በእግር  ኳስ  የፆታ ወሰንን  የሰበረች አሰልጣኝ

0
72

እ.አ.አ ሚያዚያ 10 ቀን 2026 በዓለም እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ በወርቅ ቀለም የሚፃፍ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ዕለት ነው። ማሪያ ሉዊዝ ኤታ የዩኒየን በርሊን ጊዜያዊ ዋና  አሰልጣኝ  ሆና የተሾመችበት ቀን ነው፡፡ ይህም  በአውሮፓ አምስቱ ታላላቅ ሊጎች ውስጥ ለወንዶች ቡድን በዋና አሰልጣኝነት የተሾመች የመጀመሪያዋ ሴት አድርጓታል፡፡ በጀርመን ቡንደስሊጋ አስከፊ የውድድር ዘመን እያሳለፈ የሚገኘው ዩኒየን በርሊን የቀድሞውን አሰልጣኝ ስቴፈን ባውምጋርትን  በማሰናበት በምትኩ እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ ማሪያ ሊዊዝ ኤታን ቀጥሯል፡፡ አሰልጣኝ ሉዊዝ ኤታ በቅርቡ በ33ኛ ሳምንት መርሀግብር ሜይንዝን ሦስት ለአንድ በማሸነፍ በአውሮፓ አምስት ታላላቅ የወንዶች ሊግ ውድድር ጨዋታ ያሸነፈች የመጀመሪያዋ ሴት መሆን ችላለች፡፡

ይህ ድል ክለቡን በወሳኝ ሰዓት ከወራጅ ቀጠና የታደገ ከመሆኑም በላይ በወንዶች እግር ኳስ ውስጥ ለዓመታት የቆየውን እና የማይደፈር ይመስል የነበረውን የሴቶች የአሰልጣኝነት ገደብ ሰባብሮ ያለፈ ትልቅ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የኤታ ስኬት በአንድ ጀምበር የመጣ እንዳልሆነ የዘ ጋርዲያን መረጃ አስነብቧል፡፡ ይልቁንም በጠንካራ መሰረት የተገነባ እና ፈተናዎችን በፅናት ያለፈ የረጅም ጊዜ ጉዞ ውጤት መሆኑን መረጃው ያስረዳል፡፡

የኤታ የአሰልጣኝነት ጥንካሬ እና ታክቲካዊ ብስለት የመነጨው ከራሷ ደማቅ የተጫዋችነት ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ ኤታ ገና በለጋ ዕድሜዋ በጀርመን የሴቶች ከፍተኛ ሊግ (Frauen-Bundesliga) ውድድር  ትልቅ ተሰጥኦ እንዳላት አስመስክራለች፡፡  ማሪያ ሉዊስ ኤታ  በሀምቡርግ፣ በክሎፕንበርግ እና በዌርደር ብሬመን ጎልብታ በቱርቢን ፖትስዳም አንጸባርቃለች፡፡ በቱርቢን ፖትስዳም  ከ2009 እስከ 2011 እ.አ.አ በተከታታይ ሦስት ጊዜ የጀርመን ቡንደስሊጋ ሻምፒዮን መሆን እንደቻለች የቢቢሲ ስፖርት መረጃ አስነብቧል፡፡ እ.አ.አ በ2010 ደግሞ የሴቶች አውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በማንሳት ድንቅ የውድድር ጊዜ አሳልፋለች፡፡

የማሪያ ሉዊዝ ኤታ አ.አ.አ በ2008 በተካሄደው የአውሮፓ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ሻምፒዮና ላይ የጀርመን ቡድን አባል በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቃለች። ከሁለት ዓመት በኋላም በ2010 እ.አ.አ በጀርመን አዘጋጅነት በተካሄደው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ላይ ለሀገሯ ተሰልፋ በመጫወት የዓለም ዋንጫ አንስታለች። ይህ ሁሉ ተስፋ ሰጪ የተጫዋችነት ዘመኗ ግን በአጭር መቅረቱን ዘ ጋርዲያን አስነብቧል፡፡ በገጠማት ከባድ የአካል ጉዳት ምክንያት ገና በ26 ዓመቷ ከተጫዋችነት ዓለም ራሷን ማግለሏን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የተጫዋችነት ህይወቷ በአጭሩ መቀጨት ለእግር ኳስ ያላትን ጥልቅ ፍቅር ሊያጠፋው ግን አልቻለም፤ ይልቁንም አቅጣጫዋን ቀይራ ሌላ ታሪክ እንድትሰራ በር ከፈተላት እንጂ። እ.አ.አ በ2018 የዌርደር ብሬመንን ከ15 ዓመት በታች  የታዳጊ ወንዶች ቡድንን በመረከብ በጀርመን የወንዶች አካዳሚ ውስጥ ብቸኛዋ ሴት አሰልጣኝ ሆና ብቅ አለች፡፡ በአካዳሚው ቆይታዋ ተጫዋቾችን በእግር ኳስ ክህሎት ብቻ ሳይሆን በስነ ልቦና ጥንካሬም የማሳደግ   ፍልስፍናዋን ማሳየት ጀመረች፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ተጫዋቾች ከሜዳ መራቃቸውን ተከትሎ በዩቲዩብ (YouTube) የቪዲዮ ስልጠናዎችን በመስጠት መሪነቷን አስመስክራለች፡፡

