ፍልሰት አሥተዳደር እና አሠራር ሥርዓት

0
49

ፍልሰት ማለት  ሰዎች ለደህንነት፣ ለተሻለ የሕይወት ደረጃ ፣ ለሥራ ወይም ለትምህርት ፍለጋ  በሀገር ውስጥ ከቦታ ቦታ ወይም ድንበር በመሻገር  የሚደረግ ጉዞ ነው። ኢትዮጵያም መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በመከላከል እና መደበኛ በሆነ መንገድ (በሕጋዊ መንገድ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ) የሚደረግ ጉዞን  በማበረታታት የዜጎችን ደህንነትና ሰብዓዊ መብት ለማክበርና ለማስከበር ዓለም አቀፉን የፍልሰት ስምምነት (Global Compact on Migration-GCM) ፈርማለች፡፡ በስምምነቱ የተለያዩ ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎችን፣ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና ፕሮግራሞች በማካተት ተግባራዊ ስታደርግ ቆይታለች፡፡

የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ በሚደረገው ፍልሰት ውስጥ ደግሞ ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎች ይከናወናሉ፡፡  ይህንን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ብሎም የተሻለ የፍልሰት አስተዳደር እንዲኖር ለማስቻል ዓለም ዓቀፍ ሕጎችን ከማፅደቅ ጀምሮ ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎችን በማውጣት የትብብርና የቅንጅት አደረጃጀቶች ተዘርግተውም ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ አዋጅ ቁጥር 1178/12 መሰረት በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተለይም በሕግ አስከባሪ አካላት መካከል ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራር እንዲኖር እንዲሁም በዋና ዋና የወንጀል ፈጻሚዎች ላይ የሚካሄደው የሕግ ማስከበር ርምጃ እንዲጠናከር አስቀመወቷል፡፡

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሐኑ ጎሽም በሰው የመነገድ፣ ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር መላክ ወንጀሎች በዜጎች ላይ ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን እያስከተሉ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡  ይህንን ችግር ደግሞ በዘላቂነት ለመቆጣጠር የፍልሰት አሥተዳደር እና አሠራር ሥርዓት መወሰኛ ደንብ ቁጥር 252/2018 በማውጣት እና በክልሉ ምክር ቤት በማፀደቅ ከሚመለከታቸው አጋር እና ባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

በክልሉ ምክር ቤት የፀደቀው ደንብ በፍልሰት ምክንያት በዜጎች ላይ እየደረሱ ላሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ምላሽ በመስጠት ወንጀሉን ለመከላከል የሚያስችል እና ይህንን ለማድረግ ደግሞ የተቋማትን ቅንጅት የሚጠይቅ መሆኑንም ኃላፊው አንስተዋል።

በአማራ ክልል ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ በማሻገር የሚፈፀመው ንግድ በሰዎች ላይ  የሚያስከትለው አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ጉዳት እየተባባሰ የመጣ ችግር መሆኑን  ኃላፊው አንስተዋል፡፡ እነዚህን ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች ለመቆጣጠር  እና የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ የብዙ ተቋማትን ተሳትፎ እና ቅንጅት የሚጠይቅ ተግባር መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ክልሉ ይህንን ተግባር ለመቆጣጠር ጥረት ቢደረግም የራሱ የሆነ አሠራር እና አደረጃጀት የሌለው በመሆኑ የትብብር ጥምረት በመመሥረት በሕግ የታገዘ ፍልሰት አሥተዳደር እና አሠራር ሥርዓት መወሰኛ ደንብ ቁጥር 252/2018 በማውጣት ይህንን ግዙፍ ተግባር ለመቆጣጠር ማሰቡን ገልፀዋል፡፡

በክልሉ ፍትሕ ቢሮ የሕግ ምርምር ማርቀቅ እና ማጠቃለል ዳይሬክተር አቶ ፀሐይነህ አጥናፍ እንዳሉት ደንብ ቁጥር 252/2018 የወጣው  እንደ ሀገር ሰውን በሕገወጥ መንገድ ማሻገርን አስመልክቶ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1178/2012  ክልሎች የራሳቸው አስተዳደር ሊኖር እንደሚገባ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እሱን ለማስፈፀም የወጣ ደንብ ነው፡፡

