ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ታሪክ ውስጥ እጅግ የተለየች ዕለት ናት። ምክንያቱም ዐጼ ኃይለሥላሴ በጠላት ወታደሮች የሚመሯት ሀገር ተወርራ የሚያደርጉት ቢያጡ ከሀገር ወጥተው ወደ ባዕድ ሀገር ተሰደዱ፤ ከአምስት ዓመታት ድል ድል ተገኘ፡፡ ንጉሱ ወደ ሀገ ራቸው በመምጣት የጠላትን ሰንደቅ ዓላማ አውርደው የሀገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ አውለበለቡ፤ ከዚያም ለሀገራቸው ሕዝብ ንግግር ያደረገባት ቀን በመሆኗ።
ኢጣሊያ በ1888 ዓ.ም አድዋ ላይ በግማሽ ቀን ጦርነት የውርደት ማቅ መከናነቧ ሲቆጫት፤ ሲያንገበግባት ኖሮ ከ40 ዓመታት በኋላ በ1929 ዓ.ም ቂሟን ለመወጣት ኢትዮጵያን ወረረች። ኢትዮጵያ ደግሞ ገና የሽግግር ወቅት ላይ የነበረች በመሆኑ የተደራጀ መንግሥት እና ጦር አልነበራትም። ፋሽስት ኢጣሊያ ደግሞ አሉ የተባሉ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን መርዝ ከሚተፉ አውሮፕላኖች ጋር ይዛ ኢትዮጵያን ወረረች።
ወረራው የተደራጀ ስለነበር በቀላሉ ሊቀለበስ አልቻለም። ስለዚህ ንጉሠ ነገስቱ እዚሁ ሆነው የከፉ ነገር ከሚመጣ ወደ ውጭ ወጥተው መታገልን የዘመኑ ሹማምንቶች እንደ አማራጭ የመከሯቸው። እናም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከመንበረ ሥልጣናቸው ተነስተው ኢትዮጵያን ለቅቀው ወደ እንግሊዝ ተሰደዱ።
የታሪክ ፀሐፊው አንድሪው ሂለተን “The Ethiopian Patriots Forgotten Voices of the Italo-Abyssinian war 1935-41” በተሰኘው መጽሐፉ ላይ በዚህ ጦርነት ከወንዶቹ ባልተናነሰ የሴቶችን ተጋድሎ ተርኳል፡፡
ደራሲው አርበኛ ዓለሚቱ መኮንን እና ዘነበች ወልደየስ የተባሉ የ80 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አዛውንቶችን በቃለ መጠይቅ ጽሑፉ ላይ ለምስክርነት አቅርቧል። አርበኛ ዓለሚቱ መኮንን በወረራው ጊዜ ምንም እንኳን የ15 ዓመት ታዳጊ ቢሆኑም ብዙ ነገር የሚያውቁ እና የተገነዘቡ ሴት እንደ ነበሩ የታሪክ ፀሐፊው በመጽሐፉ አስፍሯል።
በዚያ ወቅት “የ15 ዓመት ዕድሜ ያለው ማንኛውም ወንድም ሆነ ሴት ሀገሩን ከጠላት ይጠብቃል ተብሎ ስለሚገመት እኔም ቤተሰቦቼ ገና የአስር ዓመት ልጅ እያለሁ ስለሀገር ፍቅር ግንዛቤ ፈጥረውልኛል፡፡ አያቴ በዓድዋ ጦርነት፣ አባቴ እና ወንድሞቼ በጣሊያን ወረራ ጊዜ በቀደምትነት በሠለጠነ መሣሪያ ሳይሆን ባላቸው የቆዬ ጠብመንጃ ፉቺሌ (Fucill) ፣በዚያን ጊዜ ይታወቅ በነበረው ናስ ማስር( Nas Masr)፣ ስናድር እና ውጅግራ በመያዝ ነበር ከጠላት ጋር ግብ ግብ የሚገጥሙት:: ሕይወታቸውን እና ንብረታቸውንም ለሀገራቸው መሰዋዕትነት ከፍለዋል” በማለት ነበር እርሳቸውም የነሱን መርህ በመከተል የውጭ ጠላት ሀገራቸውን ሲወራት በግንባር እና በደጀንነት መሳተፋቸውን የተናገሩት::
አርበኛ ዓለሚቱ መኮንን ወንድማቸው በጠላት እጅ ወድቆ በጥይት ተደብድቦ ከመገደሉ ባለፈ ጥርሶቹን አውልቀው አስከሬኑን ከሦስት ቀን በኋላ ገደል ውስጥ ጥለውት ማግኘታቸው ደግሞ እንደ ጦር ሕግ ቢሆን ኖሮ ይህን የፈጸመ አካል ተይዞ ለፍርድ ይቅርብ ነበር እንጂ እንደ እንስሳ የትም አይጣልም ነበር!” በማለት በቁጭት ወደ ትግል እንደ ገቡ ደራሲው በመጽሐፉ አስፍሯል፡፡
