የግብር ቅሬታ ለማን ይቀርባል?

0
7

“ሞት እና ግብር የማይቀር ዕዳ ነው“ የሚለው ዘመን ተሸጋሪ አባባል  ታሪካዊ እውነታን የያዘ  ነው። በሕይወት ውስጥ ምንም ነገር እርግጠኛ ባይሆንም ግብር (ታክስ) መክፈል እና ሞት ግን ለማንም ሰው የማይቀሩ  መሆናቸውን ያመላክታል።

ለመሆኑ ግብር ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ ሲነሳ መልሱ   መንግሥት በሕግና ደንብ ላይ ተመስርቶ ከሕዝብና ከድርጅቶች ገንዘብ የሚያገኝበት መሳሪያ ነው የሚል ነው፡፡

ዜጎች በመነገድ፣ ቤትና ንብረት በማከራየት፣ ዕውቀታቸውን በመሸጥ ወይም በሌላ በማንኛውም መንገድ ከሚያገኙት ገቢ ላይ በሕግ በተቀመጠው መሰረት ግብር መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለዚህ ግብር ህብረተሰቡ ወይም ግብር ከፋዮች ለመንግሥት በግዴታ ክፍያ የሚፈጽሙበት መንገድ/ሥርአት ነው፡፡

በአንጻሩ ደግሞ መንግሥት ለሕብረተሰቡ በለውጡ ወይም በምትኩ በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ልዩነት ሳይፈጥር ለሚያቀርበው አገልግሎትና መሰረተ ልማቶች የሚያውለው ገንዘብ ነው፡፡

ግብር ከእያንዳንዱ ግለሰብ የየእለት እንቅስቃሴ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሲሆን ጠቀሜታዎቹም አያሌና ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡

የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል ግብር ለኢኮኖሚ ልማት፣ ለማህበራዊ አገልግሎት መስፋፋት፣ ለባህል እድገት፣ ለሀገር ደህንነት፣ ለፍትሕና ለመልካም አስተዳደር መስፈን፣ ለአከባቢ ጥበቃ፣ ሀገርን ከጠላት ለመከላከል፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም ሠርተውና ውለው ለመግባት፣ ደህንነታቸውንና ሰላማቸውን ለመጠበቅ፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ መንገዶች፣ የኀይል አቅርቦትን ለማስፋፋት ፣ኢኮኖሚን ለማነቃቃት፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት፣ ልማትን ለማፋጠን፣ የሕብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፣ ኢኮኖሚን ለማረጋጋት፣ በዜጎች መካከል ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ እና የመሳሰሉት ሥራዎች ለማከናወን የሚውል ገንዘብ ነው፡፡

የፌዴራል ገቢዎች የሕግ አገልግሎት ቡድን አስተባባሪ አቶ አሰፋ ላመነው ለበኵር ጋዜጣ በሰጡን መረጃ ማንኛውም ገቢ የሚያገኝ ሰው በክልሉ የገቢ ግብር እና የታክስ አሰተዳድር አዋጅ  መሠረት  ግብር የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡

የገቢ ግብር የሚከፈልባችው የገቢ ዓይነቶች  የሀገራችንም ሆነ የክልላችን የግብር ሕግ የሠንጠረዥ ግብር አከፋፈል ዘዴን የሚከተል በመሆኑ ማንኛውም ግብር ከፋይ የሚያገኘው የገቢ ዓይነት/ምንጭ/ በአምስት በተጠቃላሉ የግብር ማሰከፈያ ሰንጠረዦች መሠረት ግብር እየተወሰነ እንዲከፈል የሚደረግ ነው፡፡

እነዚህም  ሠንጠረዥ ‘ሀ’ ከመቀጠር የሚገኝ ገቢ፣ ሠንጠረዥ ‘ለ’ ከቤት ኪራይ የሚገኝ ገቢ፣ ሠንጠረዥ ‘ሐ’ ከንግድ ሥራ የሚገኝ ገቢ፣ ሠንጠረዥ ‘መ’ ሌሎች ገቢዎች፣ ሠንጠረዥ ‘ሠ’ ከገቢ ግብር ነፃ የተደረጉ የገቢ ምንጮች/ዓይነቶች ናቸው፡፡

