ትዳር እና ኃላፊነት

0
360

ሰዎች ወደ ትዳር ሲገቡ ውሳኔው የሁለቱ ተጋቢዎች ብቻ ሳይሆን በአካባቢያቸው ያሉ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ተጨምሮ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድሩበት ተቋም  መሆኑን የሚገልፁልን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ መምህር አቶ አውግቸው ሽመላሽ ናቸው። ይህ ተፅዕኖ በጥሩ ጎኑ ትዳሩን ሊደግፍ ወይም በአሉታዊ ጎኑ ትልቅ ጫና ሊፈጥር የሚችል ነው፡፡ በተለይም የጓደኛ ግፊትን፣ የቤተሰብ ፍላጎትን፣ የራስ አቅም ሁኔታን መሠረት በማድረግ ተፅዕኖውን ጠቁመዋል፡፡

ከተፅዕኖዎች አንዱ  ተየቤተሰብ ፍላጎት እና ጫና ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ሀገራትም ትዳር የሁለት ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን የሁለት ቤተሰቦች ትስስር መሆኑን ባለሙያው ጠቁመዋል። በዚህም ከመጀመሪያው የትዳር አጋር ምርጫ ጣልቃ ገብነት ሊኖር ይችላል፤ ቤተሰብ የአጋርን አስተዳደግ፣ ሃይማኖት ፣ የዘር ሐረግ ወይም የኢኮኖሚ ደረጃ በማየት “ይህ ይሆንሻል/ይሆንሃል” ወይም “ይህ አይሆንህም/ሽም” የሚል ጠንካራ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡

ሌላው ለአቅመ ሔዋን እና ለአቅመ አዳም በደረሱ ወጣቶች ላይ የሚኖር የዕድሜ እና የጊዜ ጫና ነው፡፡ በተለይ ወጣቶች የተወሰነ የዕድሜ ክልል ላይ ሲደረስ “መቼ ነው የምታገቢው?/የምታገባው? የልጅ ልጅ ማየት እንፈልጋለን” የሚሉ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ግለሰቦች ዝግጁ ሳይሆኑ ወደ ትዳር እንዲገቡ ሊያስገድዷቸው የሚችሉ ተጽዕኖዎች እንደሆኑ  አቶ አውግቸው ጠቁመዋል፡፡

የጓደኛ እና የማኅበረሰብ ግፊት ሌላው ችግር  ነው፡፡ ሰው ማኅበራዊ ፍጡር እንደመሆኑ በዙሪያው ያሉ የጓደኞቹ የሕይወት ደረጃዎች በእሱ ውሳኔ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ። ይህም ሲባል የጊዜ መስመር ንፅፅር ይኖራል ያሉት አቶ አውግቸው፤ የቅርብ ጓደኞች በሙሉ ማግባት እና ልጅ መውለድ ሲጀምሩ ብቻውን የቀረው ግለሰብ “ወደ ኋላ ቀረሁ” የሚል የሥነ-ልቦና ስጋት ስለሚያድርበት ብቻ ተስማሚ አጋር ሳይመርጥ እንዲያገባ ሊገፋው ይችላል።

በሌላ በኩል የሰርግ አደረጃጀት ውድድር መኖር በተለይም በዚህ ጊዜ ትልቁ ችግር ጓደኛ ያደረገውን ዓይነት የቅንጦት ሰርግ ለማድረግ መፈለግ እና “ሰዎች ምን ይሉኛል?” የሚለው ፍርሃት ጥንዶች ከአቅማቸው በላይ በሆነ ወጪ ውስጥ እንዲገቡ እና በትዳቸው ጫና እንዲፈጠር ያደርጋል። ባለሙያው እንደሚገልፁት የትዳር ምክር እና ጣልቃ ገብነት መኖር በራሱ ጓደኞቻቸው  ስለ ትዳር ያላቸውን (አንዳንዴ የተሳሳተ ወይም ያልበሰለ) አመለካከት በጥንዶቹ ላይ በመጫን በባልና ሚስት መካከል አላስፈላጊ ጥርጣሬ ወይም ግጭት ሊፈጥሩ ይችላሉ።

ሌላው ችግር ደግሞ ከተጋቡ በኋላ የሚመጣ የኃላፊነት ጫና የራስ አቅምን ሳያገናዝቡ በቤተሰብ ወይም በጓደኛ ግፊት ብቻ ሰርግ ተደርጎ ወደ ትዳር ከተገባ በኋላ  ከሰርግ ማግስት የሚመጡ የዕለት ተዕለት ወጪዎች ጥንዶቹን ለከፋ የዕዳ እና የሥነ-ልቦና ጭንቀት ይዳርጋቸዋል። በተለይም አሁን አሁን ከሽምግልና ጀምሮ የሚፈፀም የተንዛዛ ድግስ  በመስፋፋቱ ያለአግባብ የሚደረጉ ወጪዎች (አላስፈላጊ የቅንጦትና የብክነት ወጪዎች) በትዳር ላይ ከፍተኛ አደጋ እያመጡ ነው። ባለሙያው ተፅዕኖዎችን በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ዘርዝረዋቸዋል፡፡