ከወንድማቸው አሰቃቂ ግድያ ጋር የ17 ቤተሰቦቻቸው እልቂት ተዳምሮ ሁሉን ነገር ትተው ወደ በረሀ በመግባት ትግላቸውን ጀመሩ፡፡ አርበኛዋ በቃለ ምልልሱ ወቅት እንደተናገሩት ከቤጌምድር ውስጥ ወንዶ ገጠም ተብላ ከምትጠራው ቦታ ጣሊያኖች በግራ እና በቀኝ ጦራቸውን አስፍረውባታል:: በዚች ስፍራ የአርበኞችን ጦር የሚመሩት ግራዝማች ተድላ እና ግራዝማች ገብሬም በጠላት ተገደሉ፡፡ በወቅቱ አርበኛ ዓለሚቱ የሚሳተፉበት ጦር በጠላት የኀይል ብልጫ ለመበታተን ተገደደ፤ እሳቸው ግን ከሌሎች አርበኞች ጋር በመቀላቀል ትግሉን ቀጠሉ።
“በዚያን ጊዜ ሌላው ሳልጠቅሰው ማለፍ የማልፈልገው የሬዲዮ መገናኛ ባለመኖሩ ከሌሎች ራቅ ካሉ አርበኞች ጋር የደብዳቤ ልውውጥ እናደርግ የነበረው በእንጨት ዱላ (መቃ) ውስጥ መልክቱን በመክተት ማንም በማይጠረጥረው መንገድ ነበር። እንዲሁም የአንድ አካባቢ አርበኛ ከሌላው ጋር በጠላት ላይ ሊደረግ የሚገባውን እንነጋገር ነበር። በዚህም የጦር መሳሪያ እና ሌሎችንም ርዳታዎች እንለዋወጥ ነበር። ከጎንደር ወደ ጎጃም ጥጥ ተልኮ ለአርበኞች ልብስ ይሠራ ነበር። ሕዝቡም ውኃ ብንጠይቅ ወተት ሰጥቶ በሚያስፈልገው ሁሉ እንክብካቤ እድርጎልናል።” በማለት አርበኛ ዓለሚቱ በወቅቱ ብሔር፣ ሃይማኖት…ሳይገድባቸው ለሀገራቸው ሰላም ካለልዩነት ይታገሉ እንደ ነበር መሰክረዋል::
ከንጉሡ በማንኛውም ጊዜ የማበረታቻ መልዕክት በሰውም ይሁን በደብዳቤ ለአርበኛው ይደርሰው ነበር። በመጨረሻም ወደ ድል በሚቃረቡበት ወቅት ከእንግሊዝ ጦር ጋር ሲመለሱ የጣሊያን ፋሽሽት ጦር ከውጭ የጦር ኀይል መምጣቱን ሲረዳ በጣና ኃይቅ ውስጥ ብዛት ያለው ወርቅና ብር እንዲሁም የሰዎችን አስከሬን በደብረ ታቦር፣ በጢስ ዓባይ እንዲሁም በለሎች ስፍራዎች ጥሎ መሸሹን ገልፀዋል::
“እስካሁን ያላወቅነው የተገኘው አፅም ሁኔታ ነው…የተገኘው አፅም በጨካኙ ፋሽሽት የተጨፈጨፉ ሴቶችም ጭምር እንደሆኑ ነው። በመጨረሻም ሁላችንም ታሪክ ሠራን! ምንም እንኳን የሕይወትን አስከፊ ገፅታ እንድናይ ብንገደድም በምንም አይነት ምክንያት ሀገራችንን በባእድ (በጠላት) እጅ አሳልፎ ሰጥቶ በነጭ መመራትና መገዛትን አለመፈለግ ነበር። ይህን በማድረጋችን ደግሞ ኩራት ይሰማናል::
“በአሁኑ ጊዜ ሁሉም በሕይወት ባይኖሩም ያለነውም በዕድሜ ገፋ በማለታችን የእለት ከእለት እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ ባንችልም ተስፋችንና ምኞታችን ለአዲሱ ትውልድ በአደራ እንገልጻለን፤ ሀገራችን ኢትዮጵያን ሁልጊዜም ከጠላት ነፃ አድርጋችሁ እንድትጠብቋት! እኛ ለእናንተ ውድ ሀገራችንን ያስረከብናት ተርበን፣ ተዋርደን፣ ተገድለን፣ በቆዳ በሽታ ተለክፈን… ለጠላት አንሸነፍም! በማለት ስለሆነ እናንተም ይህንን መጠበቅ እንዳለባችሁ አደራም እላለሁ! ሌላ እንዳትረሱ የምለው እኛ ኢትዮጵያን የራሳችን የሆነውን ለሌላው አንሰጥም፤ የሌሎችንም አንፈልግም!”በማለት በቃለ ምልልሱ ወቅት ለተተኪው ትውልድ ያስተላለፉትን መልእክት ፀሐፊው በመጽሐፉ አስፍሮታል::