አቶ አሰፋ አገልግሎት በመስጠት የሚገኝ ገቢን በተመለከተ  ሲገልፁ እንደ አገልግሎቱ አይነት በተቀመጠው የግብር መክፈያ ምጣኔ መሰረት ግብር የሚከፈልበት ስለመሆኑ በፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 1395/2017 የተለያዩ ድንጋጌዎች ላይ ተቀምጧል፡፡ ለምሳሌ ከሥራ አመራር ወይም ከቴክኒክ አገልግሎት ክፍያ ላይ 15 በመቶ  ግብር የሚከፈልበት ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 52 ላይ ተደንግጓል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ዲጅታል አገልግሎትን በማቅረብ ገቢ የሚያገኝ ሰው  5 በመቶ  ግብር እንደሚከፍል በሕጉ አንቀጽ 53 መቀመጡን ያመለክታሉ፡፡ ሌላው ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የመዝናኛ አገልግሎት በመስጠት ገቢ የሚያገኝ ሰው ከገቢው ላይ 15 በመቶ  ግብር መክፈል እንዳለበት  በአንቀጽ 55 ላይ እንደተቀመጠ እንስተው፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት የአገልግሎት አይነቶች በመደበኛነት የሚከናወኑ ከሆነ ግን በንግድ ሥራ ገቢ ግብር ምጣኔዎች መሰረት ግብር ይከፈልባቸዋል፡፡

ከዚህ ውጭ ባሉት አገልግሎቶች ላይ የአገልግሎት ግብር የሚጣለው በፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 ከአንቀጽ 18 ጀምሮ የንግድ ሥራ ገቢ ግብር በሚጣልበት አግባብ ነው፡፡ ድርጅቶች ከሚያገኙት የንግድ ሥራ ገቢ ላይ 30 በመቶ ግብር እንደሚከፍሉ በአዋጁ አንቀጽ 19 መቀመጡን  አቶ አሰፋ አስገንዝበዋል፡፡ ግለሰቦች ደግሞ በአዋጁ አንቀጽ 19 መሰረት ከ10 በመቶ  እስከ 35  ከመቶ ባለው ምጣኔ መሰረት በግብር ምጣኔ ውስጥ ግብር እንደሚከፍሉ በአንቀፅ 14 ሰፍሯል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በመደበኛነት የኪራይ አገልግሎት በመስጠት የሚገኝ ገቢ የንግድ ትርፍ ግብር ለድርጅት ከሆነ 30 በመቶ እንደሚከፈልበት ነው በሕጉ የተቀመጠው፡፡ ሃብትን አልፎ አልፎ በማከራየት የሚገኝ ገቢ ደግሞ 15 በመቶ ግብር እንደሚከፈልበት በሕጉ አንቀጽ 58 ላይ መቀመጡን ነው  አስተባባሪው የገለጹት፡፡  ድርጅቶች ደግሞ የሚያከራዩት ነገር ካለ ከሚያገኙት የቤት ኪራይ ገቢ ላይ 30 ከመቶ ለመንግሥት ግብር ይከፍላሉ፡፡

ሕጉ በዝርዝር ያስቀመጠው ይሄንን ቢሆንም ገቢዎች ሚኒሥቴር በሚሰጠው የታክስ ውሳኔ ቅር የተሰኘ ግብር ከፋይ ግን የግብር ውሳኔ በደረሰው በ21 ቀን ውስጥ ቅሬታውን ለመሥሪያ ቤቱ የታክስ ውሳኔ ቅሬታ አጣሪ ጽሕፈት ቤት ቅሬታውን ማቅረብ እንደሚችል  የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 54 ላይ ቢያስቀምጥ  ይታይለታል፡፡

ቅሬታ አቅራቢው ቅሬታ አጣሪው በሰጠው ውሳኔ ቅር ከተሰኘ ደግሞ በ30 ቀናት ውስጥ ለፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ይግባኝ ማቅረብ እንደሚችል  የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 56 ላይ በዝርዝር ሰፍሯል፡፡

ለፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ይግባኝ ለማቅረብ ግብር ከፋዩ ወለድና ቅጣት ሳይጨምር አከራካሪውን ፍሬ ግብር 50 በመቶ  የከፈለበትን ማስረጃ ማቅረብ አለበት፡፡

ለኮሚሽኑ ይግባኝ የሚቀርበው የቅሬታ አጣሪ ጽሕፈት ቤት ደግሞ  ውሳኔ በደረሰው በ30 ተከታታይ ቀናት ውስጥ ሲሆን ግብር ከፋዩ ይግባኝ ለማቅረብ ጊዜ የሚያንሰው ከሆነም የይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜው ከመጠናቀቁ በፊት ለኮሚሽኑ ጥያቄ ማቅረብ ይችላል፡፡  ኮሚሽኑም እስከ 15 ቀን ድረስ ሊፈቅድለት እንደሚችል በሕጉ አንቀጽ 88 ላይ ተቀምጧል፡፡

የታክስ ይግባኝ ኮሚሽኑ በሰጠው ውሳኔ ላይም ቅሬታ ካለው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብ መብት እንዳለው አንቀጽ 57 ንኡስ አንቀፅ አንድ ላይ ተቀምጧል፡፡