የኢኮኖሚ ተፅዕኖ

የመጀመሪያው የኢኮኖሚ ተጽዕኖ የዕዳ አዙሪት ነው፤ ከአቅም በላይ ለሰርግ፣ ለሽምግልና… ለቤት ዕቃ ወይም ለይስሙላ ወጪዎች መበደር ጥንዶችን ገና ሳይጀምሩ ዕዳ ውስጥ ይከታል። በእነዚህም ምክንያት የመሠረታዊ ፍላጎቶች መጓደል ይከሰታል፤  ገንዘብ ባልነበረበት ቦታ ላይ ስለሚባክን ለቤት ኪራይ፣ ለምግብ፣ ለሕክምና እና ለሌሎች ወጪ የሚሆን ገንዘብ ያጥራል። ይሄ ደግሞ በትዳር  የወደፊት እቅድ መስተጓጎል፦ ለቁጠባ እና ለኢንቨስትመንት (ቤት መግዛት፣ ንግድ መጀመር) የሚሆን አቅምን ያጠፋል።

የሥነ ልቦና ተፅዕኖ

በመጀመሪያ በተጋቢዎች ላይ የማያቋርጥ ጭንቀት  የገንዘብ ማጣት ስጋት በትዳር አጋሮች ላይ ከፍተኛ የስሜት መረበሽ፣ ድብርት እና እንቅልፍ ማጣት ያስከትላል። ከሰርግ ማግስት ተጋቢዎች የጸጸት እና የንዴት ስሜት ያድርባቸዋል፡፡  “ለምን ይሄን አደረግን?” የሚል የጥፋተኝነት ስሜት እና እርስ በርስ የመወነጃጀል ባሕርይ ይፈጠራል።

ማኅበራዊ ተፅዕኖ

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ በባለትዳሮች መካከል  የማያቋርጥ የቤት ውስጥ ግጭት መኖር እና የገንዘብ እጥረት ለጭቅጭቅ ዋነኛ መንስኤ በመሆን የፍቺ ስጋትን በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል። በዚህም ከቤተሰብና ጓደኞች ጋር መኮራረፍ፣ ለሰርግ ወይም ለቅንጦት የተበደሩትን ገንዘብ በሰዓቱ መመለስ አለመቻል፤ በዚህም  ከቅርብ ሰዎች ጋር መቃቃር ይፈጠራል። ይህን ተከትሎም   ገለልተኝነት ይከሰታል፡፡

ጥንዶቹ በኢኮኖሚ በመዳከማቸው ምክንያት ማኅበራዊ ግዴታዎችን (ዕድር፣ ሰርግ፣ መጠያየቅ) መወጣት አቅቷቸው ራሳቸውን ከማኅበረሰቡ ሊያገለሉ ይችላሉ። በትዳር ውስጥ ፍቅርን እና አንድነትን ጠብቆ ለማቆየት የማያቋርጥ ጥረት እና የጋራ ኃላፊነት እንደ ሚያስፈልግ ባለሙያው አስገንዝበዋል። ትዳር ስኬታማ የሚሆነው ሁለቱም ወገኖች የበኩላቸውን ድርሻ ሲወጡ ብቻ በመሆኑ።

ከእያንዳንዱ አጋር (ከባልም ከሚስትም) ግልጽ እና ጤናማ ግንኙነት ሊኖር ይገባል፡፡

ጥንዶቹ   ስሜትን፣ ፍላጎትን እና ስጋትን ሳይደብቁ በግልጽ መነጋገር ይኖርባቸዋል። ችግሮች ሲፈጠሩም ከመተቻቸት ይልቅ በትዕግሥት ማዳመጥ እና መፍትሔ ላይ ማተኮር ይገባል።

ታማኝነት እና መተማመን በትዳር ውስጥ ትልቁ መሠረት ናቸው። በቃል ኪዳን መጽናት፣ ምስጢር መጠበቅ እና በገንዘብም ሆነ በግል ሕይወት ግልጽ መሆን፣ ይቅር ባይነት እና ተለዋዋጭነት፣ (ፍፁም ሰው የለም።) ስህተቶችን በፍጥነት ይቅር ማለት እና ቂም አለመያዝ እንዲሁም አዳዲስ የሕይወት ለውጦችን (ልጅ መውለድ፣ የሥራ መቀየር) አብሮ መለማመድ ይገባል።

