አረንጓዴ አሻራ ሕይዎት ሲዘራ!

0
100

የደን ልማት የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተፅዕኖን ለመከላከል፣ ለመድኃኒት መቀመሚያ፣ ለዱር እንስሳት መጠለያ፣ ለቤት ግንባታ፣ ለማገዶ፣ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እና ለምነቱን ለመጨመር፣ ለውጭ ምንዛሬ ማስገኛ፣ የደረቁ ምንጮች እንዲፈልቁ እና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታን ያስገኛል። ለዚህም ነው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተካሄደ ባለው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በደን ልማቱ መነቃቃት እየታየ ያለው።

በኵር ጋዜጣም በመጭው ክረምት ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ቅድመ ዝግጅቱ እንዴት እንደሆነ  አርሶ አደሮችን እና የዘርፉን ባለሙያዎች አነጋግራለች። በአማራ ክልል በየአካባቢው የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በስልክ በነበረን ቆይታ መረዳት ችለናል።

ለአብነትም በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ሦስቱ ጀበላ ቀበሌ በግብርና ሥራ የሚተዳደሩት አርሶ አደሩ ቢተው አንጀቴ “አትክልት ማልማት  ሕይወትን ማስቀጠል ነው” ይላሉ። ቀደም ሲል በጎርፍ ምክንያት ከጥቅም ውጭ ሆኖ የቆየውን መሬታቸውን የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞችን በማልማት ዛሬ ላይ ጥቅም አስገኝቶላቸዋል። መሬታቸውንም ከጎርፍ መሸርሸር አድኖላቸዋል።

አርሶ አደሩ በዚህ ዓመት የአፈሉትን የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኝ እየተንከባከቡ ናቸው:: ከዚህ ጎን ለጎን ዘንድሮ የሚተክሉት ችግኝ  ቦታ እያፀዱ እና ጉድጓድ እያዘጋጁም ነው። በመጭው ክረምት ጌሾ፣ ወይራ፣ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝ እና ሌሎች አትክልት እና ፍራፍሬዎችን ለመትከል ተዘጋጅተዋል።

ሌላዋ የደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦከምከም ወረዳ ጣራገዳም ቀበሌ ነዋሪዋ አርሶ አደር ፈጠነች ጌጡ ለበኵር ጋዜጣ በስልክ እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት በጓሯቸው እና በእርሻ ማሳቸው ድንበር የተከሉትን ችግኝ እየተንከባከቡ ነው። አትክልት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የጠቀሱት አርሶ አደር ፈጠነች፤ ለአብነትም የአፈር ለምነቱን በማስጠበቅ እና የግብርና ምርታማነትን በተጨባጭ እንዲጨምር አይተኬ ሚና እንዳለው አረጋግጠዋል። አሁን ላይ የመኸር እርሻን ከማከናወን ባሻገር ችግኝ የሚተከልበትን ቦታ በመለየት ላይ ናቸው።

በብሔረሰብ አሥተዳድሩ የአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የሀገር ምጣኔ ሀብትን የሚያሳድገው የአረንጓዴ አሻራ ቅድመ ዝግጅት እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል። በየዓመቱ ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚሆኑ  የተለያዩ ዝርያ ያላቸው የአፈር መሸርሸርን እና የአካባቢ አየር ንብረት ሚዛንን የሚጠብቁ  የደን ችግኞች በጣቢያው ይዘጋጃሉ።  ቡና፣ አቮካዶ፣ ማንጎ እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በስፋት በማፋላት ለአርሶ አደሩ እንደሚሰራጩ ነው የተመላከተው።

የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት  የተፈጥሮ ሀብት ቡድን መሪ አቶ ዓለማየሁ አይናለም ለበኵር ጋዜጣ በስልክ እንደተናገሩት ለመጭው አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በ183 ችግኝ ጣቢያዎች ከሰባት ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለተከላ ተዘጋጅቷል። ዋንዛ፣ ወይራ፣ ግራቪሊያ፣ ጌሾ፣ የአበሻ ፅድ፣ ዲከረንስና የመሳሰሉት ተፈልተዋል። አንድ ሺህ 606 ሄክታር መሬት ለተከላ ተለይቷል። ለዚሁ ተግባርም 931 ሄክታር መሬት በጂፒኤስ ተለይቶ ተዘጋጅቷል።

