ኩራሳኦ (Curaçao)

0
303

በደቡባዊ የካሪቢያን ባሕር ውስጥ ከቬኔዝዌላ የባሕር ዳርቻ በግምት 65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ስትደርሱ፣ ዓይንዎን የሚስብ እና ልብዎን የሚያማልል አንዲት ልዩ ስፍራ አለች።

አሩባ (Aruba) እና ቦኔር (Bonaire) ከተሰኙት አጎራባች ደሴቶች ጋር በመሆን የ”ኤቢሲ ደሴቶች” (ABC Islands) በመባል የምትታወቀው የኩራሳኦ (Curaçao) ደሴት ናት። 444 ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ያላት በመልክዓ ምድሯ፣ በሕዝቧ የቋንቋ ብቃት፣ በአስገራሚ ታሪኳ እና ከየትኛውም የዓለም ክፍል በተለዩት አጓጊ እውነታዎቿ ጉድ ታስብላለች።

ብዙውን ጊዜ የካሪቢያን ደሴቶች በውበታቸው ቢታወቁም፣ ከሰኔ እስከ ህዳር ባለው ጊዜ ውስጥ በየዓመቱ በሚከሰት አውዳሚ የባሕር ላይ አውሎ ነፋስ (Hurricane) ክፉኛ ይመታሉ። የኩራሳኦ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ግን ከተፈጥሮ ቁጣ የታደጋት ይመስላል። ደሴቲቱ ከዚህ አውዳሚ የአውሎ ነፋስ መተላለፊያ ቀጠና በታች (Outside the hurricane belt) በመገኘቷ፣ ነዋሪዎቿም ሆኑ ጎብኚዎች ዓመቱን ሙሉ ፀሐያማ እና ደረቅ በሆነ የተረጋጋ አየር ንብረት ይደሰታሉ።

ይህ የተረጋጋ አየር ንብረት ኩራሳኦን ከ40 በላይ ለሚሆኑ ውብ የባሕር ዳርቻዎቿ (እንደ ግሮቴ ክኒፕ እና ካስ አባዎ) ምቹ አድርጓታል። በተጨማሪም “ክሪስቶፌል ብሔራዊ ፓርክ” በተባለው ጥብቅ ስፍራ ውስጥ የሚገኘው ብርቅዬው ነጭ-ጭራ አጋዘን፣ እንዲሁም “ሼቴ ቦካ” (ሰባቱ የባሕር መግቢያዎች) በተባለው ስፍራ ኃይለኛ የባሕር ሞገዶች ከግዙፍ የኖራ ድንጋይ ቋጥኞች ጋር በኃይል ሲላተሙ የሚፈጥሩት ትዕይንት የተፈጥሮን ድንቅ ኃይል ያሳያል። በ”ሲንት ዊሊብሮርዱስ” የጨው ሐይቆች ላይ ደማቅ ሮዝ ቀለም ያላቸው ረጃጅም ፍላሚንጎ ወፎች በመንጋ ሲመገቡ መመልከት ሌላው የዚህች ደሴት የተፈጥሮ ፀጋ ነው።

የኩራሳኦ ታሪክ እጅግ ማራኪ እና ውጣ ውረድ የበዛበት ነው። አውሮፓውያን ወደ አካባቢው ከመድረሳቸው በፊት ደሴቲቱ “ካኬቲዮ” (Caquetio) በተሰኙ የ”አራዋክ” (Arawak) የዘር ግንድ በሆኑ ተወላጆች ትተዳደር ነበር። በ1499 (እ.ኤ.አ) አሎንሶ ዴ ኦሄዳ የተባለ ስፔናዊ አሳሽ ደሴቲቱን ሲያገኛት፣ ተወላጆቹ ቁመታቸው ረጅም በመሆኑ “የግዙፎች ደሴት” (Isla de los Gigantes) ብሎ ሰይሟት ነበር።

