ለአብራሪነት ታጭቶ በጃዝ የነገሠው

0
297

“ውጊያዬ የአፍሪካን ሙዚቃ ለማሳደግ ነው፤ ሁሉንም ነገር ያገኛችሁት ከአፍሪካ ነውና፡፡

አፍሪካ ለዓለም ባህል ብዙ ሰጥታለች፤ ነገር ግን እንደሚገባት ዕውቅና አላገኘችም፡፡ ለእነዚህ መሠረቶቻችን ክብር መስጠት አለብን” ሙላቱ አስታጥቄ  ኮስሞፖላይት ሲን  በተሰኘ ገጽ ላይ ያደረገው ንግግር ነው፡፡

ሙላቱ አስታጥቄ በ1936 ዓ.ም በጅማ ከተማ ተወለደ፡፡ እ.ኤ.አ በ1956 ወላጆቹ ወደ ሰሜን ዌልስ የላኩት የኤሮኖቲካል ኢንጂነሪንግ (የአውሮፕላን ምህንድስና) እንዲያጠና ነበር፡፡

ሆኖም ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ እንደዘገበው ሙላቱ በዌልስ በሚገኘው ሊንዲስፋርን ኮሌጅ እያለ በትራምፔት መሣሪያ ተማርኮ ትምህርቱን ወደ ሙዚቃ ለወጠ፡፡

በወቅቱ የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር የሙላቱን ተሰጥኦ ተመልክተው “ሙዚቀኛ ብትሆን ስኬታማ ትሆናለህ” የሚል ምክር ሰጡት፡፡ ይህ ምክር ሙላቱን ወደ ለንደን ትሪኒቲ የሙዚቃ ኮሌጅ መራው፡፡ በዚያም ከጋናው ኦሲቢሳ ሙዚቃ ባንድ መስራች ቴዲ ኦሴይ እና ሌሎች ታላላቅ አፍሪካውያን ሙዚቀኞች ጋር የመገናኘት ዕድል አገኘ፡፡

በተለያዩ የምሽት ክበቦችና የቴሌቪዥን ሥርጭቶች ዝግጅቱን በማቅረብ የነበረውን የሙዚቃ ተሰጥኦ በተደጋጋሚ አስመስክሯል፡፡

ከዚህም አልፎ ነፍስ ነሽ የተሰኘውን የመጀመሪያ አልበሙን ፋራንክ ሆልዳና ኒያዝ አልሸሪፍ ከተሰኙ  አሳታሚዎች ጋር በመተባበር አቅርቧል፡፡

ወደ ሰሜን አሜሪካ ከተጓዘ በኋላ በ1958 ዓ.ም አፍሮ – ላቲን ሶል (Afro -Latin Soul) ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት አልበሞቹን ለማሳተም በቅቷል፡፡ በመጀመሪያው አልበም አይፈራም ጋሜ፣ አልማዝ እና አክሱም የተሰኙትን ኢትዮጵያዊ ሙዚቃዎችን ሲያካትት በሁለተኛው ቆንጂት እና ከረዩ የተሰኙትን ሠርቷል።

ኢትዮ ጃዝ ዛሬ በዓለማችን እንደ አንድ የሙዚቃ ስልት ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ የኢትዮ ጃዝ ማዕከላዊ ሃሳብ የጃዝ ሙዚቃን ባህርያት ከአገር በቀል የኢትዮጵያ ሙዚቃና የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር ማንነታቸውን ሳይለቁ ማዋሐድ ነው፡፡

በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወደ አሜሪካ በማቅናት በታዋቂው በርክሊ የሙዚቃ ኮሌጅ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ተማሪ በመሆን ተማረ፡፡ በአሜሪካ በሚገኘው ኸርትኔት ሞደርን ሚውዚክ ኮሌጅ ውስጥ ተጨማሪ የአራት ዓመታት ትምህርቱን አጠናቋል፡፡

ለኮስሞፖላይት ሲን በሰጠው ቃለ ምልልስ እንደገለጸው ሙላቱ በበርክሊ በነበረበት ወቅት የአገሩን አምስት ኖታ ቅኝቶች (Pentatonic scales) ከምዕራባውያን ጃዝ ጋር በማዋሃድ አዲስ የሙዚቃ ሳይንስ ፈጥሯል፡፡