የተዘጋጁ ችግኞች በማሳ ድንበር፣ በተራቆቱ (በተቦረቦሩ) መሬቶች፣ በወንዞች ዳርቻ፣ በወል መሬት፣ በተቋማት አካባቢ እና በጓሮ ዙሪያ የሚተከሉ መሆናቸውን ቡድን መሪው አብራርተዋል።

እንደ አቶ ዓለማየሁ ማብራሪያ የወረዳ ባለሙያዎች በሰፊው ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ እየፈጠሩ ናቸው። የተፈጥሮ ሀብት መመናመን እና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ በመከላከል የግብርናውን ዘርፍ ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ ብሎም ዘላቂነት ያለው አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተፈጥሮ ሃብትን መጠበቅ እና በዘላቂነት መንከባብ አማራጭ የሌለው ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው::

በተመሳሳይ ለመጭው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ያለው የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ነው። የዞኑ ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ጌታነህ ተክለማርያም እንደተናገሩት ዞኑ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ ደን የተሸፈነ ነው። የተራቆተውን መሬት እንዲያገግም በማድረግ፣ የደን ውጤቶችን ምርታማነት በማሳደግ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጠንካራ የአረንጓዴ ልማት ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

የግብርናውን ምርት እና ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግ ብሎም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን አደጋ በዘላቂነት ለመከላከል የሚያስችል የአረንጓዴ ሽፋንን ለማሳደግ በታቀደ እና በተቀናጀ መንገድ የልማት ሥራዎች በልዩ ትኩረት እንደሚተገበሩም አስረድተዋል:: የዞኑ የደን ሽፋን አሁን ላይ 17 ነጥብ ሦስት የደረሰ ሲሆን በቀጣይ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 18 ነጥብ ሦስት ለማድረስ ታቅዷል።  ዕቅዱን ለማሳካት የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውንም ነው ያስታወቁት። በዞኑ በ14 ሺህ 141 ችግኝ ጣቢያዎች  295 ሺህ ችግኝ ተዘጋጅተዋል። አሁን ላይ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ እየተዘጋጀ ሲሆን ከመተከሉ በፊት አንድ ወር ቀድመው መዘጋጀት እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል። ከ14 ሺህ 900 ሄክታር በላይ የካርታ ልየታም ተሠርቷል።

ቡድን መሪው የባለፈው ዓመት የፅድቀት ምጣኔ 85 በመቶ መድረሱን አረጋግጠዋል። በቀጣይ ጊዚያት የፈሉ ችግኞች በአግባቡ እንዲተከሉ፣ የዞን፣ የወረዳ እና የቀበሌ ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ውይይት መደረጉንም ጠቁመዋል::

ከግንቦት 30/2018 ዓ.ም በፊት የችግኝ ጉድጓድ ተዘጋጅቶ እንዲጠናቀቅ የጋራ ስምምነትም ተደርጓል። ከመትከል ባለፈ ማህበረሰቡ “የኔ ነው!” ብሎ በባለቤትነት ተንከባክቦ የማሳደግ ልምዱ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም የፅድቀት መጠኑ እንዲጨምር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ቡድን መሪው አሳሰበዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃ እና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምሕረት ለበኵር ጋዜጣ እንደተናገሩት ለመጭው የክረምት ወራት ለአረንጓዴ አሻራ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ነው። የሚተከሉ ችግኞች ለጥምር ደን፣ ለደን ልማት፣ ለምግብነት የሚያገለግሉ ፍራፍሬዎች እና ለአካባቢ ጥበቃ የሚውሉ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ያላቸው እንደ ዝግባ፣ ዋንዛ፣ ፅድ፣ ግራር፣ ግራቪሊያ፣ ዲከረስ (ከሰል ለማምረት የሚጠቅም ዛፍ) እና መሰል ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል። በተጨማሪም እንደ ማንጎ፣ አቮካዶ እና ፓፓያን ጨምሮ የቆላ እና የደጋ ፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል ትኩረት ተሰጥቷል።

