የአዲስ ዓመት ደጃፍ ላይ ስንደርስ አሮጌውን ዓመት በትዝታ እንመለከታለን፤ ለመጪው ዓመት ደግሞ አዲስ ዕቅድ እና አዲስ ተስፋ እናደርጋለን። ግለሰብ የግል ግቡን ያስቀምጣል፤ ቤተሰብ የወጪና የቁጠባ ዕቅድ ያወጣል፤ ድርጅት የዓመት ዕቅድ ይነድፋል፤ መንግሥትም የልማት ዕቅዶችን ያዘጋጃል።
አዲስ ዓመት ሲመጣ ዘመን ብቻ አይቀየርም፤ ተስፋም አብሮ ይታደሳል። አንዱ የገቢውን መጠን ለማሳደግ ያቅዳል፤ ሌላው ትምህርቱን ለማሻሻል፣ ሥራውን ለማሳደግ ወይም የጀመረውን ለማጠናቀቅ የዓመት ግብ ያስቀምጣል። ቤተሰብ የቤት ዕቅድ ያወጣል፤ ተቋማት የዓመት ዕቅድ ይነድፋሉ፤ ተቋማት በዓመቱ ያቀዷቸውን ለማሳካት ቃል ይገባሉ፣ ሀገርም የልማት ግቦችን ታስቀምጣለች።
ነገር ግን አዲስ ዓመት አዲስ ዕቅድን ብቻ ይዞ መምጣቱ በራሱ ለውጥ አያመጣም። ከዓመት ዓመት የምንናገረው ተመሳሳይ ቃል፣ የምናቅደው ተመሳሳይ ዕቅድና ተመሳሳይ ተስፋ ከተደጋገመ በኋላ የሚቀርበው ዋናው ጥያቄ አንድ ነው፤ “ባለፈው ዓመት ያቀድነው ምን ያህል ተፈጸመ?” የሚለው፡፡
ለመሆኑ አዲስ ዓመትን በአዲስ ዕቅድ ብቻ መቀበል በቂ ነውን? ወይስ ካለፈው ዕቅድ ምን እንደተሳካ እና እንዳልተሳካ በመገምገም መጀመር ይገባል? ከግለሰብ እስከ ሀገር የሚታቀዱ ዕቅዶች ለምን ስኬት ይርቃቸዋል? እንዴትስ ከወረቀት ወጥተው ወደ ውጤት ሊለወጡ ይችላሉ? በእነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያ የዘርፉን ባለሙያዎች በማነጋገር በትንታኔያችን በስፋት እንመለከታቸዋለን።
አቶ ገብሬ ታረቀኝ በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) የስትራቴጂክ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በልማት ኢኮኖሚክስ አግኝተዋል። በሥራ ላይም በዕቅድ ዝግጅት ክትትል እና ግምገማ ለዓመታት አገልግለዋል።
በተመሳሳይ ሙሉቀን አዳነ (ዶ/ር) በአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የቢሮው አማካሪ ናቸው፡፡ ረጅም ዓመታትን በማስተማር ሙያ ያሳለፉ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ እና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በጂኦግራፊ፣ በስነ-ሕዝብና ልማት እንዲሁም በልማትና አካባቢ እንክብካቤ የትምህርት ክፍሎች አስተምረዋል፤ በደረጃቸውም የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አላቸው። በትምህርት ዝግጅታቸው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጂኦግራፊና ሥነ-ሕዝብ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን (ማስተርስ) በቀጣናዊና የከተሞች ልማት ዕቅድ እንዲሁም ሦስተኛ ዲግሪያቸውን (ፒ ኤች ዲ) በልማት ጥናት አግኝተዋል።
ባለሙያዎቹ ከበኩር ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለ ዕቅድ ምንነት፣ ዕቅድን ተግባራዊ እንዳይሆን የሚያደርጉ ምክንