አሀጋር ብሔራዊ ፓርክ በአልጄሪያ ታማንራስ ሴት ግዛት ነው የሚገኘው፡፡ ፓርኩ በ1987 እ.አ.አ የተመሰረተ ሲሆን ስፋቱም 450,000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ተለክቷል፡፡ ፓርኩ በዓለም ላይ በስፋታቸው ቀዳሚ ከሆኑት አንዱ ነው፡፡
በመልካምድራዊ አቀማመጡ ተራሮች፣ በእሳተ ገሞራ የተፈጠሩ ተራራማ የደጋ መሬት፣ የአሽዋ ክምሮች፣ ተሸርሽረው የቆሙ ዓለቶች እና ጥንታዊ የጥበብ ስራዎችን የያዙ አለቶችን አካቶ ይዟል፡፡
ፓርኩ ሙሉ በሙሉ በሰሀራ በረሀ ውስጥ የተከለለ በመሆኑ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ነው የሚያገኘው፡፡ ፓርኩ በዩኔስኮ “የባዮስፌር ሪዘርቭ” ተብሎ የተሰየመ ሲሆን ባለፉት ምእተዓመታት “ቱዋሬግ” የተሰኙ ቀደምት ሰፋሪ ጐሳ መኖሪያነቱ ነው የሚታወቀው፡፡ ኗሪዎቹም ዘላን እና ከፊል አርብቶ አደሮች ናቸው፡፡
የሙቀት መጠኑ ከፍተኛ ነው- በበጋ (ከሰኔ- ነሀሴ)40 ዲግሪ ሴሊሺየስ፣ በክረምት ምሽት ከታህሣስ – ጥር ደግሞ በተራራዎች ላይ እስከ ዜሮ ዲግሪ ሴልሽየስ – ይወርዳል፡፡
በፓርኩ ክልል 2500 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው የአታኮር አምባ ቀዝቃዛ የዓየር ንብረት ያለው ሲሆን አልፎ አልፎ በክረምት በረዶ ይታይበታል፡፡ በፓርኩ የሚገኘው አሀጋር ተራራ ወይም ሆጋር ተራራ ደረቅ እና ሞቃታማዎቹ ከግንቦት እስከ ነሀሴ ያሉት ወራትም ለጐብኚዎች አይመከሩም፤ ከጥቅምት እስከ መጋቢት ያሉቱ ግን ተመራጭ መሆናቸውን ድረ ገፆች አስነብበዋል፡፡
ቀጣናው የተለያዩ ጥንታዊ የአለት ላይ ቅርፃ ቅርፆች መገኛ ነው፡፡ ጐብኚዎችም በቱዋሬጐች ሰፈር በባህላዊ መጠለያዎች ወይም በድንኳኖች ውስጥ ማረፍ ይችላሉ፡፡
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ናሽናል ፓርክ አፍሪካ፣ ናሽናል ፓርክ አሶሴሽን ዶት ኦርግ፣ አልጄሪያ ድረ ገጽችን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


