ለድህረ ምርጫው ስኬት ከማን ምን ይጠበቃል?

0
256

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ተካሂዷል፤ ይህን ተከትሎ ታዲያ በየምርጫ ጣቢያዎች የቆጠራ ሂደቱ ተጠናቆ ጊዜያዊ ውጤትን አሳውቀዋል፡፡ የመጨረሻው ውጤት የሚገለጸው ደግሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በድምጽ አሰጣጥ ወቅት የታየው ሰላማዊ ሂደት ከምርጫ ማግስትም (በድህረ ምርጫ) እንዲቀጥል ከማን ምን እንደሚጠበቅ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ሐሳብ ተቀብለናል፡፡

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መራጮች እንደተናገሩት የመጨረሻ ውጤት ይፋ ለማድረግ ሥልጣን ያለው አካል የሚገልጸውን በጸጋ መቀበል ይገባል፤ ይህን መሠረት በማድረግም ለሃገር ልማት በጋራ መሥራት ከሁሉም ይጠበቃል፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪ መራጮች የምርጫ ውጤቱን በጸጋ በመቀበል ለአንዲት ሀገር በጋራ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የምርጫ ውጤቱ ምንም ይሁን በጸጋ በመቀበል የዴሞክራሲ ባሕልን ማሳደግ እና ለሃር ልማት በጋራ መሥራት እንደሚገባም አክለዋል።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት አሸናፊው የፖለቲካ ፓርቲም የሕዝቡን ፍላጎት መሠረት በማድረግ መሥራት ይገባዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ይፋ በሚያደርገው ውጤት መሠረት አሸናፊ ከሆነው ጋር ለሀገር ልማት እንደሚሠሩ የተናሩት ደግሞ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የከሚሴ ከተማ ነዋሪ መራጮች ናቸው።

አሚኮ ያነጋገራቸው የከሚሴ ከተማ ነዋሪዎች ለምርጫው ስኬት የዜግነት ኀላፊነታቸውን መወጣታቸውን እና እንደሚወጡም ጠቅሰዋል።

ምርጫ ቦርድ ይፋ በሚያደርገው ውጤት መሠረት ደግሞ ከሚመሠረተው መንግሥት ጋር ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ አክለዋል።

በተለይ የኑሮ ውድነቱ ነዋሪውን እየፈተነ መሆኑን ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ አሸናፊው ፓርቲ ትኩረት ሊያደርግበት እንደሚገባ ጠይቀዋል።

ለወጣቶች የሥራ ዕድል እና የትምህርት ጥራት ነዋሪዎች ያነሷቸው ተጨማሪ የትኩረት ነጥቦች ናቸው።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በርካታ ነገሮችን ለማከናወን ለሕዝቡ ቃል ይገባሉ። ከምርጫ ማግስት ታዲያ ለቃላቸው ታማኝ በመሆን መፈጸም እንደሚገባቸው መራጮች ጠይቀዋል።

በተመሳሳይ የምርጫ ውጤቱን በጸጋ ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታውቀዋል፤ የአብን ምክትል ሊቀመንበር እና የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ መልካሙ ጸጋዬ በየምርጫ ጣቢያው የተሰማሩት የፓርቲው ታዛቢዎች እና ተወካዮች ሂደቱን በአንክሮ መከታተላቸውንም ጠቁመዋል፤ ማሸነፍም ሆነ መሸነፍ የሚወሰነው በዜጎች ነጻ ድምጽ ብቻ መሆኑን በማንሳት ፓርቲያቸው “ሕዝብ የሚሰጠውን ማንኛውንም የድምጽ ውጤት በታላቅ ጸጋ ለመቀበል ዝግጁ ነው” ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ዕጩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ “ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ሲመርጥ በማየቴ ደስ ብሎኛል። ውጤቱ ምንም ይሁን የአሸናፊውን ድምጽ እናከብራለን፤ ዋና ትኩረታችን ሃገር ግንባታ ላይ ነው” ብለዋል።

የድህረ ምርጫ ወቅት የአንድን ሀገር የዴሞክራሲ ብስለት፣ የተቋማት ጥንካሬ እና የፖለቲካ ባሕል የሚፈተንበት ወሳኝ ጊዜ ነው። የውጤት ማስታወቂያ፣ የአሸናፊነትና የሽንፈት መቀበል፣ የሕዝብ ምላሽ እና የፖለቲካ ተዋናዮች አቋም የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት በእጅጉ ይወስናሉ።

