ዓለም በፀጥታ ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተሸጋግራለች። በአንድ ወቅት የሆሊውድ ብቸኛ ይዞታ የነበረው ዓለም አቀፉ የሲኒማ መድረክ ዛሬ በሁለት ያልተጠበቁ ግዙፍ ተዋናዮች ተነጥቋል፤ በቱርክ እና ደቡብ ኮሪያ። ሁለቱም ሀገራት ያለ ምንም ወታደራዊ ኃይል፣ ያለ ፖለቲካዊ ዛቻ በተረት ተረት፣ በስሜት እና በካሜራ ጥበብ ብቻ ዓለምን በባህል ቅኝ እየገዙት ነው።
ይህ ተአምር እንዴት ተፈጠረ? ከዚህስ ጀርባ ያለው የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስሌት ምንድን ነው? የሶስት ሺህ ዓመታት ታሪክ እና ያልተነገሩ ገድሎች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያስ ከዚህ ምን ትማራለች?
የቱርክ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች በቱርክኛ “Dizi” ይባላሉ። በዓለም ዙሪያ የሚያሳዩት ግስጋሴ አስደናቂ ነው። ቱርክ ዛሬ ከአሜሪካ እና ከእንግሊዝ ቀጥላ በዓለም ሦስተኛዋ ግዙፍ የቴሌቪዥን ድራማ ላኪ ሀገር ሆናለች።
ቁጥሮቹ ምን ይላሉ? ፓሮት አናሌቲክስ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥንና የመዝናኛ መረጃ ተንታኝ ኩባንያ አሀዛዊ መረጃዎችን እንዲህ አስቀምጧል፤
- የገቢ መጠን፦ ቱርክ በየዓመቱ የቴሌቪዥን ድራማዎችን ወደ ውጭ በመላክ ብቻ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ታገኛለች።
- ተመልካች እና ተደራሽነት፦ የቱርክ ድራማዎች በዓለም ዙሪያ ከ170 በላይ ሀገራት ለዕይታ የሚቀርቡ ሲሆን ከ750 ሚሊዮን በላይ ቋሚ ተመልካቾች አሏቸው።
- የምርት አቅም፦ ሀገሪቱ በየዓመቱ ከ60 እስከ 100 የሚደርሱ አዳዲስ ግዙፍ ተከታታይ ድራማዎችን እንዲሁም ከ150 በላይ የሲኒማ ፊልሞችን ታመርታለች። እያንዳንዱ የድራማ ክፍል ከ90 እስከ 120 ደቂቃ የሚረዝም ሲሆን የማምረቻ ወጪውም በአንድ ክፍል እስከ መቶ ሺዎች የሚቆጠር ዶላር ይደርሳል።
- ተወዳጅ ስራዎች፦ ሙህተሼም ዩዝይል (ድንቁ ክፍለ-ዘመን)፣ ኤርቱግሩል (ትንሳኤ ማለት ነው፤ ኤርቱግሩል የኦቶማን መስራች የኦስማን አባት ስም ነው)፣ ካራ ሴቭዳ (ጥቁር ፍቅር) ፈጽሞ የማይጠፋ፣ ጥልቅ ወይም ዓይነ-ስውር የሆነ ፍቅር ማለት ሲሆን በእንግሊዝኛ በተለምዶ Endless Love ተብሎ ይተረጎማል። ይህ ድራማ የኤሚ አዋርድ ያሸነፈው የቱርክ ድራማ ነው) እና ሌሎች ተወዳጅ ድራማዎች ስራዎች በላቲን አሜሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በመላው እስያ እና በደቡብ አውሮፓ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ተወዳጅ ሆነዋል። ጥቁር ፍቅር እና ሌሎችም የቱርክ ድራማዎች በእኛም ሀገር ተተርጉመው ተመልክተናቸዋል።
ዓለም ለምን ተቀበላት?