በ1634 የኔዘርላንድ ምዕራብ ህንድ ኩባንያ ደሴቲቱን ስትራቴጂካዊ የተፈጥሮ ወደብ ስለነበራት ከስፔናውያን እጅ አስለቀቀ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኩራሳኦ የኔዘርላንድስ ቅኝ ግዛት ስትሆን፣ በሚያሳዝን ሁኔታ ዓለም አቀፍ የባሪያ ንግድ ማዕከል ሆና አገለገለች። ይህ የጨለማ ዘመን በ1795 “ቱላ” (Tula) በተባለ አፍሪካዊ ባርያ የተመራ ትልቅ አመፅ አስተናግዶ፣ በመጨረሻም በ1863 ባርነት በይፋ ተወገደ። የደሴቲቱ የኢኮኖሚ ትንሳኤ የሆነው በ1914 በቬኔዝዌላ ነዳጅ መገኘቱን ተከትሎ ግዙፍ የነዳጅ ማጣሪያ በኩራሳኦ ሲገነባ ነው። ዛሬ ላይ ደግሞ፣ ከጥቅምት 2010 ጀምሮ፣ ኩራሳኦ የራሷ ፓርላማ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ያላት ራስ ገዝ ሀገር ሆና በኩራት ቆማለች።

የዊልምስታድ ቀለማማ ሕንፃዎች እና ተንሳፋፊው ድልድይ ሚስጥሮች

የኩራሳኦ ዋና ከተማ “ዊልምስታድ” (Willemstad) በዓለም የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበች ውብ ከተማ ናት። ሕንፃዎቹ በደማቅ ቢጫ፣ ሰማያዊ፣ አረንጓዴ እና ሮዝ ቀለማት የተቀቡ ናቸው። ታሪክ እንደሚነግረን፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ገዢ የነበሩት አልበርት ኪከርት (Albert Kikkert) በነጭ ቀለም የተቀቡት ሕንፃዎች የሚያንፀባርቁት የፀሐይ ብርሃን ኃይለኛ የራስ ምታት እንዳመጣባቸው በመግለፅ፣ ሕንፃዎች በተለያዩ ቀለማት እንዲቀቡ አዘዙ። ነገር ግን እኚህ ገዢ በግላቸው ትልቅ የቀለም ፋብሪካ ባለቤት ስለነበሩ፣ ውሳኔው የራሳቸውን ፋብሪካ ምርት ለመሸጥ የተጠቀሙበት የንግድ ብልጠት እንደነበር ቆይቶ ተጋልጧል። ይሁን እንጂ ያ የፈጠሩት ብልጠት ከተማዋን ዛሬ ላለችበት ዓለም አቀፍ ውበት አብቅቷታል።

በዊለምስታድ ከተማ ውስጥ የሚገኘው “የንግሥት ኤማ ድልድይ” (Queen Emma Bridge) በውሃ ላይ የሚንሳፈፍ እና መርከቦች ሲያልፉ የሚከፈት ድልድይ ነው። በ1888 (እ.ኤ.አ) ይህ ድልድይ ሲገነባ ክፍያ (Toll) የሚሰበሰብበት መንገድ አስገራሚ ነበር። ጫማ ያደረጉ ሰዎች ብቻ ክፍያ ሲያስከፍሉ፣ ጫማ ያልነበራቸው (ድሆች) በነፃ ያልፉ ነበር። ይህንን የሰሙት ሀብታሞች ክፍያ ላለመክፈል ጫማቸውን እያወለቁ በባዶ እግራቸው መሻገር ሲጀምሩ፣ መንግሥት ክፍያውን በሙሉ ለማንሳት ተገዷል። በሌላ በኩል ደግሞ በከተማዋ የሚገኘው “ሚክቬ እስራኤል-ኢማኑኤል” ምኩራብ (Synagogue) በአሜሪካ አህጉር ካሉ ጥንታዊ የአይሁድ ቤተ እምነቶች አንዱ ሲሆን፣ በጥንት ዘመን አይሁዶች ሃይማኖታቸውን በድብቅ ሲያካሂዱ የኮቴያቸው ድምፅ ለጠላት እንዳይሰማ በአሸዋ ላይ ይፀልዩ የነበረውን የታሪክ ትውስታ ለማቆየት ወለሉ ሙሉ በሙሉ በነጭ አሸዋ የተሸፈነ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።