ሰዎች በተለያየ ምክንያት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ስለሚዘዋወሩ  ይህንን የሚያስተባብር ከሙያ ተቋማት እና የፓለቲካ አመራሩ ጭምር ያካተተ ደንብ ነው፡፡ አዋጁ ቅጣት ላይ ያተኮረ ሳይሆን ሰዎች ከፍልሰት እንዲቆጠቡ ታስቦ የተሠራ  ነው፡፡ የሥራ ቡድኑ ሲያደራጅ ግንዛቤ ፈጠራ፣ ተጎጂዎችን መልሶ ማደራጀት፣ ጥናት እና ምርምር አድርጎ የኢኮኖሚ ችግራቸው የሚገነባበትን  ሁኔታ ያስቀመጠ ነው፡፡

አቶ ብርሐኑ ጎሽም እንደገለፁት ወንጀሉን ለመከላከልና ተጎጂዎችን ለመርዳት ከዚህ ቀደም ጥረቶች ቢደረጉም ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍና ተቋማዊ ተጠያቂነት ያለው አሠራር ባለመኖሩ የሚፈለገው ውጤት ሳይመዘገብ ቆይቷል።   አሁን የወጣው ደንብ ተቋማት ተናበው በቅንጅት እንዲሠሩ ታስቦ የወጣ  ነው፡፡   ይህም አቅማቸው የሚገነባበትን አሠራር መሠረት ያደረገ ይህንን የሚመሩ ተቋማትም ተግባሩን እንደ አንድ የሥራ መለኪያ አድርገው የሚሠሩበት ይሆናል። ተግባሩን በማይፈጽሙ ተቋማት ላይ ተጠያቂነት እንደሚኖርም አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ምሳዬ መኮንን እስካሁን ድረስ አሠራሩ ቢኖርም የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ በርካታ ወጣቶች ለሥራ ፍለጋ በደላሎች እየተታለሉ ችግር ሲደርስባቸው መቆየታቸውን አንስተዋል። አሁን በወጣው ደንብ መሠረት ተቋማት በትብብር ከሠሩ በተለይም ለወጣቶች ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ወ/ሮ ምሳዬ   አስታውሰዋል፡፡ በተለይም ቀድሞ መከላከል ላይ መሠራቱ ችግሩን እንደሚቀንስ ተናግረዋል።

 

የህግ አንቀጽ

 

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር  ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ

  • ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በተለይም የሴቶችና ሕጻናት ዝውውር እና ስደቶኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ ሥር እየሰደደ እና እየተባባሰ፣ ዜጎችን ለአስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና እንግልት እየዳረገ ነው፡፡ ችግሩን ለመፍታት በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ የሕግ ማዕቀፉ በመከላከል ላይ የተመሠረተ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፤
  • የወንጀሉ ተጎጂ ለሆኑ ሰዎች ጥበቃ፣ እንክብካቤ እና መልሶ ማቋቋም ሊደረግላቸው እንደሚገባ በመገንዘብ እና ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዕድሜያቸውን፣ ጾታቸውንና ልዩ ፍላጎታቸውን ያገናዘበ የተለየ ጥበቃ፣ እንከብካቤ እና ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ በማመን፤
  • በወንጀል ሕጉም ሆነ በሌሎች ሕጎች የተቀመጡ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ከችግሩ ስፋት አንፃር በቂ ምላሽ የማይሰጡ በመሆናቸው እና ወንጀለኞች ላይ ለጥፋታቸው ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት ለመጣል የሚያስችል ሕግ ማውጣት በማስፈለጉ፤
  • በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 18 (2) በተደነገገው መሠረት በሰዎች መነገድ የተከለከለ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ የተደራጁ ድንበር ዘለል ወንጀሎችን ለመከላከል የተደረሰውን ዓለም አቀፍ ስምምነት ፈራሚ አገር በመሆኗ፣ ስምምነቱን ተከትለው በወጡት ሕገ-ወጥ የሰዎች በተለይም የሴቶችና ሕጻናት ዝውውር ለመከላከል ለመቆጣጠርና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለመቅጣት በወጣው ፕሮቶኮል እና ስደተኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ በየብስ፣ በባህርና በአየር ማስወጣትና ማስገባት ለመከላከል የወጣ ፕሮቶኮልን ያጸደቀች በመሆኗ፣ እንዲሁም ከሕገ መንግስቱ እና ከእነዚህ ዓለም አቀፍ ሰነዶች ጋር የተጣጣመና የተሟላ ሕግ ማውጣት በማስፈለጉ፤
  • በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 55 (1) መሠረት አዋጅ ቁጥር 909/207 ወጥቷል፡፡

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here