- የምስራቅ እና ምዕራብ ድልድይ መሆኗ፦ የቱርክ ድራማዎች የምዕራባውያንን የዘመናዊ አኗኗር እና ጥራት ከምስራቃውያን ጥብቅ የቤተሰብ ክብር፣ ታማኝነት እና ባህላዊ እሴቶች ጋር አዋህደው ያቀርባሉ።
- ተፈጥሯዊ እና ጥልቅ ስሜት፦ ከልክ ያለፈ እርቃን እና ጸያፍ ይዘት ሳይኖርባቸው፣ በልብ አንጠልጣይ ፍቅር እና የበቀል ሴራ ተመልካችን ማሰር መቻላቸው ለቤተሰብ እይታ ምቹ አድርጓቸዋል።
- ከፍተኛ የምርት ጥራት (Cinematography)፦ የኢስታንቡል የተፈጥሮ ውበት፣ አስደናቂ አለባበሶች እና ልብ የሚነኩ የሙዚቃ ቅንብሮች ተመልካችን ይማርካሉ።
ቱርክ ምን ልታገኝ አስባ ነው?
ቱርክ ይህንን የምታደርገው ለፊልም ሽያጭ ገቢ ብቻ አይደለም። ፊልሞቿ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪዋ ከፍተኛ ነዳጅ ሆነዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የውጭ ዜጎች ድራማዎቹ የተሰሩባቸውን ታሪካዊ ቦታዎች ለማየት ወደ ኢስታንቡል ይጎርፋሉ። ከዚህም በላይ ቱርክ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ላይ ያላትን የዲፕሎማሲ ተቀባይነት እና ተጽዕኖ (Soft Power) ለማሳደግ ሲኒማን እንደ ስትራቴጂካዊ መሳሪያ እየተጠቀመችበት ነው።
የደቡብ ኮሪያ “ሃልዩ” — ከኢኮኖሚ ቀውስ እስከ ኦስካር የበላይነት
የደቡብ ኮሪያ የባህል ማዕበል (Hallyu – Korean Wave) የዘመናችን እጅግ ስኬታማ የባህል እና የኢኮኖሚ ኢንጂነሪንግ ተምሳሌት ነው። በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ እስያን የመታውን የኢኮኖሚ ቀውስ ተከትሎ የኮሪያ መንግሥት “ሀብታችን አዕምሯችን እና ባህላችን ነው”በሚል የፈጠራ ኢንዱስትሪውን የመንግሥት ዋነኛ የኢኮኖሚ አቅጣጫ አድርጎታል።
የስኬቱ ማሳያዎች እና ቁጥራዊ መረጃዎች፦
- የኢንዱስትሪው ግዝፈት፦ የደቡብ ኮሪያ የይዘት ኢንዱስትሪ ዓመታዊ የውጭ ሽያጭ ገቢ ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን የኮሪያ ፈጠራ ይዘት ባለሥልጣን አስፍሯል።
- ዓለም አቀፍ ድሎች፦ በ2020 ዳይሬክተር ቦንግ ጁን-ሆ የሰራው ፓራሳይት የተሰኘው ፊልም በኦስካር ታሪክ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ያልሆነ የመጀመሪያው “ምርጥ ፊልም” አሸናፊ ሆኗል።
- በ2021 እ.አ.አ በኔትፍሊክስ የቀረበው ስኪውድ ጌም በተለቀቀ በመጀመሪያው ወር ብቻ በ1.65 ቢሊዮን ሰዓታት በመታየት የኔትፍሊክስ የዘመናት ሁሉ ክብረ ወሰን ሰባሪ ሆኗል።
- ተከታታይ ድራማዎች (K-Dramas)፦ እንደ ክራሽ ላንዲንግ ኦን ዩ፣ ዘ ግሎሪ፣ እና ዲሰንዳንትስ ኢፍ ዘ ሰን ያሉ ድራማዎች በመላው ዓለም ወጣቱን ትውልድ ማርከዋል።
የኮሪያ ስኬት ምስጢር ምንድን ነው?
