በአሜሪካ የቦስተን የወደብ ባለስልጣናት በመጪው ሰኔ ወር የሚካሄደውን የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ በክብረወሰን ለማጀብ 45 ጫማ ወይም ከፍታ የተለካ ኳስ በመስራት ላይ መሆናቸውን ማስስፖርት ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡
ግንባታው በቦስተን በሚገኝ ኃይቅ ዳር የሚከወን ሲሆን ከየአቅጣጫው የዓይን ማረፊያ ይሆናል ተብሎ እንደሚገመትም ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው ዶሀ ላይ በ2013 እ.አ.አ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ተሰርቶ ለእይታ የበቃው ትልቁ ኳስ ክብረወሰን 38 ጫማ ከ18 ኢንች የተለካ እንደነበረም ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
ቦስተን እና ማሳቹሴት መጪውን የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ለማስተናገድ በመታጨታቸው የተመረጡት ከተሞች አመራሮች ደስተኛ መሆናቸውን አብስረዋል፡፡በዚህም የእግር ኳስ ተከታታዮች ሊመለከቱት የሚችል ባለክብረወሰን መስህብ በመትከል በደስታ እንግዶችን ለመቀበል መወሰናቸውን ነው ስራ አስፈፃሚ ሪች ዴቪ ያሰመሩበት፡፡
ውድድሩን የሚያስተናግዱት አመራሮች እንደጠቆሙት በቦታው እይታን የሚስብ ልዩ ማስታወሻ መገንባት ሰዎችን አሰባስቦ እንዲገናኙ ከማስቻሉ ባሻገር አካባቢውን በማድመቅ በባህር ዳርቻው ለሚደሰቱ ልዩ እድል ይፈጥራል፡፡
ክብረወሰን ለማስመዝገብ የሚተከለውን ግዙፍ የኳስ ምስል ለመስራት በርካታ አካላት ወጪውን በመደገፍ እየተሳተፉ መሆኑን የጠቆሙት አስተናጋጆቹ ጨዋታውን በክብረወሰን አጅበው በደስታ እንደሚያሳልፉ በመግለጽ ነው ያደማደሙት፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