የድህረ ምርጫ ወቅት የሀገር ሰላም፣ መረጋጋትና የዲሞክራሲ ጥንካሬ የሚፈተንበት ምዕራፍ መሆኑን በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕግ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አብዬ ካሳሁን ለበኩር ተናግረዋል።

አቶ አብዬ እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ በድህረ ምርጫ ወቅት ከምርጫ ቦርድ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ ከሚዲያ ተቋማት፣ ከሲቪክ ማኅበራትና ከመራጩ ሕዝብ የሚጠበቁ ግልጽ ኃላፊነቶችን በአዋጅ ቁጥር 1133/2011 አንቀጽ 7 በርካታ ተግባርና ኀላፊነቶችን በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ቀዳሚው ኃላፊነት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው። ቦርዱ ሂደቱን በነፃነት፣ በገለልተኝነትና በግልጽነት የመምራት ግዴታ አለበት። በተለይም የምርጫ ውጤቶች በሕጉ በተወሰነው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ያለምንም መጓተት ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለበት።

የውጤት ማሳወቂያ መዘግየት ወይም ግልጽነት ማጣት የሕዝብ መተማመንን ከመሸርሸር ባለፈ ለብጥብጥና ለግጭት መንስኤ ሊሆን እንደሚችልም አቶ አብዬ ያስረዳሉ። ስለዚህ በየምርጫ ጣቢያው፣ በየምርጫ ክልሉና በሀገር አቀፍ ደረጃ የተገኙ ውጤቶች በወቅቱ ይፋ መደረጋቸው ለሂደቱ ተአማኒነት ወሳኝ ስለመሆኑ አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል የምርጫ ውጤት ከተገለጸ በኋላ ቅሬታዎች መነሳታቸው በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የተለመደ ጉዳይ መሆኑን አቶ አብዬ ተናግረዋል። ቅሬታዎች ደግሞ በሕግ በተዘረጋው አሠራር መሠረት ለተቋቋሙ ቅሬታ ሰሚ አካላት መቅረብ እንዳለባቸው ያሳስባሉ። ምርጫ ቦርድም ቅሬታዎቹን በፍጥነት፣ በገለልተኛነትና በፍትሃዊነት መመርመር እና ውሳኔ መስጠት ይኖርበታል።

እንደ አቶ አብዬ ገለጻ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ዕጩ ተወዳዳሪዎች በድህረ ምርጫ ወቅት በምርጫ ቦርድ የተረጋገጠ የምርጫ ውጤትን በጸጋ መቀበል እንዳለባቸው አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 131 ላይ አስቀምጦታል፡፡ ቅሬታ ካላቸውም የሕግ መንገድን ብቻ በመጠቀም መጠየቅ ይገባል። የሀገርን ሰላም ከፓርቲ ጥቅም በላይ ማስቀደም የሁሉም ፖለቲካዊ ተዋናዮች ቀዳሚ ኃላፊነት መሆን አለበት።

መራጩ ሕዝብና ሲቪክ ማኅበራትም በተመሳሳይ መልኩ ለዲሞክራሲያዊ ሂደቱ ስኬት አስተዋጽኦ አላቸው። ሕዝቡ ድምፁን ከሰጠ በኋላ ውጤት እስኪገለጽ ድረስ በትዕግሥት መጠበቅና የምርጫ ቦርድን ይፋዊ መግለጫዎች መከታተል አለበት። ሲቪክ ማኅበራትና ታዛቢዎች ደግሞ ያዩትን በሚዛናዊነትና በገለልተኛነት ሪፖርት ማድረግ እንጂ ሕዝብን ወደ አላስፈላጊ ውጥረት የሚመሩ መግለጫዎችን ማውጣት አይገባቸውም።

አቶ አብዬ አክለውም  “የምርጫ ቦርድ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ብዙኃን መገናኛዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ሕዝቡና መንግሥት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሲወጡ ሀገሪቱ ከአንድ የፖለቲካ ምዕራፍ ወደ ሌላው በሰላምና በመረጋጋት መሸጋገር ትችላለች” ብለዋል።

