ከተሳታፊነት ባሻገር እንመልከት!

0
165

በድሬዳዋ ከተማ በተካሄደው የኢትዮጵያ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ላይ የአማራ ክልል አራት የእግር ኳስ ቡድኖችን አሳትፏል። እነርሱም፦  ሁለት እጁ እነሴ፣ ሸዋ ሮቢት፣ መንቆረር እና ወረኢሉ የሚል መጠሪያ ስሞች ያሏቸው ቡድኖች ናቸው።

ቡድኖቹ ለዚህ ጨዋታ የበቁት የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2018 ዓ.ም የአማራ ሊግ ውድድሮችን  በምዕራብ እና ምሥራቅ አማራ ቀጣናዎች በሚል ከፋፍሎ ባካሄደው ውድድር  አሸናፊ በመኾናቸው ነው።

በምዕራብ አማራ ቀጣና በባሕር ዳር ከተማ ላይ በተካሄደው ጨዋታ መንቆረር እና ሁለት እጁ እነሴ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ  አሸናፊ መኾናቸው ይታወሳል፡፡

በምሥራቅ አማራ ቀጣና በደሴ ከተማ  በተከናዎነው ጨዋታ ደግሞ ወረኢሉ እና ሸዋ ሮቢት ቡድኖች በአንደኛነት እና ሁለተኛነት ውድድራቸውን አጠናቀው ነው ለኢትዮጵያ ክለቦች ሻምፒዮና የደረሱት።

አራቱ የእግር ኳስ ቡድኖች አማራ ክልልን በመወከል ከሐምሌ 5 ቀን እስከ ሐምሌ 26 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በድሬዳዋ ከተማ በተካሄደው የኢትዮጵያ የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ላይ የምድብ ጨዋታቸውን አድርገዋል።

በክለቦች ሻምፒዮና ላይ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ ቡድኖችም በ2019 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ‘ሊግ’ አንድን መቀላቀላቸው ታውቋል፡፡  በ2019 የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ‘ሊግ’ አንድ ላይ እንደሚጫወቱ ያረጋገጡ የእግር ኳስ ቡድኖችም፦ ሶማሌ ፖሊስ፣ ስርጢ ከተማ፣ ቴፒ ከተማ፣ ጊምቢ ከተማ፣ ትግራይ ፖሊስ ዋልታ፣ ቡልድግሉ ዙምባራ፣ ጉለሌ ክፍለ ከተማ እና ቃኘው ናቸው።የአማራ ክልልን ወክለው የተጫወቱት ቡድኖች ተሳትፎ እና ውጤት ምን ይመስላል? ቡድኖቹ ያስመዘገቡት ውጤት እንዴት ይገለጻል? በቀጣይ ለውድድር የሚቀርቡ ቡድኖችስ ከተሳትፎ ባሻገር ሊግ አንድን ለመቀላቀል እንዴት ይቅረቡ? የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም።

እኛም የ”ኢትዮጵያ ሊግ አንድ” ድረ ገጽን ተመልክተን እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን አስተያዬት አካተን ያጠናቀርነውን መረጃ እንካችሁ እንላለን።

በመጀመሪያም ቡድኖቹ ያደረጓቸውን ጨዋታዎች እና  ውጤቶቻቸውን በወፍ በረር እንመልከት…፡፡

ሸዋ ሮቢት

በሰሜን ሸዋ አስተዳደር ሥር የሚገኘው የሸዋ ሮቢት የእግር ኳስ ቡድን የተደለደለው ምድብ ስድስት ላይ ነው።

ቡድኑ ስርጢ ከተማን 2 ለ 1 አሸንፏል። ከአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ቡድን ጋር ደግሞ አንድ አቻ ተለያይቷል። በአንጻሩ በሽራሮ ከተማ  4 ለ 2 ተሸንፏል፡፡ በድምር ውጤትም ከ43 ተፎካካሪ ቡድኖች መካከል 32ቱን መቀላቀል ችሏል፤የሸዋ ሮቢት ቡድን፡፡

ቡድኑ ከቡርታ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ በመደበኛው 90 ደቂቃ  አንድ አቻ በመለያየቱ በተሰጠው የመለያ ምት 4 ለ 3 ድል በመንሳት ወደ 16ቱ ምርጥ ቡድኖች መቀላቀል ችሎ ነበር፡፡ ይሁንና በ16ቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ወደ ስምንቱ ምርጥ ቡድኖች ለመድረስ ከሶማሌ ፖሊስ ጋር ያደረገውን እጅግ ብርቱ ጨዋታ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት በመሸነፉ አስደናቂ ጉዞው ተገድቧል።

መንቆረር

በምሥራቅ ጎጃም አስተዳደር ደብረ ማርቆስ ከተማ ውስጥ የሚገኝ የእግር ኳስ ቡድን ነው፤ መንቆረር። ይህ ቡድን  ቃኘው ከተሰኜ ቡድን ጋር ያደረገውን ጨዋታ አንድ አቻ አጠናቋል፤  ከኡርጂ ቀፊራ ቡድን ጋር ደግሞ  ዜሮ ለዜሮ  ተለያይቷል ። ቦረና ከተማን አንድ ለ ዜሮ በማሸነፍ ጉዞውን አሳምሮ ነበር። ነገር ግን በ32ቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በቡልዲግሉ ዙምባራ ቡድን ሦሥት ለ ሁለት በሆነ ውጤት ተሸንፎ ሩቅ አላሚ ቅርብ አዳሪ በመኾን ሩጫውን ቋጭቷል።