በ1966 ዓ.ም በኒውዮርክ “Afro-Latin Soul” የተሰኙ ሁለት አልበሞችን በማውጣት የኢትዮጵያን ቅኝት ከላቲን ሪትም ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ አዋሐደ፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው መጀመሪያ ላይ ሙዚቃው እንግዳ ስለነበር ሕዝቡ “አቁም፣ ውረድ!” እያለ ይቃወመው ነበር፡፡ ሆኖም ሙላቱ ጸና፡፡ እ.አ.አ በ1973 ከአሜሪካዊ የፒያኖ ተጫዋች፣ የሙዚቃ አቀናባሪ እና የቢግ ባንድ መሪ ከነበረው ኤድዋርድ ኬኔዲ (ዱክ ኤሊንግተን) ጋር በመጫወት ክብሩን አሳየ፡፡

የሙላቱ ታዋቂ ሥራ የሆነው የከርሞ ሰው እ.አ.አ በ2005 “Broken Flowers” ፊልም ውስጥ በማጀቢያ ሙዚቃነት መካተቱ ዓለም አቀፍ ዝናን አተረፈለት፡፡ ዘ ኮንቨርሴሽን ገጽ እንደዘገበው ይህ ዜማ የተሠራው በ“ትዝታ” ቅኝት ቢሆንም አወቃቀሩ ግን የዓለምንና የአገርን ድምፅ ያዋሐደ ነው፡፡

ዜማው ከጃዝ ሙዚቀኛው ሆራስ ሲልቨር “Song for My Father” የተወሰደ ቢሆንም ሙላቱ ግን የራሱን የኢትዮጵያ ነፍስ ዘርቶበታል፡፡ ሙላቱ አስታጥቄ ስለ ሙዚቃ መሣሪያዎች ያለው ትንታኔ የአፍሪካን የበላይነት የሚያሳይ ነው፡፡

“ማሲንቆና ቼሎ ተመሳሳይ ድምፅ አላቸው፤ ግን የትኛው ቀደመ?” ሲል ይጠይቃል፡፡

ሙላቱ እነዚህን መሣሪያዎች የፈጠሩትን የአገሩ ጥበበኞች “የእኛ ሳይንቲስቶች” ብሎ ይጠራቸዋል፡፡

የሙላቱ ፍልስፍና ግልጽ ነው “አፍሪካ ትፈጥራለች፤ አውሮፓ ደግሞ ታለማለች-ታሳድጋለች”  ብሎ ያምናል፡፡ ቼሎን የፈጠረው ሰው ማሲንቆን የፈጠረው ሰው እንደሆነና ልዩነቱ የማስፋፋት ጉዳይ ብቻ እንደሆነ ይከራከራል፡፡ የፒያኖም አመጣጥ ከአፍሪካ እንደሆነ በምርምር ማረጋገጡን ኮስሞፖላይት ሲን ላይ በሰጠው ቃለ ምልልስ ገልጿል፡፡

ሙላቱ እንደሚለው በምዕራቡ ዓለም ሙዚቃ እንደ ሕክምናና ሳይንስ ይታያል፡፡

“በአውሮፓ ለ60 እና 80 ሰዎች ኦርኬስትራ ሲጽፉ እንደ ሐኪም ነው የሚታዩት፤ ዜማውን፣ ስምምነቱንና ድምፁን በጥንቃቄ ያቀናጃሉ” ይላል፡፡ እሱም የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዚህ የሳይንስ ቀመር ለመቅረጽ ስድስት አሥርተ ዓመታትን አሳልፏል፡፡

ሙላቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀውን የጃዝ ሙዚቃ አላባውያን እንዳለ ከመገልበጥ ይልቅ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ያልተቋረጠ ጥናት በማካሄድና ግኝቶቹን በሥራዎቹ ውስጥ በማካተት የተለያዩ ሥራዎችን አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያው ሙላቱ (Mulatu of Ethiopia) የተሰኘውን ሦስተኛውን አልበም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ድጋፍ ወደ አሜሪካ በማቅናት አበርክቷል፡፡ በመቀጠል በአገር ውስጥ የመጀመሪያ የሆነውን ኩሉን ማንኳለሽ አልበም በሚል ርዕስ ከፊሊፕስ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር አሳተመ፡፡

ለኢትዮጵያ አየር መንገድ በተከታታይ የተቀረጹትን ኢትዮ ጃዝ እና አስዮ ቤሌማ የተሰኙትን በምሣሌነት ይጠቀሳሉ፡፡ በተለያዩ የአገራችን ብሔረሰቦች ሙዚቃዎችና አገር በቀል የሙዚቃ መሣሪያዎች ላይ የሚያደርጋቸው ዘርፈ ብዙ የምርምር ሥራዎችም ጭምር አድርጓል፡፡

