ፈጠራ ሥራዎች የሰውን ልጅ አስተሳሰብና ችሎታ በአዲስ መንገድ በተግባር የሚገልጡ ተግባራት ናቸው – የፈጠራ ሥራዎች። ነገሮችን በአዲስ ዕይታ መመልከት፣ ችግሮችን በልዩ መንገድ መፍታት እና አስተሳሰብን ወደ ተግባር መቀየር ማለት ነው። የፈጠራ ሥራ ሂደቱም ተደጋጋሚ ሙከራን እና መሻሻልን ያካትታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዓለማችን በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኗን የፈጠራ ሥራዎችን ትኩረት አድርጎ የሚሠራው ቴክኖሎጂ ዶት ኦርግ ላይ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። ለዚህ ደግሞ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች በተግባር መገለጥ መሆኑን ነው ያስገነዘበው።
በሀገራችንም በርካቶች ችግር ፈች የፈጠራ ውጤቶችን እያስተዋወቁ ይገኛሉ። ዘርፉን ይበልጥ ለመደገፍ እና የፈጠራ ሥራዎች ችግር ፈችነት እንዲጎለብት ከሚኔስቴር ጀምሮ በተዋረድ ጽ/ቤት ተቋቁሞ እየተሠራ ይገኛል።
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው ወጣት ብሩክ ወንድይፍራው ደግሞ በፈጠራ ሥራ ከሚጠቀሱት መካከል ይጠቀሳል። ወጣቱ በተለይ ከሰሞኑ የብዙኃኑን ቀልብ የገዛ የፈጠራ ሥራውን ማስተዋወቁን ተከትሎ የአድናቆት ርእሰ ጉዳይ ሆኗል። የፈጠራ ሥራው ደግሞ ከወዳደቁ ብረቶች የሠራት መኪና (ተሽከርካሪ) ናት።
ወጣት ብሩክ ከበኩር ጋር ባደረገው ቆይታ እንዳለው የፈጠራ ሥራ ፍላጎት ከልጅነቱ ጀምሮ የመጣ ነው፤ በተለይ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት “የእጅ ሥራ” የትምህርት አይነት ለፈጠራ ሥራ ከፍተኛ ፍላጎት አሳድሮበታል:: በወቅቱም የወዳደቁ ብረቶችን እና ሽቦዎችን በመሰብሰብ አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርግ ነበር:: ይህ ተደጋጋሚ ሙከራ እና የፈጠራ ሥራ እያደገ መጥቶ በአሁኑ ወቅት በተግባር መገለጥ መጀመሩን ነው የነገረን::
በመደበኛ የትምህርት ጊዜያት የሚገኘው ዕውቀት በአብዛኛው ንድፈ ሐሳባዊ (Theoretical) ነው፤ እንደየ ትምህርት ዓይነቱ የሚቋቋሙት የቤተ ሙከራ ክፍሎች ደግሞ የክፍል ውስጡን ንድፈ ሐሳባዊ ዕውቀት ተግባራዊ ለማድረግ ያስችላል::
ወጣት ብሩክ በእሱ የተማሪነት ወቅት የተሻለ የተግባር ትምህርትን አላገኘም:: ይሁን እንጂ አባቱ በባሕር ዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ (Bahir Dar textile) የሚሠራ መሆኑ ለብሩክ መልካም አጋጣሚ ሆነለት:: አባቱ ስለ ፈጠራ ሥራ ግንዛቤ ያለው መሆኑና አብሮት መሥራቱ ለብሩክ ከዚህ ደረጃ ላይ መድረስ አስተዋጽኦው ከፍ ያለ መሆኑን ነግሮናል::
የቤተሰብ ድጋፍ ለሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን የሚናገረው ብሩክ ከአባቱ ጋር የመሥራቱ ተሞክሮ የቴክኒክ ዕውቀቱን እንዳሳደገለትና ችሎታውን እንዲያዳብር መሠረት እንደሆነው አክሏል።
