በአሜሪካ የሮቦት መስሪያ የንግድ ድርጅት ባለቤት በአውሮኘላን ወንበር አስይዞ ያሳፈረው ሮቦት የደህንነት ጥያቄ በማስነሳቱ ዓየር መንገዱ ሮቦቶችን ላለማጓጓዝ መወሰኑን ሲቤኤስ ኒውስ ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡
የሮቦት አምራች “ስቱዲዮ” ባለቤት አሮን መህ ዴዛዴህ ከላስቬጋስ “ቢቦኘ” የተሰኘ 70 ፓውንድ የሚመዝን ሰውመሰል ሮቦትን በደቡብ ምእራብ አየር መንገድ ወንበር አስይዞ ማጓጓዙ ባስከተለው የደህንነት ፍተሻ እና ጥያቄ የበረራ ሰዓት ማስተጓጉሎ ነው የተብራራው፡፡
ሮቦቱ በእቃ መጫኛ ወይም በተለየ ስፍራ ሳይሆን እንደሰው ወንበር ተይዞለት ነበር፡፡ ሮቦቱ በተገጠመለት “ሊቲዬም ባትሪ” ማውራት ፣ጥያቄ መጠየቅ እና መሰል ተግባራትን በመከወኑ በርካታ ተሳፋሪዎችን ግራ አጋብቷል፡፡ ከዚህ አልፎም የመደናገጥ ስሜት በመፍጠሩ አስተናጋጆቹ ለባለቤቱ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡
የበረራ ባለሙያዎች ሮቦቱ የተገጠመለት ሊተዬም ባትሪ መጠኑ ከፍያለ ነው በሚል ጥብቅ ክትትል እና ፍተሻ አካሂደዋል፡፡ የሮቦቱ ባለቤት ግን የባትሪ መጠኑ ከላብቶፕ ባትሪ እንደማይበልጥ ነው ያስርዳው፡፡
ከሰዓታት መዘግየት በኃላም አውሮኘላኑ ከላስ ቬጋስ ወደ ላቭ ፊልድ መብረሩን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡ ከበረራው ጥቂት ቀናት በኃላም የደቡብ ምእራብ አየር መንገድ ሰው ሰራሽ ሮቦቶችን ላለማጓጓዝ መወሰኑ በማጠቃለያነት ለንባብ በቅቷል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


