ከራስህ ጋር ታረቅ

0
141

ሕይወት ነውና የመጣንበት መንገድ ውጤት ነን። ቤተሰብ፣ አካባቢ፣ ትምህርት፣ ሥራ ቦታ፣ ፓለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ መዝናኛ፣ ሃይማኖት እና ሌሎችም ማንነታችንን ይቀርጹታል።

ስለት መሆን የሚገባው ማንነታችን ዶማ፣ ጠንካራ መሆን የሚገባው ሰብዕናችን ልፍስፍስ፣ ጠቢብ መሆን የሚገባው አዕምሯችን ደደብ ይሆናል።

የአንበሳ ጉልበት ይዘን ተፈጥረን አንደ በግ እየኖርን ሊሆን ይችላል። በአንዲት አጋጣሚ የደረሰበት አደጋ፣ መለያየት፣ ችግር፣ ርሀብ፣ ስደት፣ ግርፊያ የሕይወት ዕይታችንን በአሉታዊነት ለውጦት ሊሆን ይችላል።

ስኬታማ ሆነው ዛሬም ድህነት ውስጥ ያሉ፣ ምሁር ሆነው ዛሬም ድንቁርና ውስጥ ያሉ፣ ሉዓላዊ ሆነው ዛሬም ቅኝ ግዞት ውስጥ ያሉ ሰዎችን እናያለን። ይህ ከድሮ ማንነት ጋር ያለመታረቅ ውጤት ነው። ያ ነገር አርጅቶ እንደተጣለው የልጅነት ልብሳችን መረሳት ነበረበት።

ሰው መሆን ረጅም ጉዞ ነው። በዚህ ጉዞ ውስጥ አንዳንዴ ራሳችንን እናጣዋለን። አንዳንዴ ካለፈው ስህተታችን ጋር እንላተማለን። ሌላ ጊዜ ደግሞ ስለ ነገው ባዕድነት እንሰጋለን።

ይሁን እንጂ የሰው ልጅ እውነተኛ ስኬት የሚጀምረው ከቁሳዊ ብልጽግና ሳይሆን ከውስጣዊ ዕርቅ ነው። ከማንነት ጋር መታረቅ ማለት ራስን እንደ ሁኔታው ሳይሆን እንደ ምንነቱ መቀበል ማለት ነው።

በልጅነትህ ደሀ ነበርህ። ዛሬ ግን ሀብታም ነህ። ደህነት አሁን የአንተ መታወቂያ አይደለም። ብዙዎቻችን የምንኖረው ሌሎች እንዲሆኑልን የሚፈልጉትን ማንነት ተከናንበን ነው። ይህ ሐሰተኛ ማንነት በጊዜ ሂደት ውስጣዊ ግጭትን ይፈጥራል።

ከማንነት ጋር መታረቅ ማለት የራስን ጥንካሬና ድክመት፣ ውበትና ጠባሳ አምኖ መቀበል ነው።

ታዋቂው የስነ-ልቦና ጠቢብ ካርል ዩንግ “ጥላህን (Shadow) እስካልተቀበልክ ድረስ ማንነትህ ሙሉ አይሆንም” ይላል።

ጥላችን የምንላቸው የማንነታችን ደካማ ጎኖች፣ የፈራናቸው ስሜቶችና የሸሸናቸው እውነታዎች ናቸው። ከእነዚህ ጋር ስንታረቅ ግን ውስጣዊ ሰላም ይነግሣል።

ታዋቂዋ ጋዜጠኛ  ኦፕራ ዊንፍሬን ብንመለከት ገና በልጅነቷ አስከፊ በደልና ድህነት ደርሶባታል። ለረጅም ጊዜ ያንን ታሪኳን ደብቃ ለመኖር ሞክራ ነበር። ነገር ግን እውነተኛ ስኬት የመጣላት ያንን ማንነቷን ሳትሸሽግ ያሳለፈችውን መከራ የማንነቷ አካል አድርጋ በመቀበል ለሚሊዮኖች ድምፅ መሆን ስትጀምር ነው። ማንነትህን ስትቀበል ዓለም አንተን የምታጠቃበት መሣሪያ ታጣለች።

