ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት በዘመናት የማይደበዝዝ ታሪክ አላት:: ይህም በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን በትውልድ ቅብብሎሽ የመጣ የድል ችቦ ውጤት ነው:: ከሻምበል አበበ ቢቂላ ባዶ እግር ጀምሮ፣ በማሞ ወልዴ፣ በምሩፅ ይፍጠር እና በደራርቱ ቱሉ ብርታት ታንጾ፣ በኃይሌ እና በቀነኒሳ ፈጣን እግሮች የነገሠው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ዛሬም ድረስ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማዋን በዓለም አደባባይ ከፍ አድርጎ እያውለበለበው ይገኛል:: ይህ ጉዞ የድል ብቻ ሳይሆን የማይቋረጥ ታሪክ፣ የክብር እና የተስፋ ቅብብሎሽ ጭምር ነው::
በአምስት ሺህ እና በዐስር ሺህ ሜትር የዓለምን መድረክ በበላይነት የተቆጣጠረው የኃይሌ ትውልድ ክብረ ወሰኖችን ደጋግሞ በማሻሻል የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ማድረጉን ዓለም ይመሰክራል:: የሻለቃ ኃይሌ ዘርፉን መቀላቀል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውስጥ የአንድ ትውልድ መዝጊያ እና መክፈቻ ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም ሩጫን ከስፖርታዊ ውድድርነት ባለፈ ወደ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ ልቦናዊ የበላይነት የቀየረ ትልቅ ክስተት እንጂ::
በኃይሌ ዘመን የነበረው አትሌቲክስ በዋናነት በጽናት፣ በረጅም ርቀት ሩጫ እና በታክቲክ ብልጫ ላይ የተመሰረተ እንደነበር የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያስነብበናል:: የሻለቃ ኃይሌ ትውልድ በአምስት ሺህ እና በዐስር ሺህ ሜትር የዓለምን መድረክ በብቸኝነት የተቆጣጠረበት፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በኩራት እንዲውለበለብ ያደረገበት ወርቃማ ዘመን ነበር:: በወቅቱ የነበረው ፉክክር በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል የተገደበ እንደነበር የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ድረገጽ መረጃ ያመለክታል::
በየውድድሩ የዓለም ክብረ ወሰኖችን ማሻሻል የተለመደ ክስተት በነበረበት በዚያ ዘመን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሮጡት የሀገራችውን ስም በዓለም አደባባይ ለማስጠራት እንደነበር መረጃው ይነግረናል:: ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ለተተኪው ትውልድ ያስቀመጠው አሻራ “አይቻልም” የሚለውን መንፈስ መስበሩ እና ሩጫን በሳይንሳዊ መንገድ ማሰልጠን እንደሚቻል ማሳየቱ ነው:: ከሻለቃ ኃይሌ በኋላ የመጣው በቀነኒሳ በቀለ እና በጥሩነሽ ዲባባ የሚመራው ትውልድ የኃይሌን ስኬት ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል::
ይህ ትውልድ በኃይሌ የተጀመራውን መንገድ ተከትሎ የመጣ ቢሆንም በአጨራረስ ፍጥነት እና በሁለገብነት (በአገር አቋራጭ እና በመም ውድድሮች) ፍጹም የበላይነትን ያሳየ ነበር:: ቀነኒሳ በቀለ የኃይሌን የዐስር ሺህ ሜትር ክብረ ወሰን ማሻሻል ብቻ ሳይሆን ለረጅም ዓመታት የማይደፈር አድርጎ መቆየቱን የዓለም አትሌቲክስ መረጃ አመልክቷል::
