የደቡብ ሉአንግዋ ብሔራዊ ፓርክ

0
16

የደቡብ ሉአንግዋ ብሔራዊ  ፓርክ በዛምቢያ በ1972 እ.አ.አ የተመሰረተ ሲሆን ጠቅላላ ስፋቱም 9050 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ተለክቷል፡፡ በፓርኩ ውስጥ ለሚገኙ እጽዋት ፣ የዱር እንስሳት እና አእዋፍ ዙሪያውን የከበበው የሉአንግዋ ወንዝ እንደ ደም ስር ያገለግላል፡፡

የፓርኩ መልካምድራዊ አቀማመጥ መገኛ ከባህር ጠለል ዝቅተኛው 500 ሜትር እስከ ከፍተኛው 800 ሜትር ተለክቷል፡፡

የፓርኩ ልምላሜ እንደየወቅቶቹ የተለያየ ነው፡፡ የበጋ ወራት ከህዳር እስከ መጋቢት ያሉት ሲሆኑ ከሚያዚያ እስከ ጥቅምት ያሉት ደግሞ የክረምት  ወራት ናቸው፡፡ ፓርኩ ሞቃት የዓየር ንብረት የሰፈነበት ሲሆን በውስጡ 60 የተለያዩ የዱር እንስሳት ዝርያዎችም ይገኛሉ፡፡ በአካል ግዝፈት ካላቸው ጉማሬ፣ ዝሆን፣ ቀጭኔ፣ ጐሽ፣ ነብር እና አንበሳ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከዓእዋፍት 450 ዝርያዎች ፓርኩን መጠጊያ አድርግው ይኖራሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ 39ኙ አዳኝ እንዲሁም 47ቱ ከቦታ ቦታ የሚፈልሱ መሆናቸውን ድረ ገፆች አስነብበዋል፡፡

ከእፅዋት የ“ባኦባብ” ዛፍ ዝርያ እና የ“ኢቦኒ” ደን የወንዙን ዳር እና ቀጣናውን አልብሶት ይታያል፡፡

የደቡብ ሉአንግዋ ፓርክን ለመጐብኘት በተሽከርካሪ ወይም በአውሮኘላን  መጓጓዝ ይቻላል፡፡ ለጐብኚዎች በቀጣናው ስድስት ያህል ካምፖች እና ሎጂዎች ያሉ ሲሆን ከነዚህም መካከል የሉአንጋዋ ሳፈሪ፣ ድንኳኖች፣ ጐጆዎች በውብ ማረፊያነት አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ፓርኩን የሚያስተዳድረው የበላይ አካልም የዛምቢያ የዱር እንስሳት ባለስልጣን ነው፡፡

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ዛምቢያ ቱሪዝም፣ ሳውዝ ሉአንግዋ እና ሮቢን ፖፕ ሳፈሪ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የግንቦት 17   ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here