የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን እግር ኳስ ተለዋዋጭ እና ፉክክር የበዛበት በመሆኑ የአሰልጣኞችን ሥራ አክብዶታል:: በየጊዜው ተለዋዋጭ በሆነው በዚህ ሙያ ስኬታማ የሆኑ አሰልጣኞች ዕድለኛ ያስብላቸዋል:: ያልተሳካላቸውን ደግሞ ሲባክኑ እና ሲባዝኑ ማየት የተለመደ ነው:: ይህም ሥራቸውን በፈቃዳቸው እንዲለቁ ወይም ተገፍተው እንዲወጡ ያደርጋቸዋል:: የአሰልጣኞች የትናንት እና የዛሬ ስኬት ለነገ ዋስትና አይሆናቸውም። ታዲያ ክለቦች አሰልጣኞችን ሲቀጥሩ ውጤትን መሰረት አድርገው በመሆኑ ውጤት ማምጣት ያልቻሉ አስልጣኞችን አይታገሱም::
በዘመናዊ እግር ኳስ አሰልጣኞች በክለቦች ያላቸው የቆይታ ጊዜ እያጠረ መጥቷል:: ከሌሎች የአውሮፓ ሊጎች በተለየ በአምስቱ ታላላቅ ሊጎች የአሰልጣኞች ስንብት ይበዛል:: በተለይ ፉክክሩ ጠንካራ በሆነበት እንደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ባሉ ሊጎች የአሰልጣኞች የቆይታ ጊዜ አጭር መሆኑን የቢቢሲ ስፖርት መረጃ ያመለክታል:: ይህም አሰልጣኞችን ሁሌም በቀጭን መንገድ በስጋት የሚጓዙ ባለሙያዎች አድርጓቸዋል::
ክለቦች ለተጫዋቾች ዝውውር የሚያወጡት ገንዘብ እየናረ በመምጣቱ የክለብ ባለቤቶች ፈጣን ውጤት ይፈልጋሉ:: ውጤት ሲርቅ የመጀመሪያው ሰለባ አሰልጣኙ ይሆናል:: የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ እና የደጋፊዎች ከፍተኛ ግፊት የክለብ አመራሮች የረጅም ጊዜ እቅዶችን ሰርዘው አፋጣኝ ውሳኔ እንዲወስዱ እያደረጋቸው ይገኛል:: እንደ ዌስትሃም እና ዎልቭስ ያሉ ክለቦች ወደ ወራጅ ቀጠና የመጠጋት ስጋት ሲያድርባቸው የጨዋታ ባህላቸውን ትተው ነጥብ የሚያመጣ አሰልጣኝ ለመፈለግ ይገደዳሉ::
ሊያም ሮሲኒየር በቅርቡ ከቼልሲ መሰናበታቸው ይታወሳል:: ይህን ተከትሎ በዚህ የውድድር ዘመን ብቻ ከሥራቸው የተሰናበቱ አሰልጣኞች ቁጥር 11 ደርሷል:: ምንም እንኳን አጠቃላይ የተሰናበቱ አሰልጣኞች ቁጥር እ.አ.አ በ2022/23 ከተመዘገበው የ14 አሰልጣኞች ስንብት ክብረወሰን በታች ቢሆንም አሁንም የውጤት ቀውስ የገጠማቸው አሰልጣኞች በፍጥነት እየተሰናበቱ መሆኑን የቢቢሲ ስፖርት መረጃ አመልክቷል:: ይህም ክለቦች ከምንጊዜውም በላይ በትዕግሥት ማጣት አዙሪት ውስጥ መውደቁን ያሳያል::
በፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛው የአሰልጣኞች ስንብት የተመዘገበው በ2022/23 እ.አ.አ የውድድር ዘመን ነው:: በወቅቱ 14 አሰልጣኞች ተሰናብተው ነበር:: እ.አ.አ በ2022/23 11 የተለያዩ ክለቦች ናቸው 14 አሰልጣኞችን ያሰናበቱት:: ስድስት የተለያዩ ክለቦችም 11 አሰልጣኞችን ከኃላፊነታቸው አንስተዋልቸዋል::
