የአማራ ክልል አትሌቲክስ ፈተናዎች

0
75

የአንድ ስኬታማ አትሌት የህይወት ጉዞ መሰረት የሚጣለው በልጅነት ዕድሜ መሆኑን የዓለም አትሌቲክስ መረጃዎች ያስነብባሉ፡፡ በስፖርት ሳይንስ መርህ መሰረትም ታዳጊዎች አትሌቲክስን መጀመር ያለባቸው ዕድሜያቸው ከዘጠኝ እስከ አስራ ሦስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ቢሆንም በአማራ ክልል ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ከሳይንሳዊ መርህ ያፈነገጠ መሆኑን የአማራ ማረሚያ ቤቶች አትሌቲክስ ክለብ አሰልጣኝ የሆኑት ኮማንደር ደጀኔ ክፍሌ ተናግረዋል፡፡አሰልጣኙ ከአሚኮ በኵር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት አብዛኛዎቹ የክልሉ አትሌቶች ወደ ስፖርቱ ዓለም የሚገቡት ትክክለኛውን የዕድሜ እርከን ካለፉ በኋላ ነው። በዚህ ምክንያት ታዳጊዎቹ ወርቃማውን የመማሪያ እና ራሳቸውን የመገንቢያ ጊዜያቸውን እንደሚያጡ አስረድተዋል፡፡ከዕድሜ መግፋት እና ከቤተሰብ ጫና ባሻገር በታችኛው መዋቅር ያለው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እጦት ለዘርፉ ሌላው ፈተና መሆኑን አሰልጣኝ ኮማንደር ደጀኔ ይናገራሉ፡፡ በዋና ዋና ከተሞች ጥቂት ሜዳዎች ቢኖሩም በዞን እና በወረዳ ደረጃ ግን አትሌቶች ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ ምቹ ማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት አለ፡፡በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የስፖርት ፕሮጀክቶች እና ክለቦች የተቋቋሙት አትሌቶችን ለማፍራት ቢሆኑም ከመንግሥትም ሆነ ከሚመለከተው የስፖርት አካል ተገቢውን ድጋፍ እያገኙ አይደለም፡፡ “ፕሮጀክቶቹ በበቂ በጀት የማይደገፉ፣ አሰልጣኞቻቸው ተገቢውን ክትትል የማያገኙ እና አትሌቶቹም በባዶ እግራቸው ወይም በተቀደደ ጫማ ለመሮጥ የሚገደዱባቸው ማዕከላት ሆነዋል” ብለዋል አሰልጣኝ ኮማንደር ደጀኔ፡፡ ይህም የክልሉን አትሌቲክስ ከስሩ እያመነመነው እና ጠንካራ ተተኪዎችን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ወደ ኋላ እያስቀረው መሆኑን ገልጸዋል፡፡በአማራ ክልል  አማራ ፖሊስ፣ አማራ ማረሚያ ቤቶች እና ሌሎችም ክለቦች አቅም ያላቸውን አትሌቶች መልምለው በማሰራት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን ክለቦቹ ያላቸው የበጀት አቅም እጅግ አነስተኛ መሆኑ አትሌቶቹን በዘላቂነት ይዘው እንዳይቀጥሉ ትልቅ እንቅፋት እየሆነባቸው ነው፡፡ “በአማራ ክልል ለአትሌቶች የሚከፈለው ደመወዝ አነስተኛ ሲሆን በአዲስ አበባ የሚገኙት እንደ ባንክ እና መብራት ኃይል ያሉ ክለቦች የሚከፍሉት ደመወዝ ግን ከፍተኛ ነው፡፡ እናም  በክልሉ ውስጥ ያሉ ጠንካራ አትሌቶች የተሻለ ክፍያ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ያመራሉ” ብለዋል  አሰልጣኙ ፡፡ይህ የአትሌቶች ፍልሰት በአማራ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና በአትሌቶቹ መካከል ከፍተኛ የሆነ መቃቃርን ይፈጥራል፡፡

ፌዴሬሽኑ ዓመቱን ሙሉ ለአትሌቶቹ የሚያደርገው የስልጠናም ሆነ የቁሳቁስ ድጋፍ እጅግ አንስተኛ ሆኖ ሳለ ሀገር አቀፍ ውድድሮች ሲመጡ ግን አትሌቶቹ መጥተው ክልሉን ወክለው እንዲወዳደሩ ያስገድዳል፡፡

“ያለ ምንም ቅድመ ዝግጅት እና ድጋፍ በውድድር ወቅት ብቻ አትሌቱን ፈልጎ ማምጣት የክልሉን ስፖርታዊ መዋቅር ችግር በግልጽ ያሳያል” ሲሉም አሰልጣኝ ኮማንደር ደጀኔ ያነሳሉ፡፡ከፍተኛ ደረጃ (Elite Level) ላይ ለሚገኙ አትሌቶች አዲስ አበባ ትልቅ የዕድል በር ናት፡፡ ብዙ ጊዜ በዚያ ያለው አሰራር ግን በማናጀሮች የተጠለፈ ነው፡፡

