አውቶቡስን በገመድ የጐተተው ባለክብረወሰን

0
10

የ49 ዓመቱ የአሩባ ደሴት ኗሪ 9859 ኪሎ ግራም ክብደት የሚመዝን አውቶቡስን በገመድ አንገቱ ላይ አስሮ 20 ሜትር የተለካ ርዝመት መጐተት በመቻሉ በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ክብረወሰን መስበሩን ዩፒአይ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡

ኤድመንድ ሞሊና 9859 ኪሎ ግራም  የሚመዝነውን አውቶቡስ ከፊት ለፊት በገመድ አስሮ አንገቱ ላይ በመጠምጠም ከባድ ተሽከርካሪን በመጐተት በ2024 የተያዘውን ክብረወሰን መስበር ችሏል፡፡

በ2024 እ.አ.አ በዩክሬናዊው ዲሚትሮ ህሩንስኪ 17769 ፓውንድ ክብደት የሚመዝን አውቶቡስ በመጐተት ያስመዘገበውን ክብረወሰን ኤድመንድ መስበር መቻሉንም ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

አዲስ ክብረወስን ያስመዘገበው ኤድመንድ ሞሊና 9859 ኪሎ ግራም ክብደት የሚመዝነውን አውቶቡስ በገመድ አስሮ ሲጐትት በአንገቱ  የአየር መተላለፊያ ቱቦው ላይ በተፈጠረበት ጫና መተንፈስ አለመቻል ወይም መጨናነቅ እንደገጠመው ነው የተናገረው፡፡

ባለክብረወሰኑ ኃይሉን አሰባስቦ ባደረገው እልህ አስጨራሽ ጥረትም ያለመውን ርቀት ጐትቶ ቀደም ብሎ በ2024 እ.አ.አ  የተያዘውን ክብረወሰን መስበሩን በኩራት አብራርቷል፡፡

ክብረወሰን የሰበረው ኤድመንድ ሞሊና ቀደም ባሉት ዓመታት አውቶቡስን  20  ሜትር በአንድ ጣቱ በ33 ሰከንድ ፍጥነት በመጐተት፤ የከተማ ባቡርን በገመድ አስሮ በጥርሱ በ39 ሰከንድ 20 ሜትር በመጐተት እንዲሁም ስድስት ጠርሙሶችን በሁለት እጁ በ30 ሰከንድ በመክፈት ክብረወሰኖችን አስመዝግቧል፡፡

ኤድመንድ ሞሊና የክብረወሰኖቹን መታሰቢያነት ለልጆቹ እና ለአሩባ ደሴት ኗሪዎች እንዲሆን መወሰኑን በማጠቃለያነት አስነብቧል- ድረ ገጹ፡፡

 

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር  የግንቦት 10  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ

በhttp:// www.ameco.et/Bekur

በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here