ኖቲንግሃም ፎረስት በያዝነው የውድድር ዘመን አራት አሰልጣኞችን በመቀያየር ቀደሚው ክለብ ነው:: ኖቲንግሃም ኑኖ ስፕሪንቶ ሳንቶ፣ አንሄ ፖስቴኮግሉ፣ ሺያን ዲያች እና ቪቶር ፔሬራ እንደ እሳት በሚፋጀው ወንበር የተቀመጡ አሰልጣኞች ናቸው:: ቼልሲ ኢንዞ ማሬስካን እና ሊያም ሮሴኒርን መቀየሩ አይዘነጋም:: ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ቶተንሃም ሆትስፐርስ ደግሞ በአንድ የውድድር ዘመን ውስጥ ሁለት አሰልጣኞችን በመቀየር ቀዳሚ ከሆኑት መካከል ይጠቀሳል::
በ2025/26 የውድድር ዘመን በበርካታ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ዘንድ የታየው የአሰልጣኞች ስንብት እና ቅያሬ የሊጉን ፉክክር አዲስ መልክ አስይዞታል:: በተለይም በማንቸስተር ዩናይትድ፣ ዌስትሃም እና ዎልቭስ የተደረጉት ለውጦች የክለቦቹን ደጋፊዎች ትኩረት ስቧል::
በኦልድትራፎርድ የነበረው የሩበን አሞሪም ቆይታ በጥር 5 ቀን 2026 በይፋ ተቋጭቷል:: ክለቡ ውጤት መራቅን ተከትሎ አሞሪምን ካሰናበተ በኋላ የቀድሞው የክለቡ ተጫዋችና ረዳት አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ቡድኑን እንዲመራ በጊዜያዊነት ኃላፊነት ተሰጥቶታል:: ካሪክ በአሁኑ ወቅት ክለቡን ካለበት አለመረጋጋት አውጥቶ ወደ ቀድሞ ግርማ ሞገሱ ለመመለስ በከፍተኛ ጥረት ላይ ይገኛል::
የለንደኑ ክለብ ዌስትሃም ከግርሃም ፖተር ያለው የውል ስምምነት መስከረም 27 ቀን 2025 አብቅቷል:: ፖተርን በመተካት የቡድኑን መሪነት የተረከቡት ኑኖ ኢስፒሪቶ ሳንቶ ናቸው:: ኑኖ ቡድኑን በሊጉ ሰንጠረዥ አናት ለማስጠጋት እና የተሻለ ተወዳዳሪነትን ለመፍጠር ላይ ታች እያሉ ይገኛሉ::
ዎልቭሶች በበኩላቸው ቪቶር ፔሬራን ህዳር 2 ቀን 2025 አሰናብተዋል:: ፔሬራን ተክተው ቡድኑን ወደ ድል ጎዳና ለመመለስ የተሾሙት ሮብ ኤድዋርድስ ናቸው:: ኤድዋርድስ የክለቡን የመከላከል ችግሮች በመቅረፍ እና በሊጉ ለመቆየት የሚያስችለውን ውጤት ለማምጣት አዳዲስ ስልቶችን እየቀየሱ ይገኛሉ::
በ2022/23 እ.አ.አ የውድድር ዘመን አንድ ተሰናባች አሰልጣኝ በአማካይ ለአስራ ሰባት ዓመት ከአምስት ወራት በሥራው ላይ እንደቆየ የማች ቢንጎ መረጃ አመልክቷል:: ዘንድሮ ግን ይህ አኃዝ በግማሽ ቀንሶ ወደ ዘጠኝ ወራት ዝቅ ብሏል:: ክለቦች ለአሰልጣኞች የሚሰጡት ጊዜ በየዓመቱ እጅግ እያጠረ መጥቷል:: ለዚህም እንደ ማሳያ የሚጠቀሰው አንሄ ፖስቴኮግሉ በኖቲንግሃም ፎረስት የነበራቸው የ39 ቀናት ቆይታ እና የኢጎር ቱዶር የ44 ቀናት ቆይታ በሊጉ ታሪክ አጭር ጊዜ ሆኖ ተመዝግቧል:: ከተሰናባች አሰልጣኞች መካከል ግማሽ ያህሉ ስድስት ወር እንኳ ሳይሞላቸው የተሰናበቱ ናቸው:: ይህም እንደ ማች ቢንጎ መረጃ ክለቦች ለረጅም ጊዜ እቅድ የሌላቸው መሆኑን ያሳይል::