ከሰሜኑና ከመካከለኛው የአገራችን የሙዚቃ ባህል ባለፈ በኮንሶ፣ በወላይታ፣ በከፋ፣ በደራሼ፣ ጋሞ፣ አኙዋክ፣ በሱርማና በሌሎችም ብሔረሰቦች ሙዚቃ ላይ ምርምር አድርጓል፡፡

እ.አ.አ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ያደረጋቸው የረጅም ዓመታት ሥራዎች በዓለም አቀፍ መድረክ ይበልጥ እውቅና አስገኝተውለታል፡፡ በተለይ ፓሪስ የሚገኘው ቡዳ ሚውዚክ የተሰኘው ሪከርድ ሌብል ኢትዮ ጃዝና ኢንስትሩመንታል በሚል ርዕስ በሙላቱ ከተቀነባበሩት ቀደምት ሥራዎች የተወሰኑትን ለዓለም አቀፍ አድማጭ ማድረሱ በስፋት እንዲታወቅ አድርጐታል፡፡

ሙላቱ ከዚህ ቀደም ሲልም በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም አቀፍ የሙዚቃ መማክርት ሽልማት ዕጩ ፣የኢንተርናሽናል ጃዝ ፌዴሬሽን የቦርድ አባል እንዲሁም የፖላንድ የጃዝ ማኅበርና የብሔራዊ ጃዝ ኤዱኬተርስ አባል ወ.ዘ.ተ ሆኖ ሠርቷል።

ከታዋቂ ሰዎች ጋር ብዙ ኮንሰርቶችን አዘጋጅቷል፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችንም አግኝቷል፡፡ ከአገራችንም አልፎ የዓለማችን ብርቅዬ አርቲስት በመሆኑ በጀርመን አገር በስሙ መንገድ ተሰይሟል፡፡

ሙላቱ ከአሜሪካው የበርክሌይ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ ኮሌጅ የክብር ዶክትሬት ያገኘ ሲሆን፤ በሰሜን አሜሪካ በቦስተን ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ታላቅ የሽልማት ሥነ ሥርዓት የክብር ዶክትሬቱን ተሰጥቶታል፡፡

ከሳምንታት በፊት  በአዲስ አበባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም  የ82 ዓመቱ ሙላቱ አስታጥቄምስጋና እና እውቀና ተሰጥቷል፡፡ በዚህ መድረክም “በአፍሪካ ውስጥ ብዙ ታላላቅ ሳይንቲስቶች አሉ፤ እባካችሁ ክብር ስጧቸው፣ ውደዷቸው፣ የሚሰሩትንም ተከተሉ” ብሏል።

ሙላቱ በፈረንሳይና በጣሊያን መንግሥታት ከፍተኛ የክብር ኒሻኖችን ያገኘ እና የአገሩን ስም በዓለም ካርታ ላይ በትልቁ ያስጠራ ሊቅ ነው፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው ሙላቱ ከዓለም አቀፍ ኮንሰርት ጉዞዎች ጡረታ ቢወጣም ሥራው ግን አያበቃም፡፡ በአዲስ አበባ በሚገኘው “አፍሪካ ጃዝ ቪሌጅ” (African Jazz Village) ወጣቶችን ማስተማሩንና ምርምሩን ቀጥሏል፡፡

በ2025 Mulatu Plays Mulatu የተሰኘውን የመሰናበቻ አልበሙን ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ አልበም የኢትዮጵያን ባህላዊ መሣሪያዎች ማለትም ክራር፣ ማሲንቆ፣ ዋሽንትና በገናን ከዓለም አቀፍ የጃዝ ስልት ጋር በከፍተኛ ጥራት ያዋሐደ ነው፡፡

 

ማረፊያ

መብረር እችላለሁ!

መሄድ እየቻልኩ መብረር እንደ ወፍ፣

እንደ ንስሩ በአድማስ መንሳፈፍ፣

ታስሯል በገመድ ቢሉኝ ገረመኝ፣

እምነት ነበረ እኔስ ያቆመኝ፡፡

እውነቴን ስማ ና ባለ ገመድ፣

አሰርኩት ብለህ እንዳትሸወድ፣

ታምኜህ እንጂ ሁሉን አውቃለሁ፣

እንኳን መራመድ፣ መብረር ‘ችላለሁ፡፡

ገጣሚ ተሾመ ብርሀኑ

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሰኔ 1   ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here