የማሕበራዊ ሚዲያ ሱስና መውጫ መንገዱ

0
80

“ማሕበራዊ ሚዲያ ሲፈጠር ዋና ዓላማው በአካል መገናኘት የማይችሉ ሰዎችን በርቀት መረጃ እንዲለዋወጡ፣ እንዲነጋገሩ እና ሃሳብ እንዲያንሸራሽሩ ነበር” ያሉን በጅማ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ህክምና ክፍል ዲፓርትመንት ሄድ እና ሳይካትሪስት ዶ/ር ታምራት ተፈራ ናቸው፡፡

በቴከኖሎጂ በተሳሰረው በአሁኑ ዘመን፤ ማህበራዊ ሚዲያ በመላው ዓለም በተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ሰዎችን ግንኙነት በማመቻቸት ከፍተኛ ሚና እንደ ሚጫወትም ዶ/ር ታምራት ጠቁመዋል፡፡

ማሕበራዊ ሚዲያ ጠቃሚም ጎጂም ጎኖች እንዳሉት የጠቆሙ  ዶ/ር ታምራት፤ ማሕበራዊ ሚዲያ የምንጠቀም  ለምንድን ነው? የሚለው  ጥቅሙን ይወስናል፡፡ በሕይወታችን ካስቀመጥነው ግብ አንፃር የሚሄድ ነገር ለማየት፣ ምን ያህል ጊዜ በቀን እንጠቀማለን? ለመዝናናት ነው ወይስ የተለያዩ ትምህርታዊ ሃሳቦችንና መረጃዎችን ለማጋራት? የተለያዩ ምርትና አገልግሎቶች ለማስተዋወቅ ነው? የሚለው የአጠቃቀም ሁኔታ ይወስነዋል፡፡

እያደገ በመጣው የማሕበራዊ ሚዲያ  ታዳጊዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ  ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ። እንደ ቤተሰብ ማህበረሰብ፣  እንደ ሀገርም ታዳጊዎቹ የሚጠበቅባቸው ተግባር ትምህርታቸውን መማር ነው፡፡ ነገር ግን  ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ብዙ ጊዜ ሲያሳልፉ ትምህርት ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል፡፡

ማሕበራዊ ሚዲያ የሥነ አዕምሮ ሱስ  (socal media addiction) አለው ተብሎ እንደ ሕመም መቆጠር ጀምሯል፡፡ ይሄ ሱስ ደግሞ አዕምሮአችን ውስጥ በየቀኑ ደስተኛ እንድንሆን ፣ መግባባት እና  ሥራችንን በአግባቡ መከወን እንድንችል የሚጠቅመን “ዶፓሚን” የሚባል የኬሚካል መጠን ያለ አግባብ እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ በዘህም  ከሰዎች ጋር መግባባትን ፣ ከቤተሰብ ጋር  ማሳለፍን እንዲሁም በመግባባት የምናገኘውን ደስታ ተራ  ያደርገዋል፡፡ ይሄ ማለት ሱሰኛ ወጣት /ታዳጊ ከሰዎች ጋር መዋል ደስታ አይሠጠውም ማለት ነው፡፡

ማሕበራዊ ሚዲያ በልጆች ዕእምሮ ላይም በጣም ተፅእኖ ይኖረዋል፡፡ ልጆች በአምስቱ የስሜት ህዋሳት በዐይናቸው ያዩት እና በጆሮዋቸው የሰሙት /የመጣ/ መረጃ በሙሉ አዕምሮቸው ውስጥ የሚቀመጥ ነው፡፡ ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የሚተላለፍ ነገር በሙሉ ደግሞ ጠቃሚ ላይሆን  ስለሚችል አዕምሮቸው ጠቃሚ ባለሆነ ነገር ይሞላ እና ጠቃሚ የሆነ ነገር (መረጃ) ለመያዝ ቦታ አይኖረውም፡፡ በዚህም ምክንያት ልጆች ላይ ትኩረት ለማድረግ መቸገር፣ ፈጣሪ አለመሆን እንዲሁም አዲስ ነገር ለመፍጠር አቅማቸውን የመቀነስ ችግር ያስከትላል፡፡