የአሰልጣኝ ለውጥ ሁልጊዜ ውጤት እንደማያመጣ መረጃው ይነግረናል:: እ.አ.አ በ2022/23 አሰልጣኞቻቸውን ደጋግመው የቀየሩት ሊድስ እና ሳውዝሃምፕተን ወደ ታችኛው ሊግ መውረዳቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው:: ዘንድሮም በተመሳሳይ ቼልሲ ለተጫዋቾች ዝውውር ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ቢያፈስም አሰልጣኞችን በመቀያየሩ ምክንያት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን በቀላሉ ያገኛል ተብሎ አይታሰብም:: ከሁሉም በላይ አስገራሚው ክስተት ቶተንሃም ሆትስፐር በተደጋጋሚ አሰልጣኝ ቢቀይርም አሁን ላይ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ታችኛው ሊግ የመውረድ አደጋ ተጋርጦበታል:: ኖቲንግሃም ፎረስትም አራት አሰልጣኞችን በመቀየር በሊጉ ለመቆየት የሚያደርገው ጥረት የተሳካ ቢመስልም የተረጋጋ የቡድን ግንባታ ግን እስካሁን ሊኖረው አልቻለም::
የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በአሁኑ ወቅት በአሰልጣኞች ላይ ያላቸው ትዕግሥት በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ቀንሷል:: ይህ የትዕግሥት ማጣት በዋናነት የመነጨው ከውጤት መጥፋት ስጋት እና በሊጉ የመቆየት ከፍተኛ የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ከመቸኮል ነው:: ተከታታይ ስንብቶች የቡድን ማንነትን (Club Identity) ያጠፋሉ:: ተጫዋቾች በየስድስት ወሩ አዲስ ስልት እንዲላመዱ መገደዳቸው የረጅም ጊዜ ጥንካሬያቸውን ይሸረሽርባቸዋል:: አሰልጣኙ ቢቀየርም የክለቡ የጨዋታ ፍልስፍና እንዳይቀየር የሚቆጣጠር ጠንካራ የቴክኒክ አመራር መኖር አለበት::
ሆኖም ግን አሰልጣኞችን ቶሎ ቶሎ መቀያየር የቡድንን ጥንካሬ እና ወጥነት ከማጥፋት ባለፈ ዘላቂ መፍትሄ እንዳልሆነ መረጃዎቹ ያሳያሉ:: ወደፊት ክለቦች ለአሰልጣኞች በቂ ጊዜ መስጠት ካልቻሉ የሊጉ ተወዳዳሪነት እና የተጫዋቾች እድገት አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል የቢቢሲ መረጃ ያመለክታል:: ክለቦች ከኖቲንግሃም ፎረስት እና ከቶተንሃም ወቅታዊ ቀውስ በመማር የአሰልጣኝነት ሥራን ከውጤት ባሻገር መመልከት እንደሚገባ የማች ቢንጎ መረጃ ይመከራል::
እንደ ማይክል ካሪክ እና ሮብ ኤድዋርድስ ያሉ አሰልጣኞች ሲመጡ ተጫዋቾች ራሳቸውን ለማሳየት በሚያደርጉት ጥረት ለተወሰኑ ሳምንታት የውጤት መሻሻል ይታያል:: ይህ ግን ዘላቂ መፍትሄ እንደማይሆን የቢቢሲ መረጃ ያስረዳል:: እንደ አርሴናል እና ማንቸስተር ሲቲ ያሉ ክለቦች ተፎካካሪ የሆኑት በአሰልጣኞቻቸው ላይ ትዕግስት በማድረጋቸው መሆኑን ትልቅ ትምህርት ነው:: አሰልጣኝ ሲቀጠር በስሜት ሳይሆን ከክለቡ ባህል እና ካለው የተጫዋቾች ስብስብ ጋር የሚጣጣም መሆን እንዳለበት እና ክለቦችም በጥልቀት ማጥናት እንደሚጠበቅባቸው የማች ቢንጎ ዘገባ ያመለክታል::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


