አህጉርም፣ ሀገርም ናት፤ በሀገሪቱ ውስጥ ካለው የሰዎች ቁጥር ይልቅ የካንጋሮዎች ቁጥር በእጥፍ ይበልጣል፤ በውስጧ ከ10 ሺህ በላይ የባህር ዳርቻዎች አሏት፤ አንድ ሰው በየቀኑ እነዚህን የባህር ዳርቻዎች ቢጎበኝ ከ27 ዓመታት በላይ ይፈጅበታል። በዓለም ላይ ካሉት እጅግ መርዛማ የሆኑ 25 የእባብ ዝርያዎች መካከል 21ዱን በውስጧ ይዛለች- አውስትራሊያ፡፡
አውስትራሊያ በደቡባዊው ንፍቀ ክበብ ትገኛለች፡፡ ይህች አህጉር ብቻዋን ሀገር የሆነች ታላቅ ምድር ናት፡፡ በዙሪያዋ ባሉ ሰማያዊ ውቅያኖሶች ተከባ ከየትኛውም ሀገር ጋር የማትጋራው ለየት ያለ ማንነት እና ተፈጥሮ አላት፡፡ የሀገሪቱ ዋና ከተማ ካንቤራ ትባላለች፡፡
ዋና ከተማዋ የተመሰረተችው በሲድኒ እና በሜልቦርን ከተሞች መካከል የነበረውን የዋና ከተማነት ውዝግብ ለመፍታት ታስቦ ነው፡፡
አውስትራሊያ በዓለም ላይ በቆዳ ስፋቷ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
አሁን ላይ የሀገሪቱ የሕዝብ ብዛት ወደ 28 ሚሊዮን ይጠጋል፡፡ ይህ ቁጥር ከሀገሪቱ የቆዳ ስፋት ጋር ሲነፃፀር በዓለም ላይ እጅግ አነስተኛ የሕዝብ ጥግግት ካላቸው ሀገራት አንዷ ያደርጋታል፡፡ የአገሬው ተወላጆች ወይም አቦርጂናውያን ይባላሉ፤ ከ65 ሺህ ዓመታት በላይ በአውስትራሊያ ምድር እንደኖሩም ይነገርላቸዋል፡፡ ጥንታዊ እና ጥልቅ ባህል እንዳላቸውም የአውስትራሊያ ዶት ኮም መረጃ ያትታል፡፡ የአገሬው ተወላጆች ሕዝብ (አቦርጂናውያን) በምድር ላይ ካሉ ጥንታዊ እና የማይበረዝ እና የጠራ ባህል ካላቸው ሕዝቦች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
አቦርጂናውያን ከምድር እና ከተፈጥሮ ጋር ያላቸው መንፈሳዊ ትስስር፣ በሙዚቃዎቻቸው እና በድንጋይ ላይ በሚስሏቸው ስዕሎች ዛሬም ድረስ የአውስትራሊያ ትልቅ ኩራት ሆኖ ቀጥለዋል፡፡የአውስትራሊያ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ የሚኖረው ከባህር ዳርቻ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ባሉ ከተሞች ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የሀገሪቱ የመሀለኛው ክፍል ሰው የማይኖርበት ምድረ በዳ መሆኑን የአውስታራሊያ ዶት ኮም መረጃ ያስረዳል፡፡ሰፊ ውቅያኖሶችን ተሻግሮ ለሚመጣ እንግዳ አስገራሚ የተፈጥሮ ምስጢራትን፣ ዘመናዊ የከተማ ህይወትን እና ጥንታዊ ታሪኮችን በአንድ ላይ አጣምራ የምታሳይ አስደናቂ ምድር አላት፡፡
የቀዘቀዘ ምድሯን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚረግጥ ሰው የሚሰማው የመጀመሪያው ስሜት ነፃነት እና የተረጋጋ መንፈስ መሆኑን ብሪታኒካ ዶት ኮም ያበስራል። ምንም እንኳ ከጫፍ እስከ ጫፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ካሬ ኪሎ ሜትሮች የተንጣለለ ሜዳ ቢሆንም አብዛኛው ሕዝቧ የሚኖረው ውብ በሆኑት የባህር ዳርቻዎቿ ነው፡፡ ተፈጥሮ አብዝቶ የባረካት ይህች ሀገር ካንጋሮ፣ ኮአላ እና ፕላቲፐስን የሚባሉ በሌላው የዓለም ክፍል የማይገኙ ልዩ ፍጥረታት መኖሪያ ናት፡፡
