የዓድዋ ጦርነት ምንጭ

0
56

የውጫሌ ውል በኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ  ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው እና ለታላቁ የዓድዋ ጦርነት መነሻ የሆነ ዋነኛ ክስተት ነው ሲሉ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ” በተሰኘው መጽሐፍ ገልጸዋል። ውሉ የተፈረመው ሚያዝያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም በደቡብ ወሎ አምባሰል አካባቢ በምትገኘው ውጫሌ በተባለች ቦታ ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ እንዲሁም በጣሊያን በኩል የንግሥት ማርጋሪታ ልዩ መልዕክተኛ የነበሩት ኮንት ፒዬትሮ አንቶኔሊ ስምምነቱን አጽድቀዋል። ይህ ውል የተፈረመበት ወቅት ዐፄ ዮሐንስ አራተኛ በመተማ ጦርነት ላይ የወደቁበት እና ዐፄ ምኒልክ የመላ ኢትዮጵያን ንግሥና ለመያዝ ጥረት በሚያደርጉበት የሽግግር ወቅት ላይ ነበር።

ስምምነቱ በአጠቃላይ 20 የሚጠጉ አንቀጾች የነበሩት ሲሆን በወቅቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን ግንኙነት ለማጠናከር፣ የንግድ ልውውጥን ለማስፋፋት እና የድንበር ወሰንን ለመለየት ያለመ ነበር። ሆኖም ግን ውሉ ከታለመለት ዓላማ ይልቅ ለትልቅ ቅራኔ መነሻ የሆነው በአንቀጽ 17 ላይ በተፈጠረው የትርጉም ልዩነት ምክንያት ነው። በስምምነቱ የአማርኛ ቅጂ ላይ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር ለምታደርገው ማንኛውም ግንኙነት የጣሊያንን መንግሥት እርዳታ መጠቀም “ይቻላታል” የሚል ሲሆን ይህም ለኢትዮጵያ የመምረጥ መብትን የሚሰጥ ነበር። በአንጻሩ በጣሊያንኛው ቅጂ ላይ “ይገደዳል” ወይም “ይገባታል” የሚል ትርጉም እንዲኖረው ተደርጎ ተተረጎመ። ይህ ማለት ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቷን በሙሉ በጣሊያን በኩል ብቻ እንድታደርግ የሚያስገድድና ሉዓላዊነቷን አሳልፎ የሚሰጥ ነበር።

ጣሊያኖች ይህንኑ የተዛባ ትርጉም በመጠቀም ኢትዮጵያ የጣሊያን የሞግዚት አስተዳደር ወይም ጥገኛ (Protectorate) መሆኗን ለዓለም መንግሥታት አወጁ። ዐፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ይህንን ተንኮል ሲረዱ መጀመሪያ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማስተካከል ጥረት አድርገዋል።

በአንቀጽ 17 አማካኝነት ጣሊያን የውሉን ሀሳብ በጣሊያንኛ በመቀየር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመገርሰስ የጣልያን ሞግዚት እንድትሆን ቀዳዳ እያበጀች ነው ብለው ነገሥታቱ እና መኳንንቱ ስለተገነዘቡ የውጫሌ ውልን እንደማይቀበሉት አሳወቁ፡፡ የጣሊያን መንግሥት ውሉን ለማፍረስ አሻፈረኝ በሚልበት ጊዜ የውጫሌ ውል እንዲፈርስ እና ኢትዮጵያ ለማይቀረው ጦርነት እንድትዘጋጅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ግለሰቦች መካከል የዳግማዊ ዐጼ ምኒልክ ሚስት የሆኑት እቴጌ ጣይቱ ብጡል እንደነበሩ ታሪክ ይናገራል፡፡

የጣሊያኑ መንግስት መልክተኛ ኮንት አንቶሊኒ ከምኒልክ ችሎት ቀርቦ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “ኢጣሊያ 17ኛዉ አንቀጽ ተበላሽቷል ወይም ተሳስቷል የሚባለውን አትቀበልም፡፡