የኩራሳኦን ስም በዓለም ዙሪያ ካስጠሩት ነገሮች መካከል ዋነኛው “ብሉ ኩራሳኦ” (Blue Curaçao) የተሰኘው ሰማያዊ ኮክቴል መጠጥ ነው። ስፔናውያን ጣፋጭ የብርቱካን ዘሮችን አምጥተው ተክለው የነበረ ቢሆንም፣ በደሴቲቱ ደረቅ አየር ንብረት ምክንያት ብርቱካኑ ዉሎ አድሮ እጅግ መራራ እና ሊበላ የማይችል “ላሃራ” (Lahara) ወደሚባል አዲስ ዝርያ ተቀየረ። ነገር ግን የኩራሳኦ ሰዎች ይህን መራራ ፍሬ አልጣሉትም፤ ከልጣጩ ላይ ያለውን ዘይት በማውጣት ይህንን ዓለም አቀፍ መጠጥ ፈጠሩበት።

ካሪቢያን ሲታሰብ የባሕር ዓሳ እንጂ የአፍሪካ እንስሳት ወደ አእምሮ አይመጡም። ነገር ግን ኩራሳኦ ከአፍሪካ ውጪ በዓለማችን ካሉ ትላልቅ የሰጎን እርባታዎች (Ostrich Farms) አንዱን ይዛለች። የደሴቲቱ ደረቅ የአየር ንብረት ከደቡብ አፍሪካ ጋር በእጅጉ ስለሚመሳሰል ሰጎኖቹ በከፍተኛ ሁኔታ ሊራቡ ችለዋል። ከዚህም ባለፈ ጎብኚዎች በ”ኩራሳኦ ሰብስቴሽን” ሰርጓጅ መርከብ ተሳፍረው 1,000 ጫማ ጥልቀት ባለው የባሕር ወለል ውስጥ መጓዝ ይችላሉ።

የኩራሳኦ ሕዝብ ብዛት ከ150,000 በላይ ሲሆን፣ ከ50 በላይ የተለያዩ ብሔረሰቦች ይኖሩባታል። ማህበረሰቡ የአፍሪካ፣ የአውሮፓ፣ የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ተወላጆች ድንቅ ቅልቅል ነው። በኩራሳኦ አንድ ተራ ዜጋ ቢያንስ አራት ቋንቋዎችን አቀላጥፎ ይናገራል! ሕዝቡ የሀገሪቱን ይፋዊ ቋንቋ የሆነውን እና ከአፍሪካ፣ ስፓኒሽ፣ ፖርቹጋልኛ እና ደች የተዳቀለውን “ፓፒያሜንቱ”(Papiamentu)፣ የትምህርት ቋንቋ የሆነውን ደች፣ ለንግድ ስፓኒሽ፣ እንዲሁም ለቱሪዝም እንግሊዝኛን ይጠቀማል። ይህ የቋንቋ ብቃት ማህበረሰቡን እጅግ ክፍት፣ ተቻቻይ እና እንግዳ ተቀባይ አድርጎታል።

የሕዝቡ የአኗኗር ዘይቤ “ዱሺ” (Dushi) በሚለው የፓፒያሜንቱ ቃል ይገለፃል። “ዱሺ” ማለት ጣፋጭ፣ ውብ፣ እና ፍቅር ማለት ሲሆን፣ የደሴቲቱን ዘና ያለ እና ደስተኛ የሕይወት ፍልስፍና ይወክላል። “ታምቡ” (Tambú) በተባለው የከበሮ ሙዚቃ እና ጭፈራ ብሶታቸውን ወደ ጥበብ የቀየሩት እነዚህ ሕዝቦች፣ ቅዳሜ እና እሁድ ቤተሰብ እና ጓደኛሞች በባሕር ዳርቻዎች ላይ ተሰባስበው “ባርቤኪው”  በብረት ላይ ስጋ በመጥበስ በማዘጋጀት ዘና ይላሉ። ከምሽት ጀምሮ ደግሞ “ትሩክ-ኢ-ፓን” (Truk’i Pan) በተባሉ ተንቀሳቃሽ የምግብ መኪኖች ዙሪያ ተሰብስበው፣ የተጠበሰ ስጋ እና ሳንድዊቾችን እየበሉ ማውራት፣ መሳቅ እና መደነስ የዘወትር የማህበረሰብ መገናኛ መንገዳቸው ነው። “ኬሺ ዬና” የተባለውም ከ “ቺዝ” ቅርፊት፣ ስጋ እና ቅመማ ቅመም የሚዘጋጀው ጣፋጭ ታሪካዊ ምግባቸው የዚህ የባህል ውህደት ማሳያ ነው።

