትሎ በአዲስ አበባ የተካሄደው የሦስት ቀናት የንጹሐን ጭፍጨፋ የታሪክ ጥቁር ጠባሳ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፣ የሃይማኖት አባቶች እና ምሁራን ያለ ምንም ጥፋት የተገደሉበት እና አብያተ ክርስቲያናት የተቃጠሉበት ወቅት ነበር። እንደ አቡነ ጴጥሮስ ያሉ መንፈሳዊ መሪዎች ለጠላት አንገዛም በማለታቸው ተረሽነው ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፤ ይህም ለሕዝቡ የትግል ወኔ ተጨማሪ ስንቅ ሆኗል።

ጦርነቱ ማብቂያ ያገኘው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መፈንዳቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ጦር ጋር በመተባበር የመልሶ ማጥቃት እርምጃ በወሰደችበት ወቅት ነው። አርበኞቹ ከውስጥ ጠላትን ሲያዳክሙ፣ ንጉሠ ነገሥቱ ደግሞ በጎረቤት ሀገር ሱዳን በኩል ከነፃነት ኃይሎች ጋር በመሆን ወደ ሀገር ውስጥ ገቡ። በመጨረሻም ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ፋሽስት ጣሊያን ተሸንፎ ከሀገር ሲወጣ፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በጀግኖች አርበኞች ደምና አጥንት ተከብሮ ዳግም ታወጀ። ይህ ድል ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር እንደማትወድቅ ለዓለም ያስመሰከረችበት ታላቅ ክስተት መሆኑን ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት “የኢትዮጵያ አርበኞች” በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸዋል።

በአምስቱ ዓመታት የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት የኢትዮጵያ ሴቶች ከወንዶች እኩል በጦር ግንባር በመሰለፍ፣ በስለላ ተግባር በመሳተፍ እና አርበኞችን በመርዳት የማይተካ ሚና ተጫውተዋል። እነዚህ ጀግኖች ሴቶች “የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች” ተብለው በታሪክ ይጠቀሳሉ። ሸዋረገድ ገድሌ በአርበኝነት ታሪክ ውስጥ ስማቸው ቀድሞ ከሚነሳ ሴቶች መካከል አንዷ ናቸው። በሸዋ ክፍለ ሀገር ለአርበኞች መረጃ በማቀበል፣ መሣሪያ እና ስንቅ በማቅረብ እንዲሁም በከተማ ውስጥ የድብቅ ትግል በማስተባበር የታወቁ ናቸው። የጣሊያን ጦር ስለላው ደርሶበት በቁጥጥር ስር ካዋላቸው በኋላ በጽናት ስቃይን ተቀብለው ታግለዋል። ለኢትዮጵያ ድልና ለንጉሠ ነገሥቱ መመለስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ታላቅ የቁርጥ ቀን አርበኛ ናቸው። ወይዘሮ ልክየለሽ በያን በበኩላቸው በግንባር በመሰለፍ ጠላትን በነፍስ ወከፍ መሣሪያ የተፋለሙ ጀግና ናቸው። በሸዋ እና አካባቢዋ በነበረው ውጊያ ባላቸው የጦር አመራር ብቃት እና በጀግንነታቸው በአርበኞች ዘንድ ከፍተኛ ክብር ነበራቸው። በተለይም በደፈጣ ውጊያዎች ላይ በግንባር ቀደምትነት በመሰለፍ የጣሊያንን ጦር ክፉኛ በመምታት የሚታወቁ የጦር ሜዳ አርበኛ ናቸው።

ልዕልት ፀሐይ ኃይለ ሥላሴ ደግሞ በሕክምናው ዘርፍ የላቀ ሚና ተጫውተዋል። በስደት በነበሩበት ወቅት የነርሲንግ ትምህርት በመማር የቆሰሉ አርበኞች እና ኢትዮጵያን ወገኖቻቸው ሕክምና እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች ዕርዳታ በማሰባሰብ እና የዓለምን ትኩረት ወደ ኢትዮጵያ በመሳብ ረገድ የዲፕሎማሲ እና የሰብአዊነት አርበኛ ሆነው አገልግለዋል። ወይዘሮ ከበደች ሽባባው ሌላዋ በጀግንነታቸው የሚታወቁ አርበኛ ናቸው። ባለቤታቸው ደጃዝማች በየነ መርዕድ በጦር ሜዳ ሲሰው የእሳቸውን ጦር ተረክበው በመምራት ጠላትን በፅናት ተከላክለዋል። ከእነዚህ በተጨማሪም ስማቸው ያልተጠቀሰ በሺዎች የሚቆጠሩ እናቶች እና እህቶች አርበኞችን በመመገብ፣ ቁስለኞችን በማከም፣ ጥይት እና መረጃ በማመላለስ ለነፃነቱ ቀን መምጣት የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል። ሚያዝያ 27 ቀን የነፃነት በዓል ሲከበር የእነዚህ ሴት አርበኞች ጀግንነት ሁልጊዜም በኩራት አብሮ ይነሳል።

ሚያዝያ 27 በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ትልቁን ስፍራ የሚይዝ የሉዓላዊነት እና የፅናት መገለጫ ቀን ነው። ይህ ታሪካዊ ዕለት ከአምስት ዓመታት መራራ የዱር ተጋድሎ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋሽስት ጣሊያንን ወራሪ ኃይልን ድል አድርጎ ነፃነቱን በይፋ ያወጀበት ብሔራዊ በዓል ነው። በ1933 ዓ.ም በዚህ ዕለት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በስደት ከቆዩባት እንግሊዝ ሀገር ተመልሰው በአርበኞች ታጅበው አዲስ አበባ በመግባት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በታላቅ ኩራት መልሰው ሰቅለዋል። ይህ አጋጣሚ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ሕዝብ ትልቅ የድል ብስራት ነበር።

ይህ ቀን ከድል በዓልነቱ ባሻገር ከፍተኛ የታሪክ ጠባሳን እና የሰማዕታትን መስዋዕትነት አብሮ ይዘክራል። በ1929 ዓ.ም የካቲት 12 ቀን በግራዚያኒ ላይ ከተሰነዘረው የግድያ ሙከራ በኋላ ፋሽስቶች በአዲስ አበባና አካባቢዋ በንጹሐን ዜጎች ላይ የፈጸሙት ጭፍጨፋ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ጥልቅ ቁስል ጥሎ አልፏል። ሚያዝያ 27 እነዚህን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰማዕታት የምናስብበት እና ለነፃነት የተከፈለውን ደም የምናስታውስበት ቀን ነው። በየዓመቱ በስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማዕታት ሐውልት ፊት ለፊት የሚከናወነው ስነ-ስርዓትም ይህንኑ የታሪክ እውነት ለትውልድ ለማስተላለፍ ያለመ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሚያዝያ 27 የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። በወቅቱ ብዙ የአፍሪካ እና የእስያ ሀገራት በቅኝ ግዛት ስር በነበሩበት ወቅት የኢትዮጵያ ድል ለሌሎች ጭቁን ሕዝቦች የነፃነት ችቦ ሆኖ አገልግሏል። ኢትዮጵያ በራሷ ጀግኖች እና በብሪታንያ ጦር ድጋፍ ወራሪውን ኃይል አስወጥታ ነፃነቷን ማስጠበቋ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መወለድ እና መጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ይህም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አሁኑ የአፍሪካ ሕብረት) ምስረታ መሪ ተዋናይ እንድትሆን መንገድ የከፈተ ክስተት ነው። በአሁኑ ወቅት ሚያዝያ 27 ሲከበር ትልቁ ትኩረት ለወጣቱ ትውልድ የሀገር ፍቅርን እና የአንድነትን ትርጉም ማስተማር ነው።

 

 

ሳምንቱ በታሪክ

በጣሊያን ላይ ድል

ደጃዝማች በላይ ዘለቀ በደብረ ማርቆስ እና በአባይ በረሃዎች ከወራሪው ጣሊያን ጋር ተዋግተዋል። ጣሊያኖች በላይን ለመያዝ ወይም ለመግደል ከፍተኛ ጦር እና አውሮፕላኖችን በተደጋጋሚ ቢያሰማሩም እሱ ግን በመልክዓ ምድራዊ እውቀቱ እና በደፈጣ ውጊያ ስልቱ ሁልጊዜም ድል አድራጊ ነበር። ጣሊያኖች “የጎጃም አንበሳ” እያሉ የሚጠሩት በላይ ዘለቀ የጠላትን ምሽግ ሰብሮ በመግባት እና መሣሪያዎችን በመማረክ ይታወቃል።

ከድሎቹ ሁሉ እጅግ ጎልቶ የሚታወሰው ሚያዝያ 19 ቀን 1933 ዓ.ም የጎጃም ዋና ከተማ የሆነችውን ደብረ ማርቆስን ከጠላት ነፃ ማውጣቱ ነው። በዚህ ውጊያ ላይ የበላይ ጦር ከእንግሊዝ ጦር ጋር በመቀናጀት የጣሊያንን ምሽግ ሰባብሮ በመግባት ከተማዋን ተቆጣጥሯል። ይህ ድል ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከስደት ተመልሰው በጎጃም በኩል ወደ አዲስ አበባ ለሚያደርጉት ጉዞ መንገድ የከፈተ ታሪካዊ ክስተት ነበር።

በላይ ዘለቀ ከጦር ሜዳ ጀግንነቱ በተጨማሪ ለተከታዮቹ የነበረው ፍቅር እና የሀገር ፍቅር ስሜቱ እጅግ የሚደነቅ ነው። ንጉሠ ነገሥቱ አዲስ አበባ ሲገቡ በላይ ዘለቀ በታላቅ ክብር እና በሺዎች በሚቆጠሩ የታጠቁ አርበኞቹ ታጅቦ ወደ መዲናዋ በመግባት የጀግንነት አቀባበል ተደርጎለታል። ይሁን እንጂ ከነፃነት በኋላ በነበረው የፖለቲካ ሴራ ምክንያት የሕይወቱ ፍፃሜ አሳዛኝ ቢሆንም በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ግን ሁልጊዜም የማይበገር የነፃነት ምልክት ሆኖ ይኖራል።

ምንጭ፡-የግርማ ሰይፉ “በላይ ዘለቀ (አባ ኮስትር)”

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሚያዚያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here