በዓለም ላይ የሀገራት ዕድገት በተፈጥሯዊ ሀብታቸው ብቻ ሳይሆን በሰው ኃይል ጥራት እንደሚወሰን በብዙ ጥናቶች ተረጋግጧል። በተለይም የልጅነት ዘመን በሰው ሕይወት ውስጥ አዕምሯዊ፣ አካላዊ፣ ማኅበራዊ እና ስነ-ምግባራዊ መሠረት የሚጣልበት ወሳኝ የዕድገት ዘመን መሆኑ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት አግኝቷል። ስለዚህም ሀገራት ቀዳማይ ልጅነት ልማትን እንደ ሀገራዊ የወደፊት ዕድገት መሠረት በመቁጠር በሰፊው እየሠሩበት ይገኛሉ።
በቅርቡ በባሕር ዳር ከተማ የተካሄደው የአፍሪካ ቀዳማይ የልጅነት ልማት ማዕከል የአምስት ዓመት ፍኖተ ካርታ ዝግጅት የምክክር መድረክ ደግሞ በኢትዮጵያ ይህ ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ትኩረት እያገኘ መምጣቱን ያሳያል። በመድረኩ የተሳተፉ ምሁራንና የዘርፉ ኃላፊዎች እንደገለጹት፣ ከጽንስ እስከ ስድስት ዓመት ያለው የሕፃናት ዘመን የሰው ልጅ ሕይወትን የሚወስን ወሳኝ ምዕራፍ ነው። በዚህ ዘመን የሚገኘው የተመጣጠነ ምግብ፣ የተሻለ ጤና አገልግሎት፣ የትምህርት ዝግጅት፣ የቤተሰብ ፍቅር እና የማኅበራዊ ድጋፍ የልጆችን የወደፊት ስኬት በእጅጉ ይወስናል።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው የልጅ አዕምሮ ዕድገት ከፍተኛው ደረጃ የሚከናወነው በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ነው። በዚህ ወቅት የሚደረግ ኢንቨስትመንት በትምህርት፣ በጤና፣ በምርታማነት እና በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ውጤት ያስገኛል። በአጠቃላይ ይህ የዕድሜ ክልል ጤናማ እና ሙሉ የሆነ ትውልድ ለመገንባት መሠረት ነው፡፡
የሕፃናት ምግብ እጥረት፣ የፍቅር እና የእንክብካቤ እጦት፣ እንዲሁም የመማር ዕድል አለመኖር ደግሞ የልጆችን የመማር አቅም እና የሕይወት ዕድል በአሉታዊ መልኩ ይጎዳል።
በብዙ የበለፀጉ ሀገራት ቀዳማይ ልጅነት ልማት እንደ ዋነኛ የመንግሥት ፖሊሲ ተወስዶ በሰፊው እየተተገበረ ይገኛል። የቅድመ ትምህርት ሽፋን ማሳደግ፣ ለእናቶች እና ሕፃናት የጤና እንክብካቤ ማቅረብ፣ የሥነ-ምግብ ፕሮግራሞችን ማጠናከር እና ለወላጆች ግንዛቤ መፍጠር በልጆች ልማት ላይ የሚሠሩ ዋና ዋና ተግባራት ናቸው። በተለይም “በልጆች ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት በሀገር የወደፊት ልማት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ነው” የሚለው አመለካከት በዓለም አቀፍ መግባቢት ላይ ተደርሶበታል።
በኢትዮጵያም ይህ ጉዳይ ትኩረት እያገኘ መጥቷል። ዩኒቨርሲቲዎች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ማኅበረሰቡ በጋራ በመሆን በሕፃናት ዕድገት ላይ የሚያተኩሩ ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ። ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ምግብ ትምህርት ክፍል መምህር ነፃነት ወርቁ (ዶ/ር) ለበኩር እንዳስረዱት፣ ዩኒቨርሲቲው ፍሬያማ ትውልድ ለመገንባት ግንዛቤ የመፍጠር፣ ጥናትና ምርምር የማካሄድ እና ውጤቶቹን ወደ ተግባር የመቀየር ሥራ እየሠራ ነው።
የልጆችን ዕድገት ውጤታማ ለማድረግ ወላጆች፣ ማኅበረሰቡ፣ መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
የታዳጊ ሕጻናት ሕይወት የሚወሰነው በቀዳማይ የልጅነት ጊዜ ምዕራፍ በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
በተመሳሳይ የአፍሪካ ቀዳማይ የልጅነት ልማት ማዕከል የአማራ ክልል አማካሪ አየልኝ ሙሉዓለም እንደገለጹት፣ ማዕከሉ የልጆችን አዕምሯዊ፣ አካላዊ እና ማኅበራዊ ዕድገት በሳይንሳዊ መንገድ በማገዝ ብቁ ትውልድ ለመገንባት እየሠራ ነው። የአምስት ዓመት ፍኖተ ካርታውም በልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ መሠረት ለመጣል ያለመ ነው። ይህም በጥናት እና በምርምር የተደገፈ ሀገራዊ ፖሊሲ እንዲቀረጽ ያግዛል ብለዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮም በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ላይ ከፍተኛ ሥራ እየሠራ እንደሆነ ተገልጿል።
የልጅ አዕምሮ ዕድገት ከፍተኛው ደረጃ የሚከናወነው በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ነው። በዚህ ወቅት የሚደረግ ኢንቨስትመንት በትምህርት ላይ የሚፈጥረው አዎንታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው።