በተጨማሪም “ኢምፖስተር ሲንድረም” የተባለው የስነ-ልቦና ቀውስ ብዙ ስኬታማ ሰዎችን ያጠቃል።

ይህ ራስን እንደ ብቁ አለመቁጠር ስሜት የሚመነጨው ከማንነት ጋር ካለመታረቅ ነው። ማያ አንጀሉ ታዋቂ ደራሲ ብትሆንም “አሁንም ቢሆን ሰዎች ድንገት መጥተው የጻፍኩት ሁሉ ከንቱ እንደሆነ የሚነግሩኝ ይመስለኛል” ትል ነበር። ይህ የሚያሳየው ከራስ ጋር መታረቅ የዕለት ተዕለት ሥራ መሆኑን ነው።

ያለፈው ሕይወት ወይ እስር ቤት ነው ወይም ደግሞ ትምህርት ቤት። ካለፈው ጋር ያልታረቀ ሰው ፊቱ ወደ ፊት ቢሆንም ልቡ ግን ወደ ኋላ እየተቀረቀረ ይሄዳል። “ለምን እንዲህ ሆነ? ለምን እንዲህ አደረግሁ?” የሚሉ ጸጸቶች የዛሬን ጉልበት ይበላሉ።

በዚህ ረገድ ቪክቶር ፍራንክል የተባለው የሥነ-ልቦና ባለሙያና በናዚ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የነበረው ምሁር “ማንስ ሰርች ፎር ሚኒንግ” በተሰኘው መጽሐፉ የሚገርም ሐሳብ ያነሳል።

ካለፈው መከራ ጋር መታረቅ የሚቻለው ለዚያ መከራ “ትርጉም” ስንሰጠው ብቻ እንደሆነ ይነግረናል። ያለፈው ስህተትህ ዛሬ ለምትገነባው ማንነት እንደ ግብዓት ካላገለገለህ እንደ ሸክም ይከብድሃል።

አብርሃም ሊንከን በሕይወቱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ውድቀቶችን አስተናግዷል። የንግድ ሥራው ከስሯል፣ የምርጫ ውድድሮችን ተሸንፏል፣ የሚወዳት ሴት ሞታበታለች።

ሊንከን በእነዚህ ውድቀቶች ውስጥ ተዘፍቆ ቢቀር ኖሮ አሜሪካን ከከፋ መከራ የታደገ መሪ መሆን ባልቻለ ነበር። እርሱ ግን ካለፈው ውድቀቱ ጋር ታርቆ፣ ውድቀትን እንደ ልምድ በመቁጠር ለትልቅ ዓላማ ተዘጋጀ።

በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ለ75 ዓመታት የተደረገ ጥናት  እንደሚያሳየው ደስተኛና ስኬታማ ሕይወት የሚመራው ካለፈው ቁስሉ ጋር ታርቆ ጤናማ ግንኙነትን በውስጡ መፍጠር የቻለ ሰው ነው። “ጸጸት የነፍስ መርዝ ነው” ይላሉ ጥናቶቹ።

ከራሱና ካለፈው ጋር የታረቀ ሰው ለወደፊቱ ግልጽ ራዕይ ይኖረዋል። የወደፊት ዝግጅት የሚጀምረው ካለፈው በተቀሰመ ትምህርት ላይ ቆሞ የዛሬን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ነው። የወደፊት ዝግጅት ማለት ጭንቀት ሳይሆን “ስትራቴጂ” ነው።

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከአሰቃቂ ሁኔታ በኋላ የሚመጣ እድገት ያላቸው ሰዎች ካለፈው መከራቸው ጋር ሰላም የፈጠሩ ናቸው።

እነዚህ ሰዎች ለወደፊቱ ያላቸው ዝግጁነት ከሌላው በበለጠ የላቀ ነው። ምክንያቱም ውድቀትን አይፈሩም፤ ውድቀትን እንደ መማሪያ መንገድ ቀርጸውታል።