በትዳር  የዕለት ተዕለት አኗኗር ፍቅርን እንዳያቀዘቅዘው እርስ በርስ መተሳሰብ፣ አብሮ ማሳለፍ እና ትናንሽ መልካም ነገሮችን ማድነቅ ተገቢ መሆኑን ባለሙያው ጠቁመዋል። በዚህ ጊዜ ከቤተሰብ እና ከማኅበረሰቡ አዎንታዊ ድጋፍ መስጠት ይጠበቃልለ፡፡ ጥንዶቹ ራሳቸውን እንዲችሉ ማበረታታት እና ሲቸገሩ አቅም በፈቀደ  በምክር መደገፍ አለበት። በተቻለ መጠን ጣልቃ አለመግባት፤ ለአብነት  በባልና ሚስት መካከል በሚፈጠሩ ጥቃቅን ግጭቶች ውስጥ ባለመግባት ራሳቸው እንዲፈቱት ዕድል እና ነፃነት መስጠት ያስፈልጋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ባሕላዊ ጫናዎችን መቀነስ ይገባል፤ “ልጅ መቼ ትወልዳላችሁ? ይህን አድርጉ” የሚሉ ጫናዎችን በማስቀረት የጥንዶቹን የግል ምርጫ ማክበር ይገባል። ይህ ከተደረገ ደግሞ “አብራችሁ አርጁ!” ተብሎ የተመረቀው ትዳር እንደታሰበው ረጅም ዕድሜን እንዲዘልቅ እንደሚያግዝ ባለሙያው አስገንዝበዋል፡

መረጃ

የጋብቻ አፈፃፀም በተሻሻለው የፌዴራል ቤተሰብ ሕግ

ጋብቻ ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን የሚያስከትል እንደመሆኑ ከምስረታው ጀምሮ በሕግ የሚገዛ እና ጥበቃ የሚደረግለት ነው፡፡ ጋብቻ በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ ቀጥተኛ ትርጓሜ ባይሰጠውም ከሕጉ ጠቅላላ መንፈስ መረዳት የሚቻለው አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ሕጋዊ እና ማህበራዊ ተቀባይነት ባለው ሥርአት የሚፈጥሩትን ጥምረት የሚወክል ነው፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት በአንቀፅ 34(3) ቤተሰብ የህብረተስብ የተፈጥሮ መሰረታዊ መነሻ እንደሆነ እና የህብረተሰብ ብሎም የመንግሥትን ጥበቃ የማግኘት መብት እንዳለው ደንግጓል፡፡ ጋብቻም የዚህ ቤተሰባዊ ግንኙነት ዋነኛ መመስረቻ ሥርአት እንደመሆኑ ጥበቃ የሚደረግለት ነው፡፡

በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 1 መሰረት ሦስት አይነት የጋብቻ አፈፃፀም ሥርአቶች አሉ፡፡ እነዚህም በክብር መዝገብ ሹም ፊት ፣ በሃይማኖት እና በባህል ሥርዐት መሰረት የሚፈፀሙ የጋብቻ ሥርዓቶች ናቸው፡፡

ጋብቻው በየትኛውም አይነት አፈፃፀም ሥርአት የሚፈፀም ቢሆንም ከመፈፀሙ በፊት የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላትታቸው መረጋገጥ አለበት፡፡ ጋብቻ በተጋቢዎች ነፃ እና ሙሉ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት፡፡ ይህ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 34(2) እና በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 6 የተቀመጠ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ተጋቢዎች እራሳቸው ፈቃዳቸውን መግለፅ ያለባቸው ሲሆን በማስገደድ፣ በማሳሳት እና በመሳሰሉት መንገዶች ጋብቻው ቢፈፀም እንኳል ሊፀና አይችልም ፡፡

በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 7 መሰረት ወንዱም ሆነ ሴቷ 18 ዓመት ካልሞላቸው ጋብቻ አይፈፅሙም፡፡ ሆኖም ከባድ ምክንያት ባጋጠመ ጊዜ ተጋቢዎቹ ወይም ከተጋቢዎቹ የአንዳቸው ወላጆች ወይም አሳዳሪ ጥያቄ ሲቀርብ ፍትሕ ሚኒሥቴሩ ከመደበኛ የጋብቻ ዕድሜ ከሁለት ዓመት ያልበለጠ ጊዜ ቀንሶ እንዲጋቡ በልዩ ሁኔታ ሊፈቅድ ይችላል፡፡

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here