ባላገር ናፋቂው

0
10

የጋራ የዘመን ውክልናዎች ባለፉት ዓመታት እያለፉ ነው፡፡ ቀደምት የምንላቸው ኪነ ጥበበኞች እያለፉ ነው፡፡ በ1930 እና 40ዎቹ የተወለዱ የሀገር ባለውለታዎች ጥቂት ናቸው በሕይወት የቀሩት፡፡ የትውልድ ምልክቶች እያለፉ ነው፡፡

ዓለም ግን ምልክት አታጣምና ትተካለች፡፡

አንዱ በሌላ የተተካ ቢመስልም እኩል ግን አይደለም፡፡ ጥላሁን ገሠሠን፣ ብዙነሽ በቀለን፣ ሙሉቀን መለሰን፣ ሒሩት በቀለን፣ ሽሽግ ቸኮልን፣ ማዲንጎ አፈወርቅን ማን ተካቸው የሚለው ጉልህ ጥያቄ ነው፡፡የባህል ሙዚቃ አምባሰደሩን ሰማኸኝ በለውን ሰሞኑን በተወለደ በ58 ዓመቱ አጥተነዋል፡፡ የሰማኸኝ ማለፍ በባህል ሙዚቃችን፣ የታሪክ እና ጥበባዊ ውክልናችን ላይ የሚያጎድለው አለ፡፡ ሙዚቃ ረቂቅ ኃይል ነው፡፡ በአንቱየዋ፣ ባላገር፣ እንጃ፣ ደቦት እንስራ፣ አውዳመት፣ በላይ ዘለቀ፣ ዙማዋ፣ ማር አለሽ፣ እንዴት ነሽ፣ በዝናቡን እና ሌሎች ሙዚቃዎች የጋራ ሐሳቦችን  ወክሎ አስቀምጠዋል፡፡ግንስ ምን ማድረግ ይቻላል? ሞት አይደል፡፡ሞት ቆሞ አያውቅም፡፡ አመጣጡም አዲስ ነው፡፡ የሰው ልጅ መጠርያው የተለያየ ነው፡፡ ፈላስፋው አርተር ሾፐንሀወር ዓለምን በጨለምተኝነት በማየት በኩል ቀዳሚ ነው፡፡

የሰው ልጅ ፍላጎቶች ማለቂያ የላቸውም፡፡

አንዱ ሲሟላ ሌላው ስለሚተካ ህይወት በዋነኛነት በረሃብ፣ በእጥረት እና በውጥረት የተሞላች ናት ይላል፡፡ ህይወትንም “እጅግ የከፋ ዓለም” በማለት ይገልጻታል፡፡ በዚህም መኖር ስቃይ ነው ይላል፡፡ እናም ሾፐንሃወር ሞትን የህይወት የመጨረሻ ግብ እና አላማ አድርጎ ይመለከተዋል፡፡ ህይወት ራሱ የማያቋርጥ የሞት ሂደት እንደሆነ ይከራከራል፡፡ ሞትን ሙሉ በሙሉ እንደ መጥፋት ወይም መደምሰስ አድርጎ አይመለከተውም፡፡ ይልቁንም ሞት የግለሰቡን “የመኖር ፍላጎት” የሚገታበት፣ የሰው ልጅ ከዚህ ማለቂያ ከሌለው የፍላጎት እና የስቃይ ዑደት የሚገላገልበት መንገድ ነው ብሎ ያምናል፡፡ምንም እንኳን ጨለምተኛ  ፈላስፋ ቢባልም ስለ ሞት ያለው አስተሳሰብ አንዳንዴ አጽናኝ ነው፡፡ ሞትን እንደ መጥፎ ነገር ከመፍራት ይልቅ ከህይወት የስቃይ ዑደት የሚገላግል እንደ ወዳጅ ሊታይ ይገባል ብሏል፡፡ሾፐንሃወር ህይወትን እንደ ስቃይና ማለቂያ እንደሌለው ፍላጎት ሞትን ደግሞ ከዚህ ሁሉ ስቃይ የሚገላግል እንደ ተፈጥሯዊ  የህይወት  መቋጫ አድርጎ ይገልጸዋል፡፡

ከዚሁ በተቃራኒ ደግሞ አብዘርዲዝም የሚባል ፍልስፍና አለ፡፡ ሕይወት ከባድ ቢሆንም መልካም ትርጉም የሚፈጥረው የሰው ልጅ ነው የሚል ነው፡፡ አልበርት ካሙስ የዚህ ሀሳብ መስራች ነው፡፡ህይወት ትርጉም አልባ መሆኗን መቀበል ነገር ግን በዚያ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ህይወትን    በመታገል በደስታ መኖር ማለት ነው፡፡