የሕዝቦቿ የዕለት ተዕለት አኗኗር እጅግ የተረጋጋ፣ ዘና ያለ እና ከጭንቀት የራቀ ነው፤ ኑሮውም ከተፈጥሮ ጋር የተቆራኘ ነው፤ ጠዋት በጠራራ ፀሐይ መሮጥ፣ በባህር ዳርቻ ላይ ቡና እየጠጡ መዝናናት እና ቅዳሜና እሁድን በዱር እንስሳት መሀል በድንኳን ማሳለፍ የአውስትራሊያዊያን ከደማቸው ጋር የተዋሀዶ የህይወት ዘይቤ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ከሥራ በኋላ ወደ ባህር ዳርቻዎች በመሄድ በማዕበል ላይ በመንሸራተት ወይም በከተማ መናፈሻዎች ውስጥ ከቤተሰብ እና ከጓደኛ ጋር ማሳለፍ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ይህም አውስትራሊያን በዓለማችን ላይ ለመኖር ከሚያስደስቱ ቀዳሚ ሀገራት መካከል አንዷ እንድትሆን አድርጓታል።
በበአውስትራሊያ ምድር ሥራ እጅግ የተከበረ ባህል ነው፤ አብዛኛው ሕዝብ (ከ75 በመቶ) በላይ የሚሆነው የተሰማራው በአገልግሎት ሰጭ ዘርፎች ላይ ሲሆን በገጠራማው የሀገሪቱ ክፍል ደግሞ በከብት እርባታ እና በግብርና ሥራ ነው፡፡
በአውስትራሊያ የሚገኘው አና ክሪክ የተባለው የከብት እርባታ መሬት ከእስራኤል ወይም ከቤልጂየም የበለጠ ስፋት አለው፡፡
ይህ የእርሻ ቦታ በዓለም ላይ በስፋቱ በቀዳሚነት ይቀመጣል፡፡ ለኑሮ ምቹ የሆነችዋ አውስትራሊያ በዓለም ላይ ካሉ ስደተኞች በተድላ ከሚኖሩባቸው ሀገራት አንዷ ናት፤ ከጠቅላላው ሕዝቧ ከ32 በመቶ በላይ የሚሆነው ከአውስትራሊያ ውጪ የተወለደ ነው፡፡ በአውስትራሊያ የህንድ፣ የእንግሊዝ፣ የቻይና፣ የኒውዚላንድ፣ እና የፊሊፒንስ፣ የቪየትናም፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የጣሊያን፣ የማሌዢያ እና ከተለያዩ የአውሮፓ እና እስያ ሀገራት የመጡ ሕዝቦች ይኖሩባታል፡፡ የዘር ሀረጋቸው ከኢትዮጵያ የሚመዘዝ ከ17 ሺህ ዜጎችም በተቀደሰችዋ ሀገር እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ሁሉም ሰው ምንም ዓይነት የዘር፣ የሃይማኖት ወይም የኢኮኖሚ ደረጃ ሳይለየው እየኖረ ይገኛል፡፡
አውስትራሊያ በዓለማችን ላይ ካሉ እጅግ ባለጸጋ እና የተረጋጉ ሀገራት አንዷ ስትሆን የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀሟ እና የቴክኖሎጂ ምጥቀቷ ኢትዮጵያን የመሰሉ ደሃ ሀገራትን ያስቀናል፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የዱር ግመሎች ይገኛሉ፡፡ ያላትን የግመል ሀብትም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በመላክ ቀዳሚ መሆኗንም መረጃው ይነግረናል፡፡