ሌላዋ ሴት አርበኛ ዘነበች ወልደየስ ይባላሉ፤ በቃለ ምልልስ ወቅት የ80 ዓመት አዛውንት ነበሩ። “የሀገር ፍቅር ያደረብኝ ባለቤቴ ከማይጨው ጦርነት ድል አድርገው ከተመለሱ በኋላ ነው። ከዚያም በአምስት ዓመት የጣሊያን ወረራ መሳተፍ የጀመርሁት ታዳጊ እያለሁ ነው:: የውጭ ጠላት በአጭር ጊዜ በአካባቢዬ ቡልጋ ድረስ በመምጣት ቤት፣ ከብት፣ ንብረቱን… በእሳት አወደመ። ይህን የፈፀመን ጠላት ለመዋጋት ወደ ጫካ በመሄድ ከጦሩ ጋር ተቀላቀልሁ።
መጀመሪያ በአርበኝነት ያገለገልሁት ቀኛዝማች ልክየለህ በሚመሩት ጦር ስር በኋላም ከራስ አበበ አረጋይ ጋር ነበር። የመዋጋት ልምድ ባይኖረኝም የወገን ጦር በሠጠን ስልጠና በመታገዝ ጠላት ሀገሬን እንዳይወር በብርቱ ታግያለሁ::
“አብዛኞቹ ሴት አርበኞች እንደኔው ነበሩ። በወቅቱ ብዙም የጦር መሳሪያ አልነበረንም፤ መሳሪያ ያገኘነው ካለው ላይ በመግዛት ነበር:: ይህ ትግል ይካሄድ የነበረው ደግሞ በውስጥ አርበኞች አማካኝነት ነበር” በማለት ሀገርን በውጭ ጠላት ላለማስደፈር ያደረጉትን ትግል ከጅማሮው አንስተው ተናግረዋል::
መንግሥት የነበረው መሣሪያ የተከፋፈለው በከተማው ላሉት ተፋላሚዎች ነበር። በየጊዜው በሚማርኩት ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እየታገዙ ለመዋጋት መቻላቸውን ተናግረዋል። ትግሉ የሚደረገው ደግሞ አንድ ቦታ ሳይሆን ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ መሆኑ ጥንካሬ ፈጥሮላቸዋል::
በአጠቃላይ የሀገራችንን ክብር ለማዋረድ ለመጣ የውጭ ጠላት በርካታ ሴቶች በግንባር ከመፋለም ጀምሮ በጀግንነት ጉልህ ሚና ማበርከታቸውን የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ዘክረዋቸዋል፡፡
በመጨረሻ ንጉሱ አፄ ኃይለስላሴም ወደ ሀገራቸው ሲገቡ ባደረጉት ንግግር “የሰማይ መላዕክ የምድር ሠራዊት ሊያስቡት እና ሊያውቁት ይቻላቸው ባልነበረ፤ በዚህ በዛሬ ቀን ቸሩ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ለመገኘት ስላበቃኝ በሰው አፍ የሚነገር ምስጋና የሚበቃ አይደለም። ከማናቸውም አስቀድሞ ለሁላችሁ ልነግራችሁ እና ልትረዱት የምፈልገው ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ ያዲስ ታሪክ ዘመን መክፈቻ መሆኑን ነው። በዚህም በአዲስ ዘመን ሁላችን መፈፀም ያለብን አዲስ ሥራ ይጀመራል”በማለት ነበር፡፡
ማናት
በአምስት ዓመቱ የፋሺስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ ለሀገራችን አኩሪ ገድል በመፈፀም ለነፃነታቸው ዋጋ በመክፈል ስማቸው ከሚነሱ ሴቶች ሸዋረገድ ገድሌ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በ1878 ዓ.ም ተወልደው በጥቅምት 22 ቀን 1942 ዓ.ም ላረፉት ሸዋረገድ ገድሌ ስለጀግንነታቸው ሕዝቡ በግጥም አወድሷቸዋል፡፡ የምታስፎክር ሰንጋ ገለሌ
በጦር መካከል ሳይሆኑ አያሌ
በጥይት ገዳይ ነጭ ብርገድሌ
የሴት ጀግና ናት ሸዋረገድ ገድሌ፡፡
እናንት ወጥ ቤቶች በርበሬ ቀንጥሱ
እናንት ሥጋ ቤቶች ሰንጋውን ምረጡ
ሸዋረገድ ገድሌ ለገና ሲመጡ፡፡
ቤተሰቧ ሰፊ ገናና ጥምቀት
ሸዋረገድ ገድሌ እንደምን ትሙት፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የሚያዚያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