ደሳለኝ የሻንበል (ዶ/ር) በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መምህር ናቸው፤ መምህሩ ለበኩር እንደተናገሩት በድህረ ምርጫ ወቅት ትልቁ ኃላፊነት የሚጠበቀው ከመንግሥት ነው። ምርጫው በምንም አይነት ውጤት ቢጠናቀቅም መንግሥት የዜጎችን ሰላም፣ ደህንነት እና መብት ለማስጠበቅ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። የዜጎች ደህንነት በማረጋገጥ በትምህርት፣ በግብርና፣ በንግድና በሌሎች የልማት ዘርፎች ውጤታማ ተሳትፎ በመፍጠር ለሀገር ዕድገት መሠረት መሆን እንደሚገባም ገልጸዋል።

ከመንግሥት በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በድህረ ምርጫ ወቅት ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው። ዶ/ር ደሳለኝ እንደሚሉት የምርጫ ውጤት ፍትሐዊ ነው ወይም አይደለም በሚል ቅሬታ ቢኖርም የፖለቲካ ፓርቲዎች ውጤቱን በጸጋ መቀበል እና ቅሬታቸውን በሕጋዊና በተቋማዊ መንገድ ለምርጫ ቦርድ ማቅረብ ይገባቸዋል። ደጋፊዎቻቸውን ወደ ግጭት የሚመሩ መግለጫዎችን ከመስጠት መቆጠብ እና የሕዝብን ሰላም ማስቀደም እንዳለባቸውም አስረድተዋል።

“አሸናፊ ፓርቲዎች ድላቸውን በትህትና ሲቀበሉ፣ ተሸናፊ ፓርቲዎች ደግሞ የሕግ አግባብን በመከተል የዴሞክራሲ ባሕልን ማጠናከር ይገባቸዋል” ብለዋል።

በዚህ ሂደት የዜጎች ሚናም እጅግ ወሳኝ ነው። ዜጎች ውጤቱ ከግል ፍላጎታቸው ጋር ባይጣጣምም የሕግ የበላይነትን ማክበር እና የምርጫ ውጤትን በሰላማዊ መንገድ መቀበል አለባቸው። በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ እየተስፋፉ የሚገኙ ያልተረጋገጡ መረጃዎች፣ የሐሰት ወሬዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ግጭትን ሊያባብሱ ስለሚችሉ ከእነዚህ መራቅ ይገባል።

ማሕበረሰቡ በአካባቢው ሰላም ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ወደ ሁከትና ብጥብጥ የሚያመሩ አካላትን በማግባባትና በመምከር የራሱን ድርሻ መወጣት እንደሚኖርበትም አስገንዝበዋል።

በድህረ ምርጫ ወቅት የብዙኃን መገናኛዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ደሳለኝ የሕዝብን አመለካከት በመቅረጽ እና የሰላም ወይም የግጭት አቅጣጫን በመወሰን ትልቅ ተፅዕኖ ያላቸው ተቋማት ናቸው። ስለዚህ ዋና ኃላፊነታቸው ትክክለኛ፣ ሚዛናዊ እና የተረጋገጠ መረጃ ለሕዝብ ማቅረብ መሆን አለበት። የምርጫ ውጤቶችን ሲዘግቡ ያልተረጋገጡ ወሬዎችን ከማሰራጨት መቆጠብ፣ የተለያዩ አመለካከቶችን በእኩልነት ማቅረብ እና የሰላምና የውይይት መድረክ መሆን አለባቸው።

ከዚህ በተጨማሪ የምርጫ ሂደቶችን፣ የቅሬታ አፈታት ሥርዓቶችን እና የመንግሥት እርምጃዎችን በገለልተኛነት በመከታተል የሕዝብ እምነት በተቋማት ላይ እንዲጠናከር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ የሻንበል በመጨረሻ መልዕክታቸው እንዳሉት ፓርቲዎች ይመጣሉ ይሄዳሉ፤ ሀገር ግን ትቀጥላለች። ስለዚህ ሁሉም አካላት የሀገርን ህልውና፣ ሰላምና አንድነት በማስቀደም የድህረ ምርጫ ሂደቱን በሰከነ እና በሕጋዊ መንገድ ማስቀጠል ይገባቸዋል።

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የሰኔ 1   ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here