- የመንግሥት እና የግል ዘርፍ ቅንጅት፦ የኮሪያ መንግሥት ለፈጠራ ሰዎች የገንዘብ ድጎማ፣ የታክስ ማቅለያ እና ዘመናዊ የስልጠና ማዕከላትን አዘጋጅቷል።
- ሁለንተናዊ የሰው ልጅ ፈተናዎችን ማንሳት፦ የኮሪያ ፊልሞች የማህበራዊ መደብ ልዩነትን፣ የፍትህ እጦትን፣ የድህነት እና የሀብት ንፅፅርን በልዩ የጥበብ ጥልቀት ያሳያሉ፤ ይህም በየትኛውም የዓለም ክፍል ያለ ተመልካች የራሱ ጉዳይ አድርጎ እንዲመለከተው ያደርጋል።
- የቴክኖሎጂ እና የግብይት ብቃት፦ ስራዎቻቸውን በኔትፍሊክስ፣ ዩቲዩብ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የዲጂታል መድረኮች ላይ በተገቢው መንገድ ተደራሽ አድርገዋል።
የሲኒማ ኃይል ቲኬት ከመቁረጥ ወይም ሰዎችን ከማዝናናት እጅግ የላቀ ነው። ጆሴፍ ናይ የተባለው የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ምሁር “ሶፍት ፓዎር” (ለስላሳ ኃይል) ብሎ የሚጠራው ጽንሰ-ሀሳብ በሲኒማ ውስጥ ይንጸባረቃል።
አንዲት ሀገር በጦር መሳሪያ ሰዎችን ማስገደድ ሳያስፈልጋት በፊልሞቿ አማካኝነት ሰዎች ቋንቋዋን እንዲማሩ፣ ምግቧን እንዲመገቡ፣ ፋሽኗን እንዲከተሉ እና ለሀገሪቱ ፍቅርና አክብሮት እንዲኖራቸው ታደርጋለች።
ዛሬ የኮሪያ ፊልሞችን ያየ ወጣት የኮሪያን ምግብ (ኪምቺ/ራመን) ይቀምሳል፤ የኮሪያን ስልኮችና መኪኖች (ሳምሰንግ፣ ሃዩንዳይ) በልበ ሙሉነት ይገዛል፤ የኮሪያ መዋቢያዎችን ይጠቀማል። ቱርክን ያየ ተመልካች በበኩሉ የቱርክን ልብሶች ይሸምታል፤ ለዕረፍት ወደ ኢስታንቡል ይጓዛል።
ሲኒማ የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ በሙሉ የሚያንቀሳቅስ ግዙፍ ሞተር ነው። ይህንን ሁሉ ስንመለከት ወደራሳችን ማየታችን አይቀሬ ነው። ኢትዮጵያ ከ3 ሺህ ዓመታት በላይ የዘለቀ ያልተነካ የታሪክ ማዕድን፣ አስደናቂ የተፈጥሮ ውበት፣ ከ80 በላይ የተለያዩ ባህሎች፣ አፈ-ታሪኮች እና ጀግንነቶች ባለቤት ነች። ሆኖም የሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ አሁንም ድረስ በዝቅተኛ በጀት፣ በተደጋጋሚ የፍቅር-ቀልድ (ሮማንቲክ ኮሜዲ) ታሪኮች እና በቴክኒክ ድክመቶች ታጥሮ ይገኛል።
የ21ኛው ክፍለ ዘመን ኃያልነት የሚለካው በኒውክሌር ብዛት ብቻ ሳይሆን ዓለምን በሚያስለቅሱ፣ በሚያስቁ እና በሚያስተምሩ ታሪኮች ብቃት ጭምር ነው። ቱርክ እና ደቡብ ኮሪያ ዓለምን ለመማረክ የራሳቸውን ማንነት እና ባህል አዘምነው ለዓለም አቀረቡ፤ ዓለምም በክብር ተቀበላቸው።
ኢትዮጵያም በታሪኳ እና በማንነቷ የምትኮራ ሀገር እንደመሆኗ ካሜራዎቿን አውጥታ ያልተነገሩ ታሪኮቿን ለዓለም የምታሳይበት ጊዜ አሁን ነው። ካልሆነ ግን፣ የሌሎችን ታሪክ በገዛ ሳሎናችን እየተመለከትን፣ የሌሎችን ባህል በራሳችን ልጆች ላይ እያተምን የባህል ተገዢ ሆነን ልንቀር እንችላለን።
መረፊያ
አለቀለት ያሉት
ከጅረት አጠገብ ፥ቆሞ የኖረ ዛፍ
መብረቅ ገነደሰው
አሁን ድልድይ ሁኖ፥ ያሸጋግራል ሰው ::
“አለቀለት” ያሉት፤ ተልኮው መች አልቆ
ቆመ የጠቀመ፥ መላ አያጣም ወድቆ::
(በእውቀቱ ስዩም)
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