ታዳጊ እና ወጣት ሁነው ማሕበራዊ ሚዲያ ሲጠቀሙ  እውነት እና ውሸት የመለየት አቅም የላቸውም፤ ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የሚቀርብ ነገር ደግሞ ግለሰቦቹ አንዲታይላቸው የመረጡትን እንጅ እውነተኛው ማንነታቸው አይደለም፡፡  የሚመለከተው ሰው በተለይ ወጣቶች የሚያዩት ነገር በሙሉ የእውነት እየመሰላቸው ራሳቸውን ማወዳደር ይጀምራሉ፡፡ ይሄ ደግሞ የበታችነት፣ የባዳነት፣ “ምንም የለኝም” የማለት ስሜት እንዲሰማቸው አድርጎ በራሳቸው እና በሚሠሩት ሥራ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ውስጥ ይከታቸዋል፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ ወደ ድባቴ(ዲኘሬሽን) በመክተት ወደ ሱስ የመግባት አሊያም ደግሞ ራሳቸውን ወደ  ማጥፋት  ይመራቸዋል፡፡ ስለዚህ ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ እውነት እና ውሸት የመለየት ዕድሜ ላይ (ብስለት) እስኪደርስ ድረስ ወላጅ የሚያዩትን ነገር መቆጣጠር እና ጊዜውን መመጠን ይገባዋል፡፡

በሌላ በኩል ማሕበራዊ ሚዲያ ማሕበራዊ ጭንቀት (socal anzayt) የምንለውን ነገር ይፈጥራል፡፡ ልጆች በብዛት ከስልክ እና ኮምፒውተር ጋር የሚያሳለፉ ከሆነ ከሰዎች ጋር ዐይን ለዐይን እየተያዩ ንግግር ማድረግ እና ረጅም ሰዓት ማውራት አይችሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ትምህርት ቤት፣ ማሕበራዊ ሕይወት ፣ ሥራ ቦታ ላይ የሚፈልጉትን ነገር መጠየቅ እንዳይችሉ፣ እንዳይግባቡ የተበደሉትን ነገር መጠየቅ የማይችሉ አድርጎ ሕይወታቸው ላይ ተፅእኖ ይፈጥራል፡፡

እንደ ዶክተር ታምራት ማብራሪያ ልጆች  ከቤተሰብ ጋር መጫወት የማይፈልጉ፣ በትንሽ በትልቁ ተነጫናጭ፣ ትእግስት የሌላቸው፣ በውሳኔያቸው  እና በትምህርታቸው ደካማ ፣ በትምህርት ቤት እና በሰፈር ጓደኛ የሌላቸው፣ ማሕበራዊ ተግባቦታቸው ዝቅተኛ  የመሆን  ምልክት ካሳዩ የአደገኛ ማሕበራዊ ሚዲያ ሱሰኛ እንደሆኑ አመላካቾች ናቸው፡፡

በአሁኑ ጊዜ የማሕበራዊ ሚዲያ ሱስ ኖሮባቸው የሚታከሙ /የህክምና ክትትል/ የሚያደርጉ ሰዎች አሉ፡፡ በህክምና ወቅት  አንድ ሰው ለረጅም ጊዜ የወሰደውን (ያደረገው) ነገር  በማቆሙ ምክንያት የሚመጡ    የባህሪ ለውጦች አሉ፡፡  ቤተሰብ  አንድ ወጣት ወይም ታዳጊ ማሕበራዊ ሚዲያን በቀን ምን ያህል ጊዜ ነው መጠቀም ያለበት?  ነፃ የሆነ ወይም ማህበራዊ ሚዲያ ሳይመለከት ሊያሳልፈው ስለሚገባ ጊዜ፣ በዛሰዓት ምን  ማድረግ አለበት? የሚሉትን በማሰብ አዕምሮው የማህበራዊ ሚዲያ ሱሱን እንዲረሳ ሌላ ጠቃሚ ነገር ማስለመድ አለበት፡፡ ለምሳሌ ብዙውን ጊዜ ከቤተሰቦቹ ጋር እየተጫወተ እንዲያሳልፍ፣ መጽሐፍ እንዲያብ፣ ከጓደኞቸጋር እንዲያሳልፍ፣ ጨዋታ እንዲጫወት፣ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲሠራ በቤተሰብ  መታገዝ ይገባዋል፡፡