ኩራሳኦ በካሪቢያን ባሕር ውስጥ የምትገኝ የተፈጥሮ ውበት እና የታሪክ ክምችት ብቻ ሳትሆን፤ ሕያው የሆነ የደስታ፣ የጥበብ፣ እና የመቻቻል ትምህርት ቤት ናት። ከንግድ ብልጠት የተፈጠሩት ቀለማማ ሕንፃዎቿ፣ በባዶ እግር የሚታለፈው ድልድይዋ፣ ከመራራ ፍሬ የተገኘው ጣፋጭ መጠጧ እና በአራት ቋንቋዎች ፈገግታን የሚለግሰው ማህበረሰቧ፣ ይህችን ደሴት ከየትኛውም የዓለም ክፍል የተለየች ያደርጓታል። የቱሪዝም፣ የፋይናንስ እና የሎጂስቲክስ ጠንካራ ኢኮኖሚ የገነባችው ይህች ደሴት፣ እውነተኛ የካሪቢያን ድብቅ ዕንቁ ናት! በመሆኑም በሕይወት ዘመንዎ ሊጎበኟቸው ከሚገቡ ማራኪ ስፍራዎች ዝርዝር ውስጥ “ኩራሳኦን” ቢያካትቷት ፈጽሞ አይፀፀቱም።

 

አጫጭር እውነታዎች

ስለ ካሪቢያን አጫጭር መረጃዎች

  1. የካሪቢያን ክልል በሰሜን አሜሪካ እና በደቡብ
  2. በክልሉ ውስጥ ከ700 በላይ ትናንሽ እና
  3. የካሪቢያን ህዝብ የአፍሪካ፣ ካርታ፣ የኢሳ እና የነባር (አገሬው ተወላጅ) ህዝቦች ድብልቅ ነው። በዚ የተነሳ ከሉ እጅግ
  4. ይህ ክልል ለዓለም ካበረከታቸው ታላላቅ ሥራዎች አንዱ ሙዚቃ ነው። እንደ ሬጌ (ሬጌ – ከጃማይካ)፣ ሳልሳ (ሳልሳ – ከኩባ)፣ ካሊፕሶ (ካሊፕሶ – ከትሪኒዳድ) እና ዳንስሆል (ዳንስ አዳራሽ) ሌሎች የሙዚቃ ሥራዎች
  5. የካሪቢያን ክፍል ሞቃታማ (ትሮፒካል) የአየር ንብረት አለው። አመቱን ሙሉ ሐያማ ቢሆንም፣ ከሰኔ እስከ ህዳር ባለው ጊዜ ውስጥ ለከፍተኛ አውሎ ነፋስ (Hurricanes) የተጋለጠ ነው።
  6. የክልሉ ዋና የገቢ ምንጭ ቱሪዝም ነው። ውብ ነጭ የባህር ዳርቻ የባህር ዳርቻዎች (የባህር ዳርቻዎች)፣ የቆሻሻ መጣያ ውሃ እና ሞቃታማ አየር በፊልሊዮን ቱሪስቶች ይጎበኙታል። በተጨማሪም ግብርና (በተለይ ሸንጎ አገዳ፣ ሙዝ፣ ትምባሆ እና ቡና) ።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የሰኔ 22  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here