ዝነኞች ቢያልፉም አይሞቱም የሚባለው በስራዎቻቸው ሕያው ሆነው ስለሚኖሩ ነው፡፡ በዘፈኖቻቸው አብረው ከትውልድ ጋር የሚጓዙ ኪነ ጥበበኞች የታደሉ ናቸው፡፡ ሰማኸኝ በለው ከእነዚህ ዕድለኞች አንዱ ሆኗል፡፡ አውዳመት ሲመጣ፣ መስቀል በዓል ሲቃረብ፣ የበላይ ዘለቀ ዘፈን ሲደመጥ፣ መገን ወሎ ሲዜም፣ የምንጃር ዜማው ሲደመጥ፣ ዝናቡን ዘፈን ሲሰማ፣ ባላገር የሚለው ዘፈኑ ሲደመጥ፣ ዓባይ የሚለው ዘፈኑ የተከፈተ ዕለት፣ ዓለም እንደምነሽ ሲከፈት፣ ማር አለሽ ሲሰማ፣ ብራ ነው ሲሰማ፣ ሸጌ ስራ ሲደመጥ ሰማኸኝ እንደ አዲስ በትውልድ ውስጥ ይኖራል፡፡ሰማኸኝ ዛሬ ላይ የሄደበትን የዘላለም እረፍት ሞትን ዓለም እንደምነሽ በሚለው ዘፈኑ ገልጾት ነበር፡፡“ቶሎ ቶሎ በሉ እርቅ ይውረድ አሁን

ኋላ ከቀረማ ደመና እንዳይሆን

አንድ እንኳን የለበት የሁለት ሽራፊ

አሁን የት ይገኛል እንደሞት ቀጣፊ”

ሰማኸኝ ሞትን የገለጸበት ሌላም ዘፈን አለው፡፡ ምድር በሚለው ዘፈኑ መሞት ምን አይነት ከባድ አይቀሬ እጣ መሆኑን አዚሟል፡፡

“ቢከሰስ አንድ ቀን ምድር

ከችሎት ማን ይቀር ነበር

ሰው ሁሉ በርስቱ ይጨርሳል ሀብቱን

የኋላ የኋላ ላያጣው መሬቱን

እስኪ ምን ያጣላል በመሬት ጉዳይ

ሁሉ ዘር ሲጠፋ ይቀር የለም ወይ

ልብስህ ጭቃ ነካ ብለው ነገሩኝ

የኋላ የኋላ ሊረጋግጡኝ”

ሰዎች በመሬት እና በቁሳዊ ንብረት ላይ የሚያደርጉት ክርክር፣ ጠብና ግጭት በሞት ቀን ፊት ለፊት በሚቆምበት ጊዜ ማን ይጸድቃል? ማንም! ሞት የማይቀር የእኩልነት መለኪያ መሆኑን እና በዚያ ቀን የሰው ልጅ ምድራዊ ክርክሩ ሁሉ ትርጉም እንደሌለው አዚሟል፡፡ሰዎች ህይወታቸውን በሙሉ የሚያጠፉት መሬት ለመሰብሰብ፣ ንብረት ለማፍራት እና በርስታቸው ለመኩራራት ነው። ነገር ግን በህይወት ዘመናቸው የደከሙበት መሬት የኋላ ኋላ በሞት ጊዜ እንደማይከተላቸው ይልቁንም እነርሱ መሬቱን እንደሚለቁት ዘፍኗል፡፡ መሬት ለሰው እንጂ ሰው ለመሬቱ ባለቤት እንዳልሆነ ይልቁንም መሬቱ ሰውን እንጂ ሰው መሬቱን መቼም መያዝ እንደማይችል በሙዚቃዎቹ አሳይቷል፡፡ሰዎች ስለ “ልብስ” ወይም ስለ ውጫዊ ገጽታ ስላቅ ወይም ስለ ትንሽ ነገር ሲጨቃጨቁና ሲያሙ (ጭቃ ነካህ ብለው) የህይወትን ትልቅ ዋጋ ይረሳሉ፡፡ “የኋላ ኋላ ሊረጋግጡኝ” ሲል ደግሞ ሰዎች መጨረሻቸው አንድ መሆኑን (ወደ መሬት መውረድ፣ አፈር መሆን) እየረሱ ለነገሮች ምን ያህል እንደሚባክኑ በምፀት ይገልጻል፡፡ሰማኸኝ ምድርን ይጠይቃል፡፡ ጥያቄው ግን መልስ አልባ ነው፡፡ ክፉ እያለ ደግን  ለምን ትወስዳለህ የሚል ነው፡፡ አብልቶ አጠጥቶ መልሶ የሚከዳ እንደ ምድር ባዳ የለም ብሎ ይብከነከናል፡፡