ችግሩ በአንድ ጀንበር የሚለወጥ ስላልሆነ ለወራት ክትትል በማድረግ እና በሐኪም እና ከልጁ ፍላጐት ተመስርቶ በሚሠራ ህክምና /ቴራፒ/  ወደ ቀድሞ ማንነቱ እንደሚመለስም ዶ/ር ታምራት ጠቁመዋል፡፡ ቤተሰብ ችግሩን ሲያይ የራሱን ሙከራ በጊዜው ገደብ አስቀምጦ መከታተል ይገባዋል፡፡  ካልተቻለ የሥነ አዕምሮ ባለሙያዎችን በማማከር ልጃቸውን  በጊዜ እገዛ አግኝቶ ከችግሩ እንዲላቀቅ  ማድርግ ይቻላል፡፡

አዋቂ ስንሆን “የትኛው እየጎዳኝ ነው?” የሚለውን እናውቃለን፤ በብዛት ወጣቶች እና ሕፃናት ግን በሰዓቱ ችግር ውስጥ መግባታቸውን ስለማያውቁ መምህራን እና ወላጆች የመከታተል ኃላፊነት እንዳለባቸው ዶ/ር ታምራት አስገንዝበዋል፡፡

ወላጆች “ልጆቻችን ምን ያህል  ሰዓት ነው ከስልክ እና  ኮምፒውተር ጋር የሚሳልፉት? የሚያዩ ነገር ምንድን ነው? ብሎ የመቆጣጠር ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይሄን ከማድረግ  በተጨማሪ ልጆች ከቤተሰብ  ጋር የሚያወሩበት ጊዜ እንዲኖር በማድረግ ቤት ውስጥ ሲሆኑ እነሱ ራሳቸውም ስልካቸውን አስቀምጠው ጊዜ በመስጠት አርአያ መሆን እንዲሁም አብሮ የማውራት ግዴታ አለባቸው፡፡

በትምህርት ቤት ደግሞ መምህራን ማሕበራዊ (ሶሻል) ሚዲያ በትምህርታቸው እና በአዕምሯቸው ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ እንደሚኖረው ማሳየት፣ አዕምሯቸው ብዙ ነገር የሚፈጥር ቢሆንም በማይጠቅም መረጃ በመሙላት ፈጣሪ እንዳይሆኑ እና እንዲደክም የሚያደርግ ተፅእኖ እንደሚኖረው ግንዛቤ መስጠት ይገባቸዋል፡፡ በመንግሥት ደረጃ የምንመክረው ፓሊሲዎች ሊኖሩ እንደሚገባ ነው፡፡ ወጣቶችን በዕድሜ ሊገድብ የሚገባ፣ የሚያዩትን ነገሮች የሚመርጥ (የሚገድብ) ነገር መኖር እንዳለበት ያምናሉ፡፡

አንድ ሰው በ18ኛው ክፍለ ዘመን በሕይወት ዘመኑ ያገኝ ከነበረው መረጃ (ኢንፎርሜሽን) አሁን ላይ ያለ ወጣት በተወሰኑ ቀናት ውስጥ የሚያገኘው መረጃ እኩል ነው፡፡ ሁሉም መረጃዎች ጠቃሚ ስላልሆኑ አዕምሮ ጠቃሚ ባልሆኑ ነገሮች በተሞላ ቁጥር የፈጠራ አቅም መቀነስ፣ ውሳኔ የማሳለፍ እና የመግባባት አቅም ማጣት ይከሰታል፡፡   በተለይ ወላጆች ትኩረት ሰጥተው የልጆቻቸውን አዋዋል  እንዲከታተሉ ባለሙያው መክረዋል፡፡

 

መረጃ

የማሕበራዊ ሚዲያ ሱስ ምልክቶች

  • የጊዜ አለማወቅ- በቀን ከሁለት ሰዓት በላይ በስልክ መስኮት ላይ ማሳለፍ።
  • ጭንቀትና ድባቴ- ስልክ ሲጠፋ ወይም ኢንተርኔት ሳይኖር ሲቀር ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መግባት፣ ስሜታዊ መሆን።
  • ምርታማነት መቀነስ – በሥራ ወይም በትምህርት ሰዓት ትኩረት ማጣትና በማህበራዊ ሚዲያ መዋጥ።
  • ከእውነተኛ ሕይወት መራቅ -ከቤተሰብና ከጓደኞች ጋር አካላዊ ግንኙነትን በመቀነስ በምናባዊው ዓለም ብቻ መኖር።
  • የእንቅልፍ መዛባት- እስከ ሌሊት ስልክ መጠቀም።

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የግንቦት  10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here