በዚህም የቅድመ ትምህርት ሽፋንን ለማሳደግ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በመካሄድ ላይ ሲሆኑ፣ በስድስት ወራት የሚጠናቀቁ ከ300 በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ መሆናቸው ተጠቁሟል። በአማራ መልሶ ማቋቋም ፈንድ ጽሕፈት ቤት ብቻ 63 የቅድመ ትምህርት ቤቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል።
ይህ ሁሉ ሥራ በመጨረሻ የሚያስገኘው ውጤት በሥነ-ምግባር የታነፁ፣ በዕውቀት እና በክህሎት የበቁ እና ጤናማ ዜጎችን ነው። በልጆች ላይ የሚደረግ ሥራ በእርግጥም በሀገር ላይ የሚደረግ ሥራ ነው። ዛሬ በቀዳማይ ልጅነት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ነገ በጤናማ ማኅበረሰብ፣ በጠንካራ ኢኮኖሚ እና በብቁ ትውልድ የሚመለስ ነው።
ስለዚህ የሕፃናት አካላዊና አዕምሯዊ ዕድገት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የወላጆች፣ የማኅበረሰብ፣ የትምህርት ተቋማት፣ የጤና ባለሙያዎች እና የሁሉም ዜጎች የጋራ ኃላፊነት ነው። በልጆች ላይ የሚደረግ ትክክለኛ እንክብካቤና ድጋፍ ብቁ ትውልድን ከመፍጠር ባለፈ የሀገር የወደፊት ዕድልን የሚወስን መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ጉባዔ በግንቦት ወር 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሊካሄድ መሆኑ ተገልጿል።
ጉባኤው “የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ሥርዓት ለውጥ የግንባር ቀደምትነት ሚና፤ ከአካባቢያዊ ሞዴሎች ወደ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ” በሚል መሪ መልዕክት እንደሚካሄድ የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ከበደ ወርቁ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የሕፃናትን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ በምርምር እና በሳይንሳዊ ሥልጠናዎች ላይ የተመሠረተ መርሐግብር ቀርጾ ወደ ሥራ መግባቱ ተገልጿል።
ማዕከሉ በዋናነትም ተጋላጭ ቤተሰቦችን በመደገፍ ላይ ያተኩራል፣የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ያስመዘገቡትን ስኬታማ ተሞክሮ እንደ መነሻም ይወስዳል፣ የባለሙያዎችን አቅም በመገንባት የተሻለ የአሥተዳደግ ሥርዓት ለመፍጠር ይሠራል፣ የተመዘገቡ ስኬቶች እና የዜጎች ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል ነው የተባለው።
እስካሁን ባለው ሂደት በተከናወኑ የትምህርት ቤት ምገባ፣ ምቹ የመጫወቻ ስፍራዎች ግንባታ፣ የሕፃናት ማቆያ አገልግሎት እንዲሁም በቤት ለቤት ድጋፎች ከ350 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ስለመቻሉም ተብራርቷል። ኢትዮጵያ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ያካበተችውን ውጤታማ ተሞክሮ ለሌሎች ሀገራት ለማካፈል እና የሌሎችንም ልምድ ለመውሰድ ጉባዔው ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በመጭው ግንቦት በሚካሄደው በዚህ ታላቅ ጉባዔ ላይም ከሀገር ውስጥ፣ ከአፍሪካ እና ከተለያዩ አህጉራት የተወጣጡ ከ350 በላይ ተሳታፊዎች ይታደማሉ።
ቀዳማይ ልጅነት ለአንድ ሕፃን የነገ ማንነት መሠረት በመሆኑ በዘርፉ የሚከናወኑ መሰል ኢንቨስትመንቶች ለሀገር እና ለአህጉር ብልጽግና ወሳኝ ድርሻ እንዳላቸውም ተመላክቷል።
መረጃ
የልጆችን አመጋገብ በመጠበቅ ረገድ የወላጆች ሚና
- ለመላው ቤተሰብ የሚሰራ መደበኛ ምግብ እና መክሰስ ያዘጋጁ። የምግብ ሰአቶችን ከልጆችዎ ጋር ያካፍሉ እና ከእነሱ ጋር ይመገቡ።
- በምግብ ሰዓት, ከሁሉም የአመጋገብ ምድቦች የተመጣጠነ እና የተለያዩ ምግቦችን ያቅርቡ.
- ምግብን በቀላሉ ማስተዳደር በሚችሉት መንገድ ያቅርቡ። በትናንሽ ልጆች ላይ ማነቆን ለመከላከል, ለምሳሌ ምግብን መቁረጥ ወይም መፍጨት.
- ልጆችዎ ማንኪያ ወይም ኩባያ እንዴት እንደሚጠቀሙ በማስተማር ራሳቸውን ችለው መብላት እንዲማሩ እርዷቸው።
- ከእድሜ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የምግብ ዝግጅት እና ከልጅዎ ጋር በጠረጴዛ ዝግጅት ላይ ይሳተፉ።
- ልጆችዎ እንደ ቤተሰብ አብረው መብላት እና ጤናማ የቤት ውስጥ ምግብ መመገብ ያለውን ጥቅም ያስተምራቸዋል።
(ሰናይት በየነ)
በኲር የግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