ስቲቭ ጆብስ ከራሱ ድርጅት (አፕል) ተባሮ ነበር። ያን ጊዜ ግን ካለፈው ጋር ታርቆ አዳዲስ ነገሮችን ለመማር ተጠቀመበት። በኋላም “ከአፕል መባረሬ በሕይወቴ ከገጠሙኝ ምርጥ አጋጣሚዎች አንዱ ነበር። የስኬታማነት ሸክም ወርዶልኝ አዲስ ጀማሪ የመሆን ቅልጥፍና ሰጠኝ” ብሏል። ይህ ነው ለወደፊት መዘጋጀት ማለት፤ ትላንት የወደቅክበትን ጉድጓድ ዛሬ ድልድይ አድርገህ መሥራት።

ከቀደምት እውቀቶች ብንነሳ፣ ጥንታዊ ሮማዊያን ስቶይኮች “አሞር ፋቲ”  ወይም ዕጣ ፈንታህን ውደደው የሚል መርህ ነበራቸው። ይህም ማለት የደረሰብህን ሁሉ እንደ አስፈላጊ ግብዓት ተቀበለው ማለት ነው። ማርከስ ኦሬሊየስ የተባለው የሮማ ንጉሥና ፈላስፋ “በመንገድህ ላይ የሚመጣ እንቅፋት ራሱ መንገዱ ይሆናል” ብሏል።

ከማንነትና ካለፈው ጋር ለመታረቅ የሚከተሉት ነጥቦች ወሳኝ ናቸው፦

  1. ራስን ይቅር ማለት፦ ብዙ ጊዜ ሌሎችን ይቅር ለማለት እንቸኩላለን። ለራሳችን ግን ጨካኝ ዳኞች እንሆናለን። ራስህን እንደ አንድ የቅርብ ጓደኛህ ተመልከተው። ጓደኛህ ቢሳሳት የምትሰጠውን ምክርና ምህረት ለራስህም ስጥ።
  2. ታሪክን እንደገና መጻፍ ፦ “እኔ ተጎጂ ነኝ” የሚለውን ትረካ “እኔ ከብዙ መከራ የተረፍኩ ጠንካራ ሰው ነኝ” በሚል ቀይረው። ቃላት በውስጣዊ ማንነታችን ላይ ትልቅ ኃይል አላቸው።
  • በአሁኑ ሰዓት መኖር (ማይንድፉልነስ)፦ ያለፈው አልፏል። የወደፊቱ ገና አልመጣም። ያለህ ብቸኛው ሀብት “አሁን” ነው። አሁን ላይ ሰላም ከሆንክ የወደፊቱ ሰላምህ የተረጋገጠ ይሆናል።

ከማንነት ጋር መታረቅ የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው። ራስህን ካልወደድክና ካልተቀበልክ፣ ዓለም እንድትቀበልህ መጠበቅ ከንቱ ነው። ትናንትህ የቱንም ያህል የጨለመ ቢሆን ዛሬ ያንን ጨለማ ለነገው ብርሃን እንደ ዳራ ልትጠቀምበት ትችላለህ።

ሕይወት ልክ እንደ መጽሐፍ ናት፤ ያለፉት ገጾች ተጽፈው አልቀዋል። ልትቀይራቸው አትችልም። ነገር ግን የሚቀጥለውን ገጽ በምትፈልገው መንገድ የመጻፍ ሙሉ ሥልጣኑ በእጅህ ነው። ራስህን ይቅር በል፣ ማንነትህን አክብር፣ ካለፈው ተማር፤ ያኔ ነገ የፍርሃት ምንጭ መሆኑ ቀርቶ የተስፋ ሜዳ ይሆንልሃል።

ትላንት ተሸንፈህ ሊሆን ይችላል። ዛሬ ግን ያንን ሽንፈት “ትምህርት” ብለህ ከሰየምከው ለነገው ድል የመጀመሪያውን እርምጃ ረግጠሃል። ያለፈ ታሪክህ ለወደፊት ማንነትህ እንደ ማገዶ እንጂ እንደ ማነቆ ሊያገለግል አይገባም። ያረጀ ካርታህን ጣለው። አዲሱን ካርታ ይዘህ  ወደ ፊት ተጓዝ። ያለፈው አልፏልና።

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሰኔ 15   ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here