የእግር ኳስ እውቀቷን የተመለከተው የጀርመን እግር ኳስ ማህበር (DFB) ከ15 ዓመት በታች፣ ከ17  እና ከ19 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድኖችን እንድታሰለጥን በረዳትነት ቀጠራት፡፡  ይህ የብሔራዊ ቡድን የረዳት አሰልጣኝነት ልምድም የእግር ኳስ ታክቲካዊ እይታዋን ይበልጥ በማጎልበት በጀርመን ከፍተኛውን የአውሮፓ እግር ኳስ ፕሮ ላይሰንስ (UEFA Pro Licence) የአሰልጣኝነት ማዕረግ እንድታገኝ አስችሏታል፡፡ ከቀድሞ የታችኛው ሊግ ተጫዋች እና አሁን ላይ አሰልጣኝ ከሆነው ቤንጃሚን ኤታ ጋር ትዳር መመስረቷ ደግሞ ይበልጥ የእግር ኳስ እውቀቷን እንድታሰፋ  አግዟታል፡፡

የኤታ የአሰልጣኝነት ሙያ ወደ ከፍተኛ የወንዶች እግር ኳስ መድረክ የተሸጋገረው እ.አ.አ በ2023 ዩኒየን በርሊንን በረዳት አሰልጣኝነትን ስትቀላቀል መሆኑን የቢቢሲ ስፖርት መረጃ አመልክቷል፡፡ በወንዶች ቡንደስሊጋ እና በሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ረዳት አሰልጣኝ ሆና አዲስ ታሪክ አስመዝግባለች፡፡ እ.አ.አ በህዳር 2023 ዩኒየን በርሊን ኦግስበርግን ሦስት ለአንድ ባሸነፈበት ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ በቡንደስሊጋው የረዳት አሰልጣኞች ዙፋን  ላይ ተቀመጠች፡፡

በ2024 እ.አ.አ የዩኒየን በርሊን ዋናው አሰልጣኝ ኔናድ ብጄሊካ በቅጣት ከሜዳ በራቁበት ወቅት የመሪነት ብቃቷን በማሳየት በአውሮፓ የስፖርት መገናኛ አውታሮች መነጋገሪያ እንደነበረች የዋሽንግተን ፖስት ማስነበቡ አይዘነጋም፡፡ ኤታ ቡድኑን በሜዳ ላይ ከማስተባበር ጀምሮ የሚዲያ ሥራዎችን በከፍተኛ በራስ መተማመን ስትወጣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ድንቅ አሰልጣኝ ልትሆን እንደምትችል ብዙዎች መስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ግንቦት 2026 የተመዘገበው ድል ማሪያ ሉዊዝ ኤታ ከተጫዋችነት ዘመኗ ጀምሮ ያካበተችው የእግር ኳስ ፍልስፍና ፍሬ ያፈራበት መድረክ ሆኗል። ዝነኛዋ የእግር ኳስ ታክቲሻን ለመጀመሪያ ጊዜ የወንዶች ከፍተኛ ሊግ ጨዋታን በመምራት ታሪክ የሰራችው ሚያዝያ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ነው። ዩኒየን በርሊን በሜዳው ስታዲየም አንደር አልተን ፎርስተር ቪኤፍኤል ዎልፍስበርግን ባስተናገደበት ወቅት ነው፡፡

ማርያ ሉዊዝ ኤታ ሙሉ ቀን ስለ እግር ኳስ ብቻ የምታስብ፣ የተጋጣሚን ደካማ ጎን በመፈለግ ሰዓታትን የምታጠፋ ባለሙያ ድንቅ የእግር ኳስ ባለሙያ ናት። ከአንደበቷ የሚወጡ ቃላት እና የምትሰጣቸው የታክቲክ መመሪያዎችም የተጫዋቾቿን ልብ ያሞቃል፤ ያጀግናል። ይህ ልፋቷም ዩኒየን በርሊን በቡንደስ ሊጋው እንዲቆይ አድርጎታል፡፡ ዩኒየን በርሊንን ከወራጅ ቀጠና የመታደግ ከባድ ተልዕኮዋን በስኬት በማጠናቀቅ እግር ኳስ በፆታ ሳይሆን በእውቀት፣ በታክቲክ እና ሰውን በማስተዳደር ጥበብ ላይ የተመሰረተ መሆኑን በተግባር አረጋግጣለች።

በቀጣዩ የውድድር ዘመንም የዩኒየን በርሊን የሴቶች ቡድን ዋና አሰልጣኝ በመሆን ሌላ ምዕራፍ እንደምትጀምር ይጠበቃል፡፡ የማሪያ ሉዊዝ ኤታ አስደናቂ ጉዞ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች ህልማቸው ገደብ እንደሌለው እና በትልልቅ የወንዶች መድረክ ላይም ቢሆን በልበ ሙሉነት መሪ መሆን እንደሚችሉ ያሳየ ህያው አርአያ ይሆናል ሲል ዘ ጋረዲያን ትንታኔውን ያጠቃልላል፡፡

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የግንቦት 1ዐ  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here