የአንዲት ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትና ማኅበራዊ መረጋጋት ባመዛኙ የሚለካው የሰው ኃይሏን በተለይም ወጣቱን ትውልድ ወደ አምራችነት በመቀየር አቅሟ ላይ ነው። ወጣቱን ትውልድ ወደ አምራችነት የመቀየር አቅሟ ባደገ ቁጥር ሁለንተናዊ ዕድገቷ ይፋጠናል፤ ማኅበራዊ መረጋጋት ይሰፍናል፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ይመረቃሉ። ይህ ሰፊ የሰው ኃይል በአግባቡ ከተመራና ወደ አምራችነት ከተሸጋገረ ለሀገር ዕድገት ታላቅ ሞተር ሊሆን የሚችል ቢሆንም፣ በተቃራኒው ግን በባህላዊው “የመንግሥትና የቅጥር ሥራ ፈላጊነት” አስተሳሰብ ውስጥ ከቀጠለ የምጣኔ ሀብታዊና የማኅበራዊ ቀውስ ምንጭ መሆኑ አይቀሬ ነው። በመሆኑም ዜጎችን ከሥራ ፈላጊነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት እንዲሁም አምራችነት ማሸጋገር የአማራጭ ጉዳይ ሳይሆን የሀገር ህልውናና የምጣኔ ሀብት ነጻነት ጥያቄ ነው።
ለወጣቶች ዘላቂ የሥራ ዕድል መፍጠርና የሥራ ተሳትፏቸውን ማሳደግ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት፣ ብሎም ማኅበራዊ መረጋጋት አማራጭ የሌለው መሠረታዊ ጉዳይ ነው። በሸኘነው የ2018 በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከአምስት ሚሊዮን በላይ፣ በአማራ ክልል ደግሞ ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን የተቋማት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ አፈጻጸም ተስፋ ሰጭና በእጅጉ የሚያበረታታ ነው። በዚህ ክዋኔ መሠረት የሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጠራ በ13 በመቶ፣ የሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ደግሞ በ27 በመቶ አድጓል፡፡ ይህ ከፍተኛ አፈጻጸም መንግሥት እየተከተለ ያለው የተቀናጀ የፖሊሲ አቅጣጫ ፍሬ እያፈራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው።
ይሁን እንጂ፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከሚመረቁ ወጣቶች ቁጥርና በከተሞች ከሚታየው የሥራ አጥነት ጫና አንጻር በሥራ ዕድል ፈጠራም ኾነ በሥራ ስምሪት የተሠራው ሥራ በዘላቂነት የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ወጣቶች በራስ የመተማመን ስሜትንና የፈጠራ አስተሳሰብን አዳብረው፣ ከተቀጣሪነት ስሜት ወጥተው፣ ሥራ ሳይንቁ፣ በአዳዲስ የክህሎት ሥልጠናዎች ታግዘውና ተደራጅተው ወደ ማምረትና አገልግሎት ዘርፍ መግባት ይችሉ ዘንድ የበለጠ መሠራት ይኖርበታል፡፡ በተለይም የወጣቶቹን ተነሳሽነትና የመንግሥትን ያፈጻጸም ደረጃ ወደ ሙሉ ምጣኔ ሀብታዊ ሽግግር ለመቀየር አሁንም በመሬት ላይ ያሉ መዋቅራዊ ማነቆዎችን በድፍረት መጋፈጥና መፍታት የግድ ይላል።
ወጣቶቹ በግልጽ እንዳመለከቱት የሥራ ፈጠራ ለሀገር ዕድገት ያለው ሚና ዘልማዳዊ ከሚመስል የዕለት ጉርስ ፍጆታ የላቀ ነው። አዳዲስ የንግድ ተንቀሳቃሾች (Enterprises) ሲፈጠሩ የሀገር ውስጥ ምርታማነት ያድጋል፣ የውጭ ምንዛሬን የሚተኩ ምርቶች በሀገር ውስጥ መመረት ይጀምራሉ፤ ወጣቱ የፈጠራ አቅሙንና ቴክኖሎጂን በመጠቀም አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን ይፈጥራል፤ ሥራ ያገኘ ዜጋ ገቢ ያመነጫል፣ ራሱንና ቤተሰቡን ይደግፋል፤ ለመንግሥትም የግብር ገቢ ያበረክታል። ይህ ዑደት ደግሞ ድህነትን፣ ሕገ-ወጥ ስደትንና የወንጀል ተጋላጭነትን በመቀነስ ረገድ የሚጫወተው ሚና በቀላሉ የሚገመት አይደለም።
ከሥራ ፈላጊነት ወደ ሥራ ፈጣሪነትና አምራችነት የሚደረገው ጉዞ ዘላቂ ግብ ኖሮት፣ በስልትና በቅንጅት እየተመራ የሚተገበር፣ ድህነትን በዘላቂነት የሚያስወግድና የሀገራችንን የዕድገት ግስጋሴ የሚያፋጥን መኾን ይኖርበታል፡፡ ለዚህም ተግባራዊነት የግል ዘርፉን፣ የፋይናንስ ተቋማትን፣ የትምህርት ዘርፉንና ራሱን ወጣቱን ያካተተ ዘላቂ ሀገራዊ ስትራቴጂ ሊቀረጽለት ይገባል። የነገዋን የበለጸገችና የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለመገንባት ዛሬ ላይ በወጣቶች የፈጠራ አቅምና ሥራ ፈጠራ ላይ በቁርጠኝነት መዋዕለ-ነዋይ ማፍሰስ ብቸኛው አማራጭ መንገድ ነው!
ባጠቃላይ ሥራ ፈጠራና ስምሪት የሀገር ህልውናና የሁለንተናዊ ዕድገት ጥንካሬ ምሰሶ ነው። ስለሆነም ወጣቶች ሥራን ባለመናቅና አዳዲስ ክህሎቶችን በመቅሰም የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፤ መንግሥትና አጋር አካላት ደግሞ ሥልጠና የወሰዱ ወጣቶች በገበያ፣ በፋይናንስና በሥራ ቦታ እጥረት ምክንያት እንዳይሰናከሉ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል ሊቀጥሉ ይገባል – የወጣቶች ስኬት የሀገር ስኬት ነውና!፡፡
በኲር የሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