በዚህ የሽግግር ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከግለሰብ ክህሎት ባለፈ ወደ ተቋማዊ አሰራር መቀየር የጀመረበት ነበር:: ክለቦች የተጠናከሩበት፣ አትሌቶች የተሻለ የውጭ ማናጀሮች እና የማሰልጠኛ ማዕከሎች ማግኘት የጀመሩበት ወቅት ነው:: ይሁን እንጂ የዚህ ትውልድ ትልቁ መለያ የነበረው የረጅም ርቀት የመም ውድድሮች የበላይነት ነበር:: የሴቶች አትሌቲክስም ጎልቶ መውጣት የጀመረው በእነ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋር እና ሌሎች ተወርዋሪ አብሪ ኮከቦች ትውልድ ነው:: የጥሩነሽ ትውልድ አትሌቲክሱ የጾታ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲሄድ እና አገሪቱ የምታገኘው የሜዳሊያ ቁጥር እንዲጨምር አድርጎታል::
ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ገጽታ በእጅጉ መቀየሩን የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ መረጃ አስነብቧል:: በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በከፍተኛ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የታጀበበት ወቅት ነው:: በተጨማሪም የጫማ ቴክኖሎጂዎችም የውድድሩ አካል የሆኑበት ዘመን ነው:: አሁን ላይ እንደ እንዳለፉት ዘመናት በባዶ እግር ወይም በቀጫጭን ጫማዎች መሮጥ ቀርቶ በዘመናዊ ጫማዎች ሆኗል:: ይህ ደግሞ የሰዓት ልዩነቶችን እጅግ አጥብቦታል:: ሌላው አትሌቶች ከአምስት እና ከዐስር ሺህ ሜትር ውድድሮች በተጨማሪ ወደ ማራቶን እና ወደ መካከለኛ ርቀት (800 እና 1500 ሜትር) እየመጡ ይገኛሉ::
የቀደመው ትውልድ ትኩረቱ የመም ውድድሮች ላይ እንደነበር እና የዛሬው ትውልድ ግን ፊቱን ወደ የጎዳና ላይ ሩጫዎች (Road Races) ማዞሩን በኩር ጋዜጣ በመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ማስነበቧ አይዘነጋም:: እንደ ዮሚፍ ቀጀልቻ እና ትእግስት አሰፋ ያሉ አትሌቶች በማራቶን እያስመዘገቡት ያለው ውጤት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አቅጣጫውን ከመም ወደ ጎዳና እየቀየረ መሆኑን ያሳያል:: የዚህኛው ትውልድ አትሌቶች የሚሮጡት ለአገር ክብር ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት ለሚያስገኙ የጎዳና ላይ ውድድሮች ጭምር ነው:: ታዲያ እየተቀዛቀዘ የመጣው የመም ውድድር ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት የነበራትን የበላይነት እንድትነጠቅ አድርጓታል የሚሉ ሀሳቦችን አስነስቷል::
ሌላው በቀድሞው የአትሌቲክስ ትውልድ እና በዚህ ዘመን ያለው ልዩነት የውድድር ስልት እና ዝግጅት መሆኑን የሮይተርስ መረጃ አስነብቧል:: በሻለቃ ኃይሌ ዘመን አትሌቶች በአብዛኛው በብሔራዊ ቡድን ጥላ ስር ተሰባስበው ለረጅም ጊዜ በጋራ ይሰለጥኑ እንደነበር መረጃው ያስረዳናል:: ያ የስልጠና ስልት አትሌቶች እርስ በርሳቸው እንዲረዳዱ የሚያደርግ እንደነበር ይነገራል:: ዛሬ ግን አትሌቲክሱ በግል ማናጀሮች እና በተበታተነ የልምምድ ማዕከሎች የተከፋፈለ ነው:: እያንዳንዱ አትሌት የራሱ የግል አሰልጣኝ፣ የፊዚዮቴራፒ ባለሙያ እና የአመጋገብ ባለሙያ ሊኖረው የሚችልበት ደረጃ ላይም ደርሷል::