አንድ አትሌት ምንም እንኳ ድንቅ ብቃት ቢኖረው በትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ከማናጀሮች ጋር ጠንካራ ትስስር መፍጠር ግድ ይለዋል፡፡

በዚህ የተወሳሰበ አሰራር ውስጥ የራሳቸው የሆነ ጠንካራ መዋቅር የሌላቸው የአማራ ክልል አትሌቶች መብታቸውን ለማስከበር ይቸገራሉ፡፡ አንዳንዶቹ አትሌቶች በማናጀሮቻቸው አማካኝነት የውድድር እድል ሲያገኙ ሌሎች ደግሞ አቅሙ እያላቸው የትስስሩ አካል ባለመሆናቸው ብቻ ተስፋ ቆርጠው ከስፖርቱ የሚገለሉበት አጋጣሚ መኖሩን አሰልጣኝ ኮማንደር ደጀኔ አልሸሸጉም፡፡የአማራ ማረሚያ ቤቶች እና መሰል የክልሉ ክለቦች ይህንን የአትሌቶቻቸውን ፍልሰት እና የባይተዋርነት ስሜት ለመቀነስ በማሰብ ወደ አዲስ አበባ መጥተው የራሳቸውን ማዕከል በመክፈት አትሌቶቻቸውን ሰብስበው ለማሰራት ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ጥረታቸው በበጀት እጥረት እና በአስተዳደራዊ መሰናክሎች እየተገታ ይገኛል፡፡ አትሌቶቹ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ የሚያርፉበት ደረጃውን የጠበቀ ካምፕ፣ የተመጣጠነ ምግብ እና የትራንስፖርት አገልግሎት ማቅረብ ለክልሉ ክለቦች ከባድ ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡እናም አትሌቶቹ በራሳቸው ወጪ ቤት ተከራይተው፣ ትራንስፖርት ከፍለው እና ምግባቸውን አዘጋጅተው ለመሰልጠን ተገደዋል፡፡ ይህ ደግሞ አትሌቶቹ ሙሉ ትኩረታቸውን በስልጠናቸው ላይ ብቻ እንዳያደርጉ እንቅፋት ከመሆኑም ባሻገር ክለቡ በአትሌቶቹ ላይ ሊኖረው የሚገባውን ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም እና የባለቤትነት ስሜት ያሳጣዋል ነው ያሉት የአማራ ማረሚያ ቤቶች አትሌቲክስ ክለብ አሰልጣኝ፡፡የአማራ ክልል አትሌቲክስ ከዚህ አዙሪት ወጥቶ ታሪካዊ ተፎካካሪ አትሌቶችን እንዲያፈራ ከተፈለገ ሰፊ እና ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል- የአሰልጣኙ አስተያየት ነው፡፡

ታዳጊዎች ወደ ስፖርቱ የሚቀላቀሉበትን የዕድሜ እርከን ወደ ታች ማውረድ እና በትምህርት ቤቶች ውስጥ ጠንካራ የስፖርት መሰረት መገንባት እንደሚያስፈልግ አሰልጣኙ ይጠቁማሉ፡፡

መንግሥት እና የሚመለከታቸው አካላት በየወረዳው እና በየዞኑ ደረጃቸውን የጠበቁ ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ሊገነቡ ይገባል፡፡

ለፕሮጀክቶችም በቂ የበጀት እንዲሁም የቁሳቁስ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡በተጨማሪም የክልሉ ክለቦች አትሌቶቻቸውን ማቆየት እንዲችሉ የገንዘብ ችግራቸው ሊቀረፍ እና በዘመናዊ አሰራር ሊደራጁ ይገባል፡፡ ክለቦቹ በአዲስ አበባም ሆነ በክልሉ ውስጥ የተሟላ አገልግሎት የሚሰጡ ካምፖችን በማቋቋም አትሌቶችን ከእንግልት መታደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም የአትሌቶች ደጋፊ እና አጋዥ ወደሚሆንበት የአሰራር ስርዓት ሊሸጋገር እንደሚገባ ጠቁመዋል፤ “የአማራ ክልል አትሌቶች ከታችኛው እርከን ተነስተው በዓለም አቀፍ መድረክ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማውን ከፍ አድርገው እንዲያውለበልቡ የመንግሥት፣ የፌዴሬሽን፣ የክለቦች፣ የማህበረሰቡ እና የባለሀብቱ የተቀናጀ አሰራር እና ርብርብ ያስፈልጋል” በማለት አሰልጣኝ ኮማንደር ደጀኔ ተናግረዋል፡፡

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የግንቦት 1ዐ  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here