ጥንታዊዉ ግንብ

0
142

በደቡባዊ አፍሪካ የምትገኘው ዝምባቢዌ በታሪካዊ ቅርሶቿ፣ በባህላዊ ሀብቶቿ እና በጥንታዊ ሥልጣኔዋ የምትታወቅ ሀገር ናት። በዚህች ሀገር ውስጥ ከሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎች መካከል በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ስፍራ የምትይዘው “ታላቋ ዝምባቢዌ” የተባለችው ጥንታዊ የድንጋይ ከተማ ነች። ይህ ታላቅ ቅርስ አፍሪካውያን የሥነ ሕንፃ እውቀት፣ በንግድ ግንኙነት፣ በመንግሥታዊ አደረጃጀት እና በባህላዊ ሥልጣኔ ላይ ያላቸውን ከፍተኛ ደረጃ የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ ነው። ታላቋ ዝምባቢዌ ዛሬ በዓለም የታሪክ ተመራማሪዎች፣ በአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች እና በቱሪስቶች ዘንድ ታላቅ ትኩረት የምትስብ ቦታ ሆናለች።

“ዝምባቢዌ” የሚለው ቃል ከሾና ቋንቋ “የድንጋይ ቤቶች” ወይም “የተከበሩ የድንጋይ ሕንፃዎች” የሚል ትርጉም እንዳለው ይታመናል። ይህም የቦታውን ዋና መለያ በግልፅ ያሳያል፤ ምክንያቱም ከተማው በተደራጀ መልኩ በተከመሩ የድንጋይ ቅጥሮች እና ታላላቅ ሕንፃዎች ትታወቃለች። ታላቋ ዝምባቢዌ ከ11ኛው እስከ 15ኛው ክፍለ ዘመን ባለው ጊዜ በጣም የበለጸገች ከተማ ነበረች። በዚያን ወቅት በደቡባዊ አፍሪካ ካሉ ከተሞች መካከል ከፍተኛ የፖለቲካ፣ የንግድ እና የባህል ማዕከል እንደነበረች የታሪክ ማስረጃዎች ያመለክታሉ።

የታላቋ ዝምባቢዌ ነዋሪዎች በዋነኝነት የሾና ሕዝቦች እንደነበሩ ይታመናል። እነዚህ ሕዝቦች በእርሻ፣ በከብት እርባታ፣ በወርቅ ማውጣት እና በንግድ የተጠናከረ ኢኮኖሚ ነበራቸው። በዚህ አካባቢ የተገኘው ወርቅ በተለይ ለከተማዋ እጅግ ታላቅ ሀብት አስገኝቶላታል። የተለያዩ የአርኪኦሎጂ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ታላቋ ዝምባቢዌ ከምሥራቅ አፍሪካ የባሕር ዳርቻ ከተሞች ጋር ትልቅ የንግድ ግንኙነት ነበራት። በዚያም በኩል እቃዎች ወደ ቻይና፣ ህንድ እና ወደ አረብ አገራት ይደርሱ ነበር። በቦታው የተገኙ የቻይና ሸክላዎች፣ የፋርስ መስታወቶች እና ሌሎች የውጭ እቃዎች ይህን የንግድ ግንኙነት በግልፅ ያሳያሉ።

ታላቋ ዝምባቢዌን ከሌሎች ጥንታዊ ከተሞች ለየት የሚያደርጓት  የድንጋይ ሕንፃዎቿ ናቸው። እነዚህ ሕንፃዎች ያለ ሲሚንቶ ወይም ማጣበቂያ በተከመሩ ድንጋዮች የተገነቡ ናቸው። ድንጋዮቹ በተገቢው መጠን ተቀርጸው እጅግ ትክክለኛ በሚባል ስርዓት ተደርድረዋል። ይህም በዚያን ዘመን የነበሩት ሕዝቦች ከፍተኛ የሥነ ሕንፃ ክህሎት እና የምህንድስና እውቀት እንደነበራቸው ያሳያል። በአንዳንድ ቦታዎች የድንጋይ ቅጥሮቹ ከ10 ሜትር በላይ ከፍታ አላቸው፤ በጥንታዊ አፍሪካ የተገነባ ታላቅ የሥነ ሕንፃ ሥራ እንደነበርም ያሳያል።

ከተማዋ በሦስት ዋና ክፍሎች ትከፈላለች። የመጀመሪያው የኮረብታው ሕንፃ ሲሆን ይህ በከፍተኛ ቦታ ላይ የተገነባ ነው። በብዙ ታሪክ ባለሙያዎች አመለካከት ይህ ክፍል የነገሥታት ወይም የመንፈሳዊ መሪዎች መኖሪያ እንደነበር ይታሰባል። ሁለተኛው ክፍል “ታላቁ ግቢ” ተብሎ የሚጠራው ሲሆን በታላቅ የድንጋይ ቅጥር የተከበበ ነው። ይህ ቦታ በአፍሪካ ከሚገኙ ጥንታዊ የድንጋይ ሕንፃዎች መካከል እጅግ ውቡ ነው። በውስጡ የሚገኘው የኮኒካል ታወር ደግሞ ብዙ ጥያቄዎችን ያስነሳ ሕንፃ ነው። አንዳንዶች ይህ የንጉሥ ሀብት ምልክት ነበር ይላሉ፤ ሌሎች ደግሞ የምግብ ማከማቻ ወይም የሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ምልክት እንደነበር ያስባሉ። ሶስተኛው ክፍል የሸለቆው አካባቢ ሲሆን የብዙ ሰዎች መኖሪያ እንደነበር ይታመናል።

