ተመራማሪዎች ከመካከለኛው የመሬት ክፍል (መንትል) የአለት ንብብሮች ስር ቀልጠው የገገሩ ማእድናት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት ተከማችተው እንደሚገኙ መለየታቸውን ሳይቴክ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
በእንግሊዝ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የምድር ምርምር ትምህርት ክፍል ተመራማሪዎች ዓለም አቀፍ በሆነው ጥናታቸው ከብርቅዬ (ሬር ኧርዝ) ንጥረ ነገሮች ወይም ማእድናት መፈጠር ጀርባ የነበረውን ሂደት ጠቁመው ንድፉን አመላክተዋል፡፡
ተመራማሪዎቹ ከመሬት የላይኛው ገፅ (ክረስት) ስር የሚገኘው መካከለኛው (መንትል) የመሬት ክፍል ለብርቅዬ ማእድናት መበልፀጊያ ምቹ ሁኔታ ያለው መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡ ከውስጠኛው የመሬት ክፍል በሚነሳ መብላላት የቀለጠ አለትን አዳፍኖ በማስቀረት ብርቅዬ ሀብቱ ሊከማችበት መቻሉንም ነው ያብራሩት −በዩኒቨርስቲው የጥናት ምርምሩ መሪ ዶክተር ኢሚሊ ቦውማን፡፡ ብርቅዬ ማእድናቱ ለበርካታ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንደስማርት የምባይል ስልኮች፣ በኤሌከትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች፣ በነፋስ ኃይል ለሚሰሩ “ተርባይኖች” ወዘተ ተፈላጊ ናቸው- ተመራማሪዎቹ እንዳሰፈሩት፡፡
በአሁኑ ወቅት ብርቅዬ የምድር ውስጥ ማእድናት ክምችቶቹን በውል ለመገንዘብ አንድ ሚሊዮን ፓውንድ የተመደበለት ኘሮጀክት ተቀርፆም በኘሮፌሰር ሳሊ ጊብሰን በመመራት ላይ ነው፡፡ ለዚህም ከዓለም ዙሪያ በግምት ዘጠኝ ሺህ የ “ኢግኒየስ” ድንጋይ ከሚካላዊ ናሙናዎች ተሰብስቧል፡፡
የጂኦፊዚክስ ባለሙያዎችን ኘሮፌሰር ሰርጌ ሌቤዴቭ እና ዶክተር ሲዩዋን ሱይንን ያካተተው የምርምር ቡድን የማእድናቱን መገኘት ከምድር ውስጣዊ ይዘት ወይም መዋቅር መረጃ ጋር አጣምረውታል፡፡ ለዚህም የድንጋዮችን ኬሚስትሪ ወይም ስሪት ከምድር ውስጥ እንቅስቃሴ ጋር ማስተሳሰር ግድ እንደሚል ነው ያሰመሩበት፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


