ኢትዮጵያ ሀገራችን በታሪኳ ካጋጠሟት ችግሮች የከፋ ሊባል በሚችል ችግር ውስጥ ገብታ ትገኛለች::
የውጪ ወራሪ ጠላት መጣ ሲባሉ ከዳር እስከ ዳር ተጠራርተው አንድ ኾነው በመፋለም የሀገራቸውን
ክብር እና ነጻነት አስጠብቀው ስለመኖራቸው ታሪክ የሚመሰክርላቸው ልጆቿ በተፃራሪ ጐራ ተሰልፈው
ርስ በርስ በመጠፋፋት ላይ ናቸው:: በግጭቱ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ የማያደርጉ ወገኖቻችንም
ሕይወታቸውን እንደቀልድ እያጡ ነው::
በዚህ ሀይ ባይ ባጣዉ የርስ በርስ ጦርነት ባል ያለ ሚስት፣ ሚስት ያለ ባል፣ ልጅ ያለ ወላጅ፣ ወላጅ
ያለ ልጅ እየቀረ ነው:: አካል እየጐደለ፣ ቤት ንብረት እየወደመ፣ አቅማችን ከዕለት ወደ ዕለት እየተዳከመ
በመሄድ ላይ ይገኛል:: ቅን ልቦች በሀዘን እየተሰበሩ፣ ኢትዮጵያዊያን የሰቀቀን እና የስጋት ኑሮ እየገፉ ነው::
በሕገ መንግሥቱ እንዲሁም በሌሎች የሀገራችን ሕጎች ከለላ የተደረገለት ሰብአዊ መብት እየተጣሰ
ስለመሆኑ ችግሩ ያሳስበናል የሚሉ ድርጅቶች ሳይቀሩ እየገለጹ ይገኛሉ:: ለምሳሌ “ወርልድ ጀስቲስ
ፕሮጀክት” የተባለ ድርጅት ከሰሞኑ ባወጣው የሰብአዊ መብት አከባበር ደረጃን በሚገልጸው ሪፖርቱ
የሰብአዊ መብት አከባበር በሀገራችን ባለፉት አምስት ዓመታት እያሸቆለቆለ ስለመሄዱ እና ሀገራችን
በ2023 ከ142 ሀገራት በ129ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ይፋ አድርጓል::
የኢትዮጵያዊያን ሕይዎት በኢትዮጵያዊያን መቀጠፍ፣ ለአካል ጉዳት መዳረግ፣ የቤት ንብረት
ውድመት፣ በሀገር ላይ ስደት፣ እንግልት፣ ተረጅነት… ዛሬ የተፈጠረ ችግር አይደለም፤ የወርኃ ግንቦት
1983 የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ መስተዋል የጀመረ እንጂ:: ለዚህ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ
መሄድ ደግሞ የግንቦት 1983 የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ እየተተገበረ የሚገኘው በጎሳ፣ ነገድ፣ ቋንቋ…
የተዘረጋው የፌዴራሊዝም ሥርዓት እንዲሁም በሀሰት ላይ የተመሠረተው የጥላቻ ትርክት በምክንያትነት
ይጠቀሳሉ::
ይህን ችግር እንዲሁም ምክንያቶቹን የተገነዘቡ ወገኖች ከችግሩ ፈጥነን እንወጣ ዘንድ ሕዝቡን ጨቋኝ
ተጨቋኝ ብሎ በተሳሳተ ዕይታ መፈረጅም ኾነ የጥላቻ ትርክት ማስተጋባት ለማንም ስለማይበጅ ከዚህ
አድራጎት እንድንወጣ እንዲሁም የብሔር ፌዴራሊዝም ለውጥ እንዲደረግ በየጊዜው ከመወትወት
አልቦዘኑም:: እነዚህ ወገኖች ለኢትዮጵያ የሚበጃት የኢትዮጵያዊነት ፍቅርን ማጐልበት እና አንድነትን
ማጠንከር እንደሆነ በመጠቆም በበሬ ወለደ ላይ የተመሠረተውን የጠላቻ ትርክት ለማረም በጋራ መሥራት
እንደሚገባም ከማሳሰብ አልተቆጠቡም:: በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ የሚገኙ ወገኖች ሳይቀሩ
የተሳሳቱ ትርክቶችን በማረም ብሔራዊ አርበኝነትን መፍጠር በሚያስችል አሰባሳቢ በሆነ የጋራ ትርክት
መተካት እንደሚያሻ ይጠቁማሉ::
ይሁን እንጂ፣ እነዚህ መፍትሄ አመላካች ድምጾች ሰሚ ያገኙ አይመስሉም:: በዚህ የተነሳም ጎሳን፣ ነገድን፣
ቋንቋን፣ እምነትን… መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ቀጥለው ዛሬ ለምንገኝበት አሳሳቢ ደረጃ አብቅተውናል::
በዚሁ የጥፋት ጐዳና ከቀጠልን እንደ ሀገር የመቀጠላችን ነገር የማይታሰብ መሆኑን መጠቆም ሟርተኛ
የሚያስብለን አይመስለንም:: ትናንት በርቀት ስንሰማው የነበረው፣ ዛሬ ግን የእያንዳንዳችንን ቤት እያንኳኳ
የሚገኘው ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የሀብት ንብረት ውድመት፣ መፈናቀል፣ ስደት፣
እንግልት የሁላችንም ዕጣ ፈንታ ሊሆን እንደሚችል መጠቆም ነቢይ መኾንን አይጠይቅም::
እናም ርምጃችን እጅግ ቢዘገይም አልመሸምና የጥፋት ማዕበሉ ጠራርጉ ሳያጠፋን መፍትሄ አመላካች
ድምፆች ሊደመጡ፣ ከገባንበት ችግርም ፈጥነን ልንወጣ ይገባናል:: ቀደምት ኢትዮጵያዊያን ነጻ ሀገር
ሊያስረክቡን የቻሉት፣ እነሱም በሰላም እና በፍቅር የኖሩት አንድነትን በማጽናታቸው መኾኑን ተገንዝበን
ከመለያየት ይልቅ በጋራ ልንቆም፣ ከገባንበት ችግር የመውጫ የጋራ መፍትሄም ልንሻ ግድ ይለናል::
የችግራችን ምንጩ ሕገ መንገሥታዊ ከለላ የተሰጠው የብሔር ወይም የጎሳ ፌዴራሊዝም መሆኑን
ተገንዝበን ለአንድነታችን መጠናከር፣ ለሰላማችን መስፈን፣ ለደኅንነታችን መረጋገጥ፣ ለእድገት እና
ልማታችን የሚበጅ አካታች አንዲሁም ኢትዮጵያን የሚያስቀድም ሕገ መንግሥት ይኖረን ዘንድ በጋራ
መሥራት ይኖርብናል:: ኢትዮጵያዊያንን በፍቅር፣ ባንድነት፣ በሰላም፣ በመተሳሰብ.. ሊያኖር የሚያስችል
የፌዴራል ሥርዓት መዘርጋት ግድ ይለናል::