“ሰላም አሳድረኝ ማለቱን ረስቶ

ነገ እንድንገናኝ ይላል ድግስ ጠርቶ

ድሮማ ጥንትማ ሞት ያስደነግጣል

አሁን በኀዘን ቤት ቁማር ያጫውታል

አሁን በኀዘን ቤት ካርታ ያጫውታል”

እነዚህ ስንኞች የሰውን ልጅ የዋህነት ያሳያሉ፡፡ ጠባቂ የሌለው፣ ከንቱ እና ድንገት ተሰባሪነቱን ያሳያሉ፡፡ የበዓል ሊታረድ ቀርቦ ጨፌ እንደሚበላ በግ፣ ፍየል ወይም በሬ ከሞት ዳር ቆሞ የሚኖር የሚመስለው የሰውን ልጅ አሳዛኝ እጣ ያመለክታል፡፡ ሰው ሞተ ማለት በቃ ተከተተ ነው፡፡ ማንም ዘላለም የሚያዝን የለም፡፡ ሕይወት ይቀጥላል፡፡ ዛሬ በእሱ ኀዘን ቤት ውስጥ ካርታ የሚጫዎቱ ሰዎችን ቀና ብሎ ቢያያቸው ምን ይል?

ሰማኸኝ በለው በርግጥም የባህል ሙዚቃ አምባሳደር ነበር፡፡ ሥራዎቹ ይህን የሚናገሩ ናቸው፡፡ በባህርዳር ከተማ ተወልዶ አድጓል፡፡ ልቡ እና ዘፈኑ ግን የገጠሩን ማህበረሰብ የሚገልጽ ነው፡፡ ተወዳጅ የሙዚቃ ሥራዎች ያሉት ዘፋኝ ነው፡፡ የሙዚቃ ጅማሮው በግሽ ዓባይ የባህል ኪነት ቡድን ነው፡፡ አንቱየዋ፣ ባላገር፣ እንጃ፣ ደቦት እንስራ፣ አውዳመት፣ በላይ ዘለቀ፣ዙማዋ፣ ማር አለሽ፣ እንዴት ነሽ፣ ዝናቡን እና ሌሎች ዘፈኖቹ ይወደዱለታል፡፡ አለባበሱ የባላገሩን እሴት የጠበቀ፣ እስክስታው እና ዘፈኑ በርግጥም የባህል አምባሳደርነቱን የሚያሳዩ ነበሩ፡፡ ዘመናዊነት ወደ ገጠር የገፋውን ቁምጣ እና አለባበስ ለብሶ አሜሪካ እና ሌሎች ሀገራት ባላገርን ከፍ አድርጓል።