ባለፉት ዓመታት የደን ሽፋንን ለማሳደግ በተከናወኑ  ተግባራት ተጨባጭ ውጤት መገኘቱንም አቶ እስመለዓለም ገልጸዋል። ባለፉት ሰባት ዓመታት የችግኝ ተከላ ስኬት ከ79 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 82 በመቶ አድጓል። የክልሉ የደን ሽፋንም ከ13 ነጥብ 9 ወደ 18 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ከፍ ብሏል። የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት ምጣኔ በአንደኛው ዙር በተደረገው ጥናት 86 በመቶ ደርሷል። የፅድቀት መጠናቸውን ለመጨመርም ችግኞችን ዓመቱን ሙሉ በባለቤትነት መንከባከብ እና መጠበቅ ሥራ በዋናነት ተከናውኗል።

በቀጣይ የክረምት ወራት (ለ2018 ዓ.ም) የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ለማከናወን በተለያዩ አካባቢዎች ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው። ከቀበሌ እስከ ክልል ያሉ ባለሙያዎች እና አመራሮች ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ ናቸው። ችግኝ ጣቢያ ማዘጋጀት፣ ችግኝ ማፍላት፣ የተከላ ቦታ እና ችግኙ የሚስማማውን የአፈር አይነት መለየት፣ ግብዓት በተለይም ኮምፖስት እና  ደረጃውን የጠበቀ ጉድጓድ ማዘጋጀት፣ ከአየር ንብረቱ ጋር የሚስማማ ችግኝ መምረጥ እና መሰል ተግባራት በቅድመ ዝግጅት ተግባራት የተከናወኑ እና እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ናቸው። የአካባቢ ጥበቃን ታሳቢ በማድረግ በተራቆቱ እና በደጋማ አካባቢዎች የአየር ንብረቱን ተቋቁመው ሊያድጉ የሚችሉ የዛፍ ዝርያዎች ተለይተው እየተዘጋጁ ነው።

አቶ እስመለዓለም እንደገለጹት በአማራ ክልል በ77 ሺህ 959 የችግኝ ጣቢያዎች አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ችግኝ ለማፍላት ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል፤ እስካሁንም አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ችግኝ ተፈልቶ ዝግጁ ሆኗል።  ከችግኝ ማፍላት ጎን ለጎን የመትከያ ቦታ የመለየት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑንም ነው ዳይሬክተሩ ያስረዱት። በዚህም ከ260 ሺህ ሄክታር በላይ የመትከያ ቦታ ተለይቶ ዝግጁ መደረጉን አክለዋል።

የችግኝ ማፍላት ሥራው በግለሰቦች፣ በማሕበራት፣ በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና በተቋማት እየተከናወነ ነው። እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የችግኞችን የፅድቀት ምጣኔ ለማሳደግ ከግንቦት አጋማሽ ጀምሮ ችግኞች በችግኝ ጣቢያ እንዳሉ ውኃ ማጠጣትን መቀነስ፣ ሥራቸውን መገረዝ፣ ዳሱን  በማንሳት ፀሐይ እንዲያገኙ ማድረግ እና በአጠቃላይ ችግርን የማላመድ ሥራ ይከናወናል።

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ 2011 ዓ.ም ጀምሮ የአማራ ክልል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑ  መነቃቃትን ፈጥሯል ነው ያሉት።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የተከናወኑት ተግባራት በአካባቢ ሥነ ምሕዳር ላይ አወንታዊ ለውጥ ማምጣት እንደቻሉ አስገንዝበዋል። በተለይም ለደን ሽፉን መጨመር፣ ለደን ሥነ ምህዳር መጎልበት፣ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቷል።

መረጃ

በየዓመቱ ምን ያህል ችግኞች እንደ ሀገር ተተከሉ?

 

በ2011 ዓ.ም አራት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን

በ2012 ዓ.ም አምስት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን

በ2013 ዓ.ም ስድስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን

በ2014 ዓ.ም ሰባት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን

በ2015 ዓ.ም ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን

በ2016 ዓ.ም ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን

በ2017 ዓ.ም ስምንት ቢሊዮን እንዲሁም

በ2018 ዓ.ም ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን የሚጠጋ ችግኝ ለመትከል ታቅዷል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here