በከተሞች ውስጥ ያለው ንፅህና፣ ሰላም እና ደህንነት እንዲሁም የሰዎች እርስ በእርስ መከባበር ለማንኛውም ጎብኚ አገሪቱን ሁለተኛ ቤቱ አድርጎ እንዲመለከታት የሚያደርግ ነው፡፡ ሀገሪቱ ያሏት ልዩ ልዩ የመስህብ ስፍራዎች በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ይስባሉ። ታዋቂው የሲድኒ ኦፔራ ሃውስ በውብ የባህር ወሽመጥ ላይ ተቀምጦ የህንፃ ጥበብን ልዕልና ያሳያል፡፡ በአቅራቢያው ያለው የሃርበር ድልድይ ደግሞ የከተማዋን ውበት ያጎላል። የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት በከፍተኛ ደረጃ ከሚታወቅባቸው ሀገራት መካከልም አንዷ ናት- አውስታራሊያ፡፡በአውስትራሊያ የሚገኘው አስደናቂው የኮራል ንጣፍ ከህዋ ላይ በግልፅ የሚታይ በዓለማችን ላይ ትልቁ የተፈጥሮ ውበት ነው፡፡ ከአውስትራሊያ የዱር እንስሳት እና እፅዋት መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በዚህች ሀገር ብቻ የሚገኙ እና በሌላ የትኛውም የዓለም ክፍል የማይገኙ ናቸው፡፡ በዓለም ላይ እጅግ ንፁህ ከሆነው አየር የአውስትራሊያ ቀዳሚ ነው፤ በታስማንያ ደሴት ላይ የሚገኘው አየር በዓለማችን ላይ ንፁህ ተብሎ እንደተመዘገበ ብሪታኒካ ዶት ኮም ላይ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ጠንካራ መንግሥት፣ አስደናቂ የጤና እና የትምህርት ስርዓት መኖሩ የዜጎችን ማህበራዊ ዋስትና አስተማማኝ አድርጎታል፡፡ ሀገሪቱ በዲሞክራሲያዊ እና በተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓቷ ትታወቃለች፡፡ ይህም የሕግ የበላይነት፣ የፕሬስ ነፃነት እና የሰብአዊ መብቶች መከበር በከፍተኛ ደረጃ የተረጋገጡባት ምድር መሆኗን ዓለም ይመሰክርላታል፡፡ አንዴ የጎበኛት ሰው ሁልጊዜ በናፍቆት የሚያስታውሳት ድንቅ የምድር ገነት ሀገርም፣ አህጉርም ናት።
አጫር እዉነታ
አውስትራሊያ
የአውስትራሊያ ተራሮች ከስዊዘርላንድ የበለጠ የበረዶ ሽፋን አላቸው፡፡
ሜልቦርን ከተማ ከግሪኳ አቴንስ ቀጥላ ከፍተኛው የግሪክ ተወላጆች የሚኖሩባት ከተማ ናት፡፡
በአውስትራሊያ በርካታ አስገራሚ የሮዝ ቀለም ያላቸው ሀይቆች ይገኛሉ፡፡
በአውስትራሊያ የሚገኘው የዲንጎ አጥር ከአምስት ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ይረዝማል፡፡ አጥሩ የተገነባው የጎዳና ውሾች ወደ ለም የእርሻ መሬቶች እንዳይገቡ ለመከላከል ታስቦ ነው፡፡
አውስትራሊያ አረንጓዴማ ብትመስልም 70 በመቶ የሚሆነው መሬቷ ደረቅ ወይም ከፊል በረሃማ (Outback) ነው፡፡ የበረሃ ክልሏ ስፋት ከሳውዲ አረቢያ አጠቃላይ ስፋት ጋር እኩል ነው፡፡
የአውስትራሊያ ቀደምት ነዋሪዎች (አቦርጂናውያን) ባህል ከ65 ሺህ ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ ናቸው፡፡
በአገሪቱ ውስጥ ያለው የበግ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ከሕዝቡ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ይበልጣል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለእያንዳንዱ አውስትራሊያዊ ዜጋ በአማካይ ስድስት በጎች ይደርሳቸዋል፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


