ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት እውን እንዲሆን የግብርናው ዘርፍ ጉልህ ሚና እንዳለው ይታወቃል። በመሆኑም በዘርፉ ያለውን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እና ለማዘመን ይቻል ዘንድ ለመኸር እርሻ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችና የግብርና ቴክኖሎጅ አቅርቦት ቁልፍ ሚና አለው፡፡ ይህ እንዲሳካ ደግሞ ለአርሶ አደሩ በወቅቱና በፍጥነት እንዲደርሰው የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
የመኸር እርሻ በኢትዮጵያ ግብርና ውስጥ ከፍተኛ ምርት የሚገኝበት ወቅት ሲሆን በአብዛኛው የሃገሪቱ ሰብል የሚመረትበትና የሚሰበሰብበት የእርሻ ወቅት በመሆኑ ከፍተኛ የምርት ድርሻ የሚገኝበት የግብርና ነው። በመሆኑም ይህን ወሳኝ ወቅት ለተገቢው ምርታማነት ለማብቃት ይቻል ዘንድ የግብርና ግብአቶች በወቅቱ እና በአግባቡ ወደ አርሶ አደሩ አካባቢወች እንዲደርሱ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል።
የመኸር እርሻ የዋናውን የክረምት ዝናብ ተጠቅሞ የሚከናወን በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ ምርትና ምርታማነትን በማከናወን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በማስቻል እና የሚሰበሰበው ከፍተኛ የምርት መጠንም ለቤተሰብ ፍጆታ እና ለገበያ ቀጥተኛ አስተዋጾ እንዲያበርክት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው፡፡
በመኸር እርሻ በሚኖረው ሰፊ የግብርና ስራም የምርት ብዛት ላይ ብቻ ላይ ትኩረት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ጥራትንም ታሳቢ ያደረገ ምርት እንዲገኝ አስፈላጊ የሆኑ ግብኣቶች ማለትም የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ማዳበሪዎች፣ ምርጥ ዘርን እና አስፈላጊ የሆኑ ቴክኖሎጅዎች በወቅቱ መቅረብ አለባቸው።
ለምርታማነት አስፈላጊ ከሆኑት ግብኣቶች መካከል የአፈር ማዳበሪያ አንዱ እና ዋነኛው በመሆኑ ለመጭው የመኸር እርሻ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ተገዝቶና ተጓጉዞ ወደየአርሶአደሩ ቀዬ መድረስ አለበት። የግብርና ግብኣትንና የተሻሻሉ አሰራሮችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ተግባር የግብርናው ዘርፍ እና የባለሙያዎች ግዴታ ብቻ ባለመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ትብብራቸውን አጠናክረው ሊተገብሩት ይገባል።
የግብርና ባለሙያወችም ከሌሎች ወቅቶች በበለጠ እና በተለየ ሁኔታ ለመኸር እርሻ ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ እና ልዩ ትኩረት በመስጠት ዘርፉን በመደገፍ፣ ግብአቶች እንዲቀርቡ በመከታተል እና አርሶአደሩ በወቅቱ መስራት የሚገባውን ስራ እንዲያከናውን በአርሶ አደሩ ማሳ በመገኘት ሙያዊ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ሙያዊ ሃላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል።
ለክልሉ ኢኮኖሚ ትልቁን ድርሻ ለሚወስደው የግብርናው የሚጠበቅበትን ውጤት እንዲያመጣ ዘርፉን መደገፍ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ ያደርገዋል፡፡ ምርታማነትን በማሳደግም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ከተረጅነት መውጣትም ለነገ የማይባል የዛሬ ተግባር ሊሆን ግድ ይላል። ለዚህም ለመኸር እርሻ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች ከወዲሁ መጀመር እና መጠናቀቅ የሚገባቸው በመሆኑ በተለይም የማሳ ዝግጅትን፣ የግብአት አቅርቦትን የማዳበሪያ እና ምርጥ ዘርን ወደ አርሶአደሩ የማቅረብ ስራ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።
በአማራ ክልል በ2018/19 የመኸር ምርት ወቅት የሚያስፈልግ ስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ መታቀዱንና ከዚህ ውስጥም 46 በመቶ ያህሉ ወደ ክልሉ በመጓጓዝ ላይ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ከሰሞኑ አስታውቀዋል። አርሶአደሮችም በሰው ሰራሽ ማዳበሪ ብቻ ጥገኛ ከመሆን ተሻግረው የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማምረት ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ እና ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል።
በኲር የሚያዚያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