ይህ አሰራር አትሌቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ቢያስችላቸውም በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ያለውን የጋራ ቅንጅት ግን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል:: በኦሊምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮናዎች ላይ የሚታየው የታክቲክ ስህተት እና አትሌቶች እንደ ግል ተወዳዳሪ የመሮጥ ዝንባሌ የዚሁ የግል ማሰልጠኛ ማዕከሎች መስፋፋት ውጤት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል የሮይተርስ መረጃ ያትታል::
የዲጂታል ሚዲያ ተጽዕኖም በአትሌቶች ስነ ልቦና ላይ የራሱን አሻራ እያሳረፈ ይገኛል:: ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በሮጠበት ዘመን የሚዲያ ትኩረት በጋዜጦች እና በሬዲዮ ላይ የተገደበ ነበር:: ዛሬ ላይ ግን አንድ አትሌት በሮጠ በሽርፍራፊ ሴኮንዶች ውስጥ የዓለም ማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ይሆናል:: ይህ ዝና እና ትኩረት ለአትሌቶች ትልቅ የገቢ ምንጭ እና ተጨማሪ ቱሩፋት ይዞላቸው ቢመጣም ትኩረታቸው እንዲበተን እያደረጋቸው መሆኑ ግን አያጠያይቅም::
ከጊዜ ጋር አብሮ የመጣው ሌላኛው ለውጥ የውድድር አይነቶች መብዛት ነው:: በቀድሞው ዘመን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የሚታወቁት በረጅም ርቀት ብቻ ነበር:: ዛሬ ግን በሦስት ሺህ ሜትር መሠናክል ለሜቻ ግርማ፣ በ1500 ሜትር ሴቶች ጉዳፍ ጸጋይ እና ድርቤ ወልተጂ፣ በ800 ሜትር ደግሞ ጽጌ ዱጉማን የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያን ዓለምን እያስደመሙ ይገኛሉ:: የዛሬው የአትሌቲክስ ትውልድ ከቀድሞው በተለየ መልኩ ፈጣን የሆነ፣ የሜዳ ላይ ቴክኖሎጂን (Wavelight) ተጠቅሞ ፍጥነቱን የሚለካ እና በሳይንሳዊ ትንተና ላይ ተመስርቶ የሚወዳደር ነው:: ይህ የቴክኖሎጂ ጥገኝነት ግን አንዳንዴ አትሌቶች የራሳቸውን ውስጣዊ ጥንካሬ እና ስሜት ተከትለው እንዳይሮጡ ይልቁንም በሰዓት እና በቴክኖሎጂ እንዲመሩ እያደረጋቸው እንደሆነ መነገር ከጀመረ ውሎ አድሯል::
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከኃይሌ ዘመን ጀመሮ እስካሁን ካጋጠሙት ትልልቅ ፈተናዎች አንዱ የአበረታች ንጥረ ነገር(የዶፒንግ) አጠቃቀም ጉዳይ ነው:: በቀደመው ዘመን ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውስጥ ፈጽሞ የማይታወቅ እና የማይታሰብ እንደነበር የቢቢሲ ስፖርት መረጃ አስነብቧል:: ዛሬ ግን የዓለም አትሌቲክስ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርግበት እና በየጊዜው አዳዲስ አትሌቶች በንጥረ ነገር አጠቃቀም የሚታገዱበት ዘመን ሆኗል:: ይህም ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ትልቅ ስጋት እየፈጠረ መሆኑን መረጃው አልሸሸገም:: በሌላ በኩል የአትሌቶች ዝውውር ወይም ዜግነት የመቀየር ጉዳይ በዛሬው ዘመን በስፋት የሚታይ ክስተት ሲሆን ብዙ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የተሻለ ገቢ እና የውድድር እድል ለማግኘት ሲሉ ዜግነት እየቀየሩ ይገኛሉ::
ስፖርቱን ዛሬ ላይ በርካታ ችግሮች ቢፈታተኑትም የአሁኑ ትውልድ ያንን የቀድሞውን አኩሪ ታሪክ ሳያደበዝዝ ከዘመኑ ፍጥነት እና ቴክኖሎጂ ጋር አዋህዶ የማስቀጠል ታሪካዊ አደራ ተጥሎበታል:: ይህንን ታሪካዊ ቅርስ ለቀጣዩ ትውልድ ማሻገርም የዛሬው ትውልድ ትልቁ የቤት ሥራ ነው::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