ቀልድ እና ጨዋታ የሚደምቅለት ዘፋኝ ነው፡፡ ከስድስት ዓመታት በፊት ከአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ጋር በነበረው ቆይታ “ሁለት አልበሞችን አዘጋጅቻለሁ የገበያው ሁኔታ እስኪስተካከል እጠብቃለሁ” ብሎ ነበር፡፡ ግን ሁሉም በቀጠሮ አልተገኘም፡፡ ነጻነት ወደ ሄደበት አይቀሬ ሞት ተጓዘ፡፡ሰባት የሙዚቃ አልበሞች በግሉ ሰርቷል፡፡ ከሀያ በላይ ነጠላ ዜማዎች አሉት፡፡ ከሌሎች ዘፋኞች ጋር ስድስት የሙዚቃ አልበሞችን ሰርቷል፡፡ በግሉ ምሽት ክለብ ከፍቶ የባህል ሙዚቃን ለአፍቃሪያን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ በኋላም ከሀገር ውጪም በመዘዋወር ባህላዊ የሙዚቃ ስራውን አቅርቧል፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በሱዳን፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ አቡዳቢ፣ ዱባይ፣ ባህሬን፣ ሊባኖስ፣ እስራኤል፣ ስዊዘርላንድ፣ ስዊድን፣ አሜሪካ እና ሌሎችም ሀገራት በመዘዋወር አስተዋውቋል፡፡ “እጅግ በጣም የማደላው ግን ለባህሉ ነው፡፡ ባህሉን በጣም እወዳለሁ፡፡ ምክንያቱም ዓይኔ የሚናፍቀው የውሃ ድምጽ፣ የጅረት ድምጽ፣ እንሰራ በጀርባ አድርጋ የምትሄድ ልጃገረድ፣ ሞፈር ቀንበሩን ትክሻው ላይ አድርጎ እያፏጨ በሮቹን ድምጽ እያሰማ እያፏጨ በጣም እያንጎራጎረ የሚሄድ ኮበሌ፣ እንደዚህ አይነት ነገር ነው የሚታየኝ ሁልጊዜ ለኔ” ሰማኸኝ በለው በ1997 ዓ.ም ከተዋናይት መስታውት አራጋው ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ የተናገረው ነበር፡፡የሰማኸኝ የሙዚቃ ወዳጅነት በቀላሉ የተገኝ አልነበረም፡፡ ከቀበሌ ኪነት ጀምሮ ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ያደገ ነው፡፡ ሰማኸኝ ሙዚቃ የጀመረው በባህርዳር ታዳጊ ህፃናት ውስጥ ነው፡፡

በልጅነቱ ለሙዚቃው የነበረው ፍቅር የተለየ ነበር፡፡ ትምህርት ቤት ሲሄድ ደብተሩን በጉያው ሸጉጦ አዲስ የሙዚቃ ካሴት ወጣ ከተባለ ፖስተሩን ለማየት የሚቀድመው አልነበረም፡፡ ወደ ሙዚቃ ቤት ሄዶ ይቆምና  ያዳምጣል፡፡ ያን ዘፈን ወዲያው ትምህርት ቤት ገብቶ ለጓደኞቹ ይዘፍንላቸዋል፡፡ በ1974 ዓ.ም የ14 አመት ልጅ ሆኖ ነው ወደ ሙዚቃው ገባ፡፡ ዘፈን የጀመረውም ታዳጊ ህፃናት ክፍል ውስጥ ነው፡፡ በ1978 ህዳር 11 ቀን ግሽ ዓባይ ኪነትን በ18 ዓመቱ በውድድር አሸንፎ  ተቀላቀለ፡፡

ድምጻዊ ሰማኸኝ በለው ከአባቱ ከአቶ በለው ሹሜና ከእናቱ ከወይዘሮ እናትነሽ ቢልልኝ መስከረም 17 ቀን 1960 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ተወለደ፡፡  የባላገር ፍቅር የሚል ቴያትርም ተጫውቷል፡፡ ባደረበት ድንገተኛ ህመም በህክምና ሲረዳ የቆየው ድምጻዊው ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም  በ58 ዓመቱ አልፏል፡፡ በሙዚቃዎቹ ከትውልድ ልቦና ጋር አብሮ ይቀጥላል።ባለ ትዳርና የአራት ልጆች አባትም ነበር፡፡

 

ማረፊያ

አለማየሁ እሸቴ

ሴት ያሳደገው ልጅ ከመባል ዘወትር

ለማኝ ሆኖ አባቴ ባይጠቅመኝም ይሁር

ስድ አደግ ባለጌ ቁንጥጫ ያላየው

የሚባለው ስድብ አባት ከሞተ ነው

ሌባ ወሮ በላ ቀማኛ ዱርየ

ስራ ፈት ወስላታ ዟሪ ነው ተብየ

ቁጥጥር ግልምጫ ፍጹም ያልጎበኘው

የሚባለው ስድብ አባት ኮሞተ ነው

ራሴን እስክችል የዓይኔ ብርሀን ነው

የመኖር ትንፋሼ ሕይወቴ አባቴ ነው

ባይጠቅመኝ ባይረዳኝ ባያንቀባርረኝ

ለማኝ ሆኖ ይኑር አባት አለው ልሰኝ

እጅ እግሩ ተቆርጦ አከላቱ ጎድሎ

ይኑር አባብየ እየበላን ቆሎ

44ቱን ታቦት ጠርቶና ለምኖ

ኮቾሮ ተለጋሽ አሩግ ለማኝ ሆኖ

አባት ካለህ አጊጥ ጀምበር ካለች ሩጥ

የተባለው ፈሊጥ አይደለም ለፈሊጥ፡፡

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሰኔ 15  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here