ሁለት እጁ እነሴ

በምሥራቅ ጎጃም አስተዳደር ሥር የሚገኘው የሁለት እጁ እነሴ የእግር ኳስ ቡድን ምድብ 11 ላይ ነው የተደለደለው። ቡድኑ  ታይዋን  ከተሰኘ ቡድን ጋር አንድ አቻ፣ ከድሬ ዳዋ ፖሊስ ዜሮ ለ ዜሮ  ተለያይቷል፡፡ ቦንጋ ከተማን ደግሞ አንድ ለ ዜሮ በማሸነፍ በ32ቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ጉለሌ ክፍለ ከተማን   ሁለት ለ አንድ ድል አድርጓል፡፡

ሁለት እጁ እነሴ የእግር ኳስ ቡድን 16ቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ መቀላቀል ችሎ ነበር። ይሁንና  በጊምቢ ከተማ  ሁለት ለ ዜሮ  በኾነ ውጤት ተሸንፎ ከውድድሩ መወጣቱን የኢትዮጵያ ሊግ አንድ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

ወረኢሉ

በደቡብ ወሎ የሚገኘው ወረኢሉ ከተማ በምድብ አራት ተደልድሎ ከትግራይ ፖሊስ ዋልታ ዜሮ ለ ዜሮ፣ ከጊምቢ ከተማ አንድ አቻ   ተለያይቷል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ አንድ ለ ዜሮ ተሸንፏል፡፡

ቡድኑ በየጨዋታው ጠንካራ ፉክክር አድርጓል፡፡ ነገር ግን በምድቡ የሚገኙ ቡድኖች ከነበራቸው ወጥ አቋም እና ጥንካሬ አንጻር ወደ ቀጣዩ የጥሎ ማለፍ ዙር ሳያልፍ ቀርቷል።

በ”ኢትዮጵያ የክለቦች ሻምፒዮና”  የአማራ ክልልን ከወከሉት አራት ቡድኖች መካከል ሁለት እጁ እነሴ እና ሸዋ ሮቢት ከተማ 16ቱን የጥሎ ማለፍ ቡድኖች መቀላቀል ችለዋል። ቡድኖቹ ይዘውት የመጡትን የአሸናፊነት የሥነ ልቦና ጥንካሬ በ16ቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ላይ  ማስቀጠል ቢችሉ  ኖሮ በስምንቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ወስጥ ይገቡ ነበር። ግን አልኾነም።

በኢትዮጵያ ክለቦች ሻምፒዮና ሕግ መሠረት ከዚህ ቀደም በየዓመቱ አራት ቡድኖች ወደ ሊግ  አንድ ይገቡ ነበር።ዘንድሮ ግን ሕጉ ተሻሽሎ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃ ይዘው ማጠናቀቅ የሚችሉ ቡድኖች አንደኛ ሊግን እንደሚቀላቀሉ ተበስሯል።

የብሥራቱን ዜና ተከትሎ በ2018 የኢትዮጵያ ክለቦች ሻምፒዮና የሚሳተፉ ቡድኖች ብልጠትን አክለው፣ ጥበብን ጨምረው እና ከመቼውም ጊዜ  በተሻለ መልኩ  የአሸናፊነትን ወኔ ተላብሰው መጫወታቸውን የተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ዘግበዋል።

የሀገር ውስጥ የብዙኅን መገናኛ አውታሮች እንዳሉት ተፎካካሪ ቡድኖች ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክረው ቀርበው ታይተዋል።  ይህ ደግሞ በሰላም እጦት ምክንያት በየከተሞቻቸው ጠንካራ የውስጥ ውድድር ሳያደርጉ ለጨዋታ  ለቀረቡት የአማራ ክልል ቡድኖች ፈተናውን አግዝፎባቸዋል።

የወረኢሉ እግር ኳስ ቡድን መሪ መላኩ ሽመልስ ለአሚኮ ደሴ በስልክ በሰጡት  አስተያዬት በጨዋታው ተጫዋቾች ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል። በቀጣይ ስህተቶቻችንን ለማረም ጥረት እናደርጋለን ማለታቸው ይታዎሳል።

በዘንድሮው የኢትዮጵያ የክለቦች ሻምፒዮና አማራ ክልልን ከወከሉት ቡድኖች መካከል አንድም ቡድን  ወደ ኢትዮጵያ ‘ሊግ’ አንድ ማለፍ አልቻለም።

እኮለምን?

በአማራ ክልል ያለውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በቅርብ እንደሚከታተሉት የነገሩን አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ እና የሰውነት ማጎልመሻ እና ስፖርት ሳይንስ የኮሌጅ መምህር።

እንዳሉት በኢትዮጵያ  ክለቦች ሻምፒዮና ላይ የአማራ ክልል ክለቦች አጥጋቢ ውጤት አላስመዘገቡም።

በክልሉ የተከሰተው ግጭት/ጦርነት/ በየከተሞች የተረጋጋ የሊግ ውድድር እንዳይካሄድ በማድረጉ ቡድኖቹ ዓላማቸውን እንዳያሳኩ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፎባቸዋል ነው ያሉት።

የእግር ኳስ ተጫዋቾች/ስፖርተኞች/ በመደበኛነት በመለማመጃ ሜዳ  ላይ እየተገኙ  በግል እና በቡድን  ለመሰልጠን ብሎም ራሳቸውን ለማብቃት የሰላም እጦቱ ሳንካ ኾኖባቸው ቆይቷል። ይህም የተጫዋቾችን ሥነ ልቦና ሰብሮታል ብለዋል።

 

(ሙዋ ሊሙ)

በኲር የነሐሴ  4  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here