በዚህም ጉዳይ ማንም ኃያል መንግሥት ሊያስገድዳት አይችልም ምክንያቱም ክብሯን የምትጠብቅ ታላቅ መንግሥት ናት።”

እቴጌ ጣይቱ በዛው በችሎቱ ስለነበሩ ወዲያዉ የአንቶሊኒን ንግግር አቋርጠዉ እንደናንተ  ሁሉ  እኛም  ክብራችን እንጠብቃለን፡፡ እናንተ የምትመኙት ኢትዮጵያ በእናንተ ስልጣን ስር እንድትሆን ነው፡፡ ይህ ለምን ጊዜም የማይሆን ነገር ነው አሉት፡፡

በአስተርጓሚ አረዳድ መሠረት አንቶሊኒ 17ኛዉ አንቀጽ አሁን አናንሳዉ ብሎ የተናገረዉን ለዐፄ ምኒልክ እንሰርዘዉ ብሎ በመነገሩ 17ኛዉ አንቀጽ መሰረዙን በአማርኛ ተጽፎ ለጣሊያኑ መልክተኛ ተሰጠቶት ሲያስተረጉመው 17ኛዉ አንቀጽ ተሰርዟል የሚል ስለነበር አንቶሊኒ በብስጭት ወደ ቤተመንግሥት ተመልሶ እንዴት እንዲህ ይሆናል፤ እኔ አንደዚህ አላልኩም ቢልም ዐፄ ምኒልክ የተናገርከው ነው የተጻፈው በማለት መልክተኛውን ለማሳመን ቢሞክሩም አልተሳካም፡፡ አንቶሊኒም ውጫሌ የተዋዋልንበት ወረቀት በፈረንሳይ ቋንቋ የተዋዋልንበት ይታይልኝ ብሎ አመለከተ፡፡

እቴጌ ጣይቱም እኛ የምናዉቀዉ በአማረኛ የተጻፈዉን ነው እንጂ የፈረንጅ ቋንቋ አናውቅም፡፡ አንተ ግን የእኛን ቋንቋ ታውቃለህ እና በአማረኛ የተጻፈዉን እየው አሉት፡፡አንቶሊኒም በመናደድ ያን ትናንት አንቀጽ 17 ተሰርዟል ተብሎ የተጻፈውን ወረቀት በመቀዳደድ የኢጣሊያ መንግሥት በጦር ኃይል እንደሚያስከብር ተናገረ፡፡ ይሄን የሰሙት አቴጌ ጣይቱም ስቀው የዛሬ ሳምንት አድርገዉ፡፡ በዚህ የሚደነግጥልህ የለም፡፡ ሂድ የፎከርክበትን አድርግ፡፡ እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ሰጥቶ ሀገሩን የማያድን ሰው በዚህ የሌለ አይምሰለህ፡፡

የገዛ ደሙን ገብሮ ለገዛ ሀገሩ መሞት ጌጥ ነው እንጅ ሞት አይባልም፡፡ አሁንም ሂድ አይምሽብህ ፤ የፎከርክበትን በፈቀደልህ ጊዜ አድርገዉ፡፡ እኛም ከዚህ እንቆይሃለን አሉት፡፡

እቴጌ ጣይቱ በተለይ “እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም፤ ነገር ግን ሀገሬን ለጣሊያን ጥገኝነት የምሰጥበት ልብ የለኝም” በማለት ለጣሊያኑ ወኪል በቁርጠኝነት ምላሽ ሰጥተዋል።

የውጫሌ ውል የፈጠረው ዲፕሎማሲያዊ ሽኩቻ ወደ ወታደራዊ ግጭት አምርቶ በ1888 ዓ.ም በመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ኩራት የሆነው የዓድዋ ድል ተመዘገበ። በጦርነቱ ሽንፈት የደረሰባት ጣሊያንም ከአንድ ዓመት በኋላ የአዲስ አበባውን ስምምነት በመፈረም የኢትዮጵያን ሙሉ ሉዓላዊነት እና የውጫሌ ውል መፍረሱን አምና ለመቀበል ተገዳለች በማለት ተክለጻድቅ መኩሪያ “አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ያስረዳሉ።

