የምርጫ ሂደቱ ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ተአማኒ እና ግልጽ እንዲሆን ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል!

0
12

ምርጫ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የሕዝብ ድምፅ የሚከበርበት፣ ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ የሚሸጋገርበት እና የሀገር የወደፊት አቅጣጫ የሚወሰንበት ታላቅ የፖለቲካ ሂደት ነው። ሃገራችን ኢትዮጵያም ከቀናት በኋላ 7ተኛዉን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አከናውናለች።

ምርጫ የአንድ ተቋም ወይም የአንድ ፓርቲ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጎች፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግሥት አካላት፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የሚዲያ ተቋማት እና የጸጥታ አካላት… የጋራ ኃላፊነት ነው፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ የሀገሩን እና የራሱን  ዕጣ ፈንታ በሰላማዊ መንገድ ለመወሰን ፍላጎቱን የሚያሳይበት እና  ይሁንታውን የሚሰጥበት  ሁነኛ መሣሪያ ሊሆን ይገባል።

በመሆኑም መራጮች የምርጫ ካርድ ከመያዝ  ባሻገር   የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፖሊሲ፣ እቅድ እና አቋም በመለየት በጥንቃቄ፣  ስሜታዊነትን በማስወገድ እና  ሀሰተኛ ወሬ ወይም ጥላቻን በመራቅ  በሀገራዊ ጥቅምና በእውነተኛ መረጃን መሠረት  በማድረግ  ለቀጣይ ዓመታት  “ይመራኛል!” የሚሉትን ፓርቲ በካርዳቸው ለመምረጥ  መወሰን ይኖርባቸዋል።

መራጮች ምርጫው ውጤታማ፣ ያማረ እና የተሳካ ይሆን ዘንድ የሚመርጧቸውን  ግለሰቦች ንቃተ ህሊናቸው የዳበረ፣ ፖለቲካውን የተረዱ እና ምህዳሩን ከግምት ውስጥ አስገብተው ለሃገራቸው እና ለሕዝባቸው  የተሻለ ሥራ የሚሠሩ እና ብቁ ዜጋን ለመፍጠር የሚጥሩ መሆናቸውን አረጋግጠው ድምጻቸውን መስጠት ይገባቸዋል።

የተሳካ ምርጫ ማለት ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ግልጽ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲካሄድ ነው፡፡  መራጩ ሕዝብም ውጤቱን በይሁንታ ሲቀበለው ነውና ይህ እንዲሆንም ሁሉም የሚጠበቅበትን ግዴታ ሊወጣ ግድ ይላል።

በሃገራችን የዘንድሮውን  ምርጫ የሀሰት ወሬ እና የጥላቻ ቅስቀሳ ሂደቱን እንዳያውከው እና የተሳሳተ መረጃን እንዳያስተላልፉ በቴክኖሎጂ ተደግፎ የሚካሄድ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት  በተለይም  ወጣቶች እና የጸጥታ አካላት ሁነቱን  በመከታተል የሰላም እና የእውነት አምባሳደሮች ሊሆኑ ይገባል!

ከእነዚህ አካላት በተጨማሪ ከፖለቲካ ፓርቲዎችም ብዙ ተግባራት እና ኃላፊነቶች   ይጠበቁባቸዋል፡፡ ለዚህም ፓርቲዎች ስለሃገር እና ስለነገ በማሰብ የግል ፍላጎትን እና አመለካከትን በማስቀደም ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የዜግነት አደራቸውን መወጣት አለባቸው።

በመሆኑም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመራጮቻቸው የተሻለ ሃሳብና ፖሊሲን በማቅረብ   ጥላቻን፣ ግጭትን እና አመጽን ከመቀስቀስ በመቆጠብ ሕዝብን በአማራጭ ሀሳብ ማሳመን ላይ በማተኮር የዜግነት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባቸዋል።

የምርጫ ሂደቱ ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ተአማኒ እና ግልጽ እንዲሆንም  የመራጮች  የድምፅ አሰጣጥ፣ የድምጽ ቆጠራ እና  ውጤት የማሳወቁ ሂደት በጥንቃቄ መከናወን አለበት፡፡ ይህንኑ ለማስተግበርም የሲቪክ ማኅበራት እና የሃይማኖት ተቋማት  በመራጭነት እና  በምርጫ ክትትል ላይ በንቃት በመሳተፍ  ሕዝቡን በማስተማር ሰላምን ለማስፈንና ዘለቄታዊ ልማትን ለማረጋገጥ ምርጫ ወደር የሌለው ተግባር ስለመሆኑ ማሳየት ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆን ከሁሉም የሚጠበቅ የዜግነት ኃላፊነት ነው፡፡

 

በኲር የግንቦት 17   ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here