የኮሚሽኑ ውሳኔ በደረሰው በ30 ተከታታይ ቀን ውስጥ ግብር ከፋዩ ይግባኝ ለማቅረብ ጊዜ የሚያንሰው ከሆነም የይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜው ከመጠናቀቁ በፊት የይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜው እንዲራዘምለት ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥያቄ የማቅረብ መብት አለው፡፡

አቶ አሰፋ እንደሚገልፁት ከፍተኛ ፍርድ ቤቱም እስከ 15 ቀን ድረስ ሊፈቅድለት እንደሚችል በሕጉ አንቀጽ 57 ንኡስ አንቀፅ 2 ላይ ሰፍሯል፡፡ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ለማቅረብ ግብር ከፋዩ ወለድና ቅጣትን ሳይጨምር አከራካሪውን ታክስ 75 በመቶ  የከፈለበትን ማስረጃ ማቅረብ አለበት፡፡

ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ የሚቀርበው በሕግ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንደሆነ ነው በሕጉ አንቀጽ 57 ንኡስ አንቀፅ 4 ላይ የተመላክተው፡፡ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ቅር ከተሰኘ ደግሞ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረብ መብቱ የተጠበቀ እንደሆነ በሕጉ አንቀጽ 58 ንኡስ አንቀጥፅ 1 ላይ በዝርዝር ተመላክቷል፡፡

ግብር ከፋዩ ግን የከፍተኛ ፍቤቱ ውሳኔ በደረሰው በ30 ቀን ውስጥ ይግባኝ ማቅረብ ካልቻለ የይግባን ማቅረቢያ ጊዜው እንዲራዘምለት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን በጽሑፍ መጠየቅ እንደሚችል በሕጉ አንቀጽ 58 ንኡስ አንቀፅ 2 ተመላክቷል፡፡ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅር ከተሰኘ ደግሞ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ማቅረብ እንደ ሚችል አስተባባሪው አስገንዝበዋል፡፡

የህግ አንቀጽ

የገቢ ግብር ስሌት

ኮርፖሬት ታክስ፡- የኮርፖሬት ታክስ ድርጅቶች ካገኙት የተጣራ ትርፍ ላይ የሚከፍሉት የታክስ ዓይነት ነው። የዚህ ታክስ መጠኑ ኮርፖሬቱ በሠራው ሥራ ላይ ታክስ ከሚደረጉ የኮርፖሬቱ ኘሮጀክቶች 30 ከመቶ ነው።

የተርንኦቨር ታክስ፡- ይህ ታክስ ዓመታዊ ገቢያቸው ከ500 ሺህ  ብር በታች የሆኑ እና የተጨማሪ ዕሴት ታክስ የማይመለከታቸውን ያጠቃልላል። የሚሰላውም በአጠቃላይ ከተገኘው ገቢ 10 በመቶውን በመውሰድ ነው።

የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት)፡- የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) ዓመታዊ ገቢያቸው ከ500 ሺህ ብር በላይ የሆኑ የግብር ከፋዮች በሚያደርጓቸው በእያንዳንዱ ታክስ ያስከፍላል ተብሎ የተደነገገ የንግድ ልውውጥ ከደንበኞቻቸው 15 ከመቶ ታክስ እየሰበሰቡ ለመንግሥት ገቢ የሚያደርጉት የታክስ ዓይነት ነው።

ኤክሳይዝ ታክስ፡- ይህ ሀገር ውስጥ የተመረቱ ምርቶች ላይ የሚደረግ የታክስ አይነት ነው። ከእነዚህ ሌላ ከውጪ የሚገቡ እቃዎች ላይ፣ የባለቤትነት እና የሼርሆልደሮች ላይ የሚደረግ ታክሶች ዊዝ ሆልዲንግ ታክስ፣ ሮያሊቲ ታክስና ዲቪደንድ ታክስ ናቸው።

የግብር ከፋይ ደረጃዎች

ግብር ከፋዮች እንደሚከፍሉት ግብር መጠን በሦስት ደረጃዎች ይመደባሉ፡-

ደረጃ “ሀ” ግብር ከፋይ፡- ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢው አንድ ሚሊዮን ብር ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ድርጅት ወይም ግለሰብ፤

ደረጃ “ለ” ግብር ከፋይ፡- ድርጅትን ሳይጨምር ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢው ከ500ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር የሆነ፤

ደረጃ “ሐ” ግብር ከፋይ፡- ድርጅትን ሳይጨምር ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢው ከ500 ሺህ  ብር በታች የሆነ ነው፡፡

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here