የአዲስ አበባው ስምምነት ጥቅምት 17 ቀን 1889 ዓ.ም በኢትዮጵያ እና በጣሊያን መካከል የተፈረመ ታሪካዊ ሰነድ ነው።

የስምምነቱ ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦

የመጀመሪያው እና ዋነኛው ነጥብ ለጦርነቱ መነሻ የነበረው የውጫሌ ውል ሙሉ በሙሉ መሰረዙ ነው። ጣሊያን ኢትዮጵያን የጥገኝነት አስተዳደሯ ለማድረግ የነበራትን ምኞት ትታ የኢትዮጵያን ሙሉ ነፃነት እና ሉዓላዊነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አምና ለመቀበል ተገድዳለች። ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ እንደ አንድ ሉዓላዊት ሀገር እንድትታወቅ አድርጓታል።

በሌላ በኩል በጦርነቱ ወቅት ተማርከው የነበሩ የጣሊያን ወታደሮች እንዲለቀቁ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ለእነዚህ ምርኮኞች መኖሪያ እና እንክብካቤ ለወጣው ወጪ ጣሊያን ለኢትዮጵያ መንግሥት የካሳ ክፍያ ፈጽማለች። ይሁን እንጂ ስምምነቱ የድንበር ወሰንን በተመለከተ ጣሊያን ከመረብ ወንዝ ባሻገር ያሉትን የሰሜን ግዛቶች ይዛ እንድትቆይ በመፍቀዱ ይህም ለኤርትራ እንደ ሀገር መፈጠር እና ለቆየው የድንበር ውዝግብ መነሻ ሆኗል።

የአዲስ አበባው ስምምነት ኢትዮጵያ በጦር ሜዳ ያገኘችውን ድል በሕግ እና በዲፕሎማሲ ያጸናችበት ሰነድ ነው። ከዚህ ስምምነት በኋላ ታላላቅ የአውሮፓ መንግሥታት ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመሥረት እና በቆንስላዎቻቸው በኩል ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተገፋፍተዋል።

የዓድዋ ድል እና ተከታዩ የአዲስ አበባ ስምምነት ለአውሮፓ መንግሥታት ትልቅ ድንጋጤን እና መደነቅን የፈጠረ ክስተት ነበር። ኢትዮጵያ አንዲትን የአውሮፓ ሀገር በጦር ሜዳ አሸንፋ ሉዓላዊነቷን ማስከበሯ የታላላቅ መንግሥታትን ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል። ታላላቅ መንግሥታት የሰጡት ዲፕሎማሲያዊ ምላሽ የሚከተሉትን ነጥቦች ያካትታል፦

ከስምምነቱ በኋላ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ አንድ ገለልተኛ መንግሥት ታይታለች። ቀደም ሲል ኢትዮጵያን እንደ ጣሊያን ጥገኛ አድርገው ይቆጥሩ የነበሩት እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ወዲያውኑ የራሳቸውን ዲፕሎማሲያዊ ልዑካን ወደ አዲስ አበባ ልከዋል። ፈረንሳይ በ1889 ዓ.ም፣ እንግሊዝ ደግሞ በ1890 ዓ.ም በይፋ ኤምባሲዎቻቸውን ከፍተዋል። ይህ መሆኑ ዐፄ ምኒልክ ከአውሮፓውያን ጋር እኩል በሆነ ደረጃ እንዲደራደሩ ዕድል ሰጥቷቸዋል።

ታላላቅ መንግሥታት ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ወታደራዊ ኃይል ከተረዱ በኋላ በቅኝ ግዛቶቻቸው እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የድንበር ወሰን በውል ለመለየት ተቻኩለዋል። ለምሳሌ ፈረንሳይ ከጂቡቲ፣ እንግሊዝ ደግሞ ከሱዳን እና ከሶማሊያ ጋር ያለውን ድንበር ከዐፄ ምኒልክ ጋር ተስማምተው በካርታ ላይ አስፍረዋል። ይህም ኢትዮጵያ በወቅቱ የነበራትን ግዛቶች በሕግ እንድታስከብር ረድቷታል።