ታላቋ ዝምባቢዌ የተለመደች መንደር ወይም አነስተኛ ከተማ አልነበረችም። በዘመኗ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይኖሩባት ነበር። ይህም የተደራጀ ማህበረሰብ፣ የተዋቀረ አስተዳደር እና የተስፋፋ ኢኮኖሚ እንደነበረ ያመለክታል። ከተማዋ የፖለቲካ ኃይል ማዕከል ብቻ ሳትሆን የባህል እና የመንፈሳዊ ሕይወት ማዕከልም ነበረች። በዚያ የተገኙ ቅርሶች ሰዎቹ የተለያዩ የሃይማኖት ሥነ ሥርዓቶች እንዳሏቸውም ያመለክታሉ።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓውያን ይህን ቦታ ሲያገኙ ብዙዎች ይህን ታላቅ ሥልጣኔ አፍሪካውያን ሊገነቡት አይችሉም ብለው አስበው ነበር። አንዳንዶች ከመካከለኛው ምሥራቅ የመጡ ጥንታዊ ነጋዴዎች እንደገነቡት ለማስረዳት ሞክረው ነበር። ይህ አስተሳሰብ በዚያን ዘመን በአፍሪካውያን ላይ የነበረውን የቅኝ ግዛት እና የዘር መድልዎ አመለካከት ያንፀባርቃል። ነገር ግን በኋላ የተደረጉ የአርኪኦሎጂ ጥናቶች ከተማዋ በሾና ሕዝቦች እንደተገነባች በግልፅ አረጋግጠዋል። ይህም ታላቋ ዝምባቢዌ የአፍሪካውያን የፈጠራ ክህሎት እና የሥልጣኔ ምልክት መሆኗን አሳይቷል።

ታላቋ ዝምባቢዌ 15ኛው ክፍለ ዘመን ግን ወደ ውድቀት ገባች። የዚያ ውድቀት ምክንያቶች በሙሉ ባይታወቁም የተፈጥሮ ሀብት መመናመን፣ የንግድ መንገዶች መቀየር፣ የሕዝብ ብዛት መጨመር እና የአካባቢ አየር ለውጦች እንደ ዋና ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ከተማዋ ከወደቀች በኋላ የክልሉ የፖለቲካ ኃይል ወደ ሌሎች መንግሥታት ተዛወረ። ሆኖም ታላቋ ዝምባቢዌ በክልሉ ሕዝቦች ባህል እና ታሪክ ውስጥ ያሳደረችው ተፅእኖ እጅግ ታላቅ ነበር።

ዛሬ ታላቋ ዝምባቢዌ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ስፍራ ተብላ ተመዝግባለች። በየዓመቱ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ጎብኚዎችን ቀልብ የምትስበው “ታላቋ ዝምባቢዌ ግብም” ለዝምባቢዌ ሕዝብ የብሔራዊ ኩራት ምልክት ነች። በሀገሪቱ ባንዲራ፣ በገንዘብ እና በመንግሥታዊ ምልክቶች ላይ የሚታየው “የዝምባቢዌ ወፍ” የተባለው ታዋቂ ምስል ከዚች ቅርስ የተገኘ ነው።

በአጠቃላይ ታላቋ ዝምባቢዌ የአፍሪካ ሥልጣኔ ታላቅ ማስረጃ ናት። የድንጋይ ሕንፃዎቿ፣ የንግድ ግንኙነቶቿ፣ የፖለቲካ አደረጃጀቷ እና የባህላዊ ተፅእኖዋ አፍሪካውያን ከዘመናት በፊት ከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ እንደነበራቸው ያሳያሉ። የዚህ ቅርስ ኩራት  የዝምባቢዌ ሕዝብ ኩራት አይደለም፤ ይልቁንም የመላው አፍሪካ ታሪካዊ ሀብት እና የጥንታዊ ሥልጣኔ ድንቅ ምስክር ነው።።

 

አጫር እዉነታ

ታላቋ ዝምባቢዌ

  • ዝምባቢዌ በታሪካዊ ቅርሶቿ፣ በባህላዊ ሀብቶቿ እና በጥንታዊ ሥልጣኔዋ የምትታወቅ ሀገር ናት።
  • ታላቋ ዝምባቢዌ ዛሬ በዓለም የታሪክ ተመራማሪዎች፣ በአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች እና በቱሪስቶች ዘንድ ታላቅ ትኩረት የምትስብ ቦታ ሆናለች።
  • “ዝምባቢዌ” የሚለው ቃል ከሾና ቋንቋ “የድንጋይ ቤቶች” ወይም “የተከበሩ የድንጋይ ሕንፃዎች” የሚል ትርጉም እንዳለው ይታመናል።
  • ታላቋ ዝምባቢዌ ከ11ኛው እስከ 15ኛው ክፍለ ዘመን ባለው ጊዜ በጣም የበለጸገች ከተማ ነበረች።
  • የታላቋ ዝምባቢዌ ነዋሪዎች በዋነኝነት የሾና ሕዝቦች እንደነበሩ ይታመናል።
  • የተለያዩ የአርኪኦሎጂ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ታላቋ ዝምባቢዌ ከምሥራቅ አፍሪካ የባሕር ዳርቻ ከተሞች ጋር ትልቅ የንግድ ግንኙነት ነበራት።
  • ታላቋ ዝምባቢዌ በሦስት ዋና ክፍሎች ትከፈላለች።
  • በ19ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓውያን ይህን ቦታ ሲያገኙ ብዙዎች ይህን ታላቅ ሥልጣኔ አፍሪካውያን ሊገነቡት አይችሉም ብለው አስበው ነበር።
  • ታላቋ ዝምባቢዌ 15ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ውድቀት ገባች።
  • ዛሬ ታላቋ ዝምባቢዌ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ስፍራ ተብላ ተመዝግባለች።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here