ከሰሞኑ ያስተዋወቃትና አድናቆት የተቸራት የብሩክ የፈጠረ ሥራ ከብረታ ብረት ቅሪቶች የተሠራች ባለ አራት ጎማ ተሽከርካሪ ናት፤ ተሸከርካሪዋ 300 ሲሲ ሞተር፣ ከ400 ኪሎ ግራም በላይ ክብደት ያላት እና ከአሽከርካሪ ውጭ 4 ሰዎችን ማጓጓዝ የምትችል ናት።
ተሸከርካሪዋ ከባጃጅ የተሻለ ፍጥነት እንዳላት በማንሳት በከተማ መጓጓዣ ዘርፍ አማራጭ መሆኗን ጠቁሟል።
ብሩክ እንደተናገረው የፈጠራ ሥራውን (መኪናዋን) ሠርቶ ለማጠናቀቅ 350 ሺህ ያህል ብር ወጪ ተደርጎባታል፤ ይህ ደግሞ በአነስተኛ ሀብት ትልቅ ነገር መፍጠር እንደሚቻል ማሳያ ነው።
የብሩክ የፈጠራ ስራ ሰሞኑን አስተዋውቋት አድናቆት ባስገኘችለት ተሸከርካሪ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ቀደም ብሎ የልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ የሳሙና ማምረቻ እና የኢንዱስትሪ መሣሪያዎችን በመፍጠር ችሎታውን አሳይቷል። በፈጠራ ሥራዎቹም የባለቤትነት መብቱ ተጠብቆ ለአገልግሎት ብቁ አድርጓል:: በዚህም ከብሩክ ተጠቃሚነት ባለፈ ለበርካቶች የሥራ ዕድልን ፈጥሯል::
በኢትዮጵያ ውስጥ የመኪና ማምረትን ማበረታታት እና ከውጭ የሚገቡ መኪናዎችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የብሩክ ራዕይ ነው። በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መኪናዎችን በማምረት ከነዳጅ ጋር የሚገጥምን ችግር ከመፍታት ባለፈ ከአየር ብክለት ነጻ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እንደሚሠራም ነው የተናገረው።
ከዚህ በተጨማሪም የብሩክ ዕቅድ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነት ማሰደግ እና የአርሶአደሩን ድካም መቀነስ ነው::በዚህም፤ መፈልፈያ ማሽን፣ ትራክተር፣ የጭነት መኪና እና ሌሎች የግብርና መሣሪያዎችን ማምረት የወደፊት እቅዱ መሆኑን ተናግሯል። ይህ በኢትዮጵያ ያለውን የግብርና ዘርፍ በቀጥታ ሊያገዝ ይችላል፤ የምርት ብዛትን ያሳድጋል፣ የእርሻ ስራን ያቀላጥፋል እና የገበሬዎችን ጫና ይቀንሳል።
በዘርፉ በርካታ ወጣቶች መሰል የፈጠራ ሥራዎችን እያስተዋወቁ ይገኛሉ፤ የብሩክ እና መሰሎቹ ጥረት ከተደገፈ ደግሞ ራዕዩ ዕውን መሆኑ አይቀርም:: ይህ ደግሞ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ያበረክታል።
ነገር ግን ይህ ሁሉ በግል ጥረት ብቻ ሊቀጥል አይችልም። የፈጠራ ስራ የሚፈልገው ከፍተኛ ድጋፍ ነው -የፋይናንስ እገዛ፣ የመስሪያ ቦታ፣ የቴክኖሎጂ ማዕከላት እና የገበያ እድሎች እንዲመቻቹለት ጠይቋል።
ስለዚህ የሚመለከተው የመንግስት አካል እና የግል ዘርፍ ኢንቨስት በማድረግ እና ህብረተሰቡ የበኩልን ድርሻ በመደገፍ እንደዚህ ያሉ ፈጣሪዎችን ሊያበረታቱ ይገባል።
በአጠቃላይ የብሩክ ታሪክ አንድ የግለሰብ የተሳካ የፈጠራ ታሪክ ብቻ አይደለም፤ ሀገር የሚያሻግር አቅም ያለው እድል ነው። በተገቢው ድጋፍ ከተጠናከረ ኢትዮጵያን ከሸማችነት ወደ አምራችነት የሚዘውሩ ኃይሎች ሊሆኑ ይችላሉ::
(ሰናይት በየነ)
በኲር የሚያዚያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