ሩሲያ በጦርነቱ ወቅትም ሆነ ከጦርነቱ በኋላ ለኢትዮጵያ የነበራት አቋም የተለየ ነበር። ከጣሊያን ሽንፈት በኋላ ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራትን ግንኙነት አጠናክራለች። ቀይ መስቀልን በመላክ የቆሰሉ ወታደሮችን እንድታክም ከማድረጓም በላይ በሁለቱ ሀገራት መካከል የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ትስስርን መሠረት ያደረገ የጠበቀ ወዳጅነት እንዲመሠረት አድርጋለች።

ዲፕሎማሲያዊ ምላሹ ከአውሮፓ መንግሥታት አልፎ በአሜሪካ እና በካሪቢያን ለሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች ትልቅ ተስፋ ሆኗል። ኢትዮጵያ የነፃነት ፋና ተደርጋ መታየት በመጀመሯ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ጥቁር ሕዝቦች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት እና ግንኙነት መመሥረት ጀምረዋል። ይህም በኋላ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መሠረት ጥሏል።

የአውሮፓ መንግሥታት ኢትዮጵያን በኃይል ከመጫን ይልቅ በዲፕሎማሲ እና በድርድር መቅረብን መርጠዋል። ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያ በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ያላትን ስም ከፍ እንዲል አድርጎታል።

ሳምንቱ በታሪክ

ጋብቻው

የዐፄ ቴዎድሮስ እና የንግሥት ተዋበች ጋብቻ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ፍቅር እና ፖለቲካ የተሰናሰሉበት ትልቅ ክስተት ነው። ካሳ ኃይሉ (በኋላ ዐፄ ቴዎድሮስ) በዘመነ መሳፍንት ወቅት በሽፍታነት በነበሩበት ጊዜ የየጁ መኳንንት በተለይም የራስ አሊ እናት እቴጌ መነን ሊበን ካሳን ለማለዘብ እና በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ ልጃቸውን ተዋበች አሊን ግንቦት 11 ቀን 1840 ዓ.ም እንዲያገባ አደረጉ።

ተዋበች አሊ ከአባቷ እና ከአያቷ ይልቅ ለባሏ ለካሳ ኃይሉ ያላት ታማኝነት የላቀ ነበር። ካሳ ከአባቷ ከራስ አሊ ጋር በነበረው የሥልጣን ሽኩቻ ወቅት ተዋበች የቤተሰቦቿን ወገን ትታ ባሏን ትደግፍ ነበር። የቤተሰቦቿን ሚስጥር ለባሏ በመንገር እና ምክር በመስጠት ለካሳ ድል መምታት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጋለች። ካሳም ለተዋበች የነበረው ፍቅር እጅግ ጥልቅ እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል።

ምንም እንኳን ጋብቻው ካሳን በዘመነ መሳፍንት ሥርዓት ውስጥ ለማሰር የታለመ ቢሆንም ውጤቱ ግን ተቃራኒ ነበር። ካሳ ከተዋበች ጋር በነበረው ጋብቻ አማካኝነት ወደ መኳንንቱ መንደር ጠጋ ለማለት እና የውስጥ አሠራራቸውን ለመረዳት ዕድል አግኝቷል። ይህ ሁኔታ በኋላ ላይ ሁሉንም መኳንንት አሸንፎ ኢትዮጵያን ወደ አንድ ማዕከላዊ አስተዳደር ለማምጣት ለጀመረው ጉዞ እንደ መነሻ ሆኖታል ሲሉ ጳውሎስ ኞኞ”አፄ ቴዎድሮስ” በሚለው መጽሐፋቸው ያስረዳሉ።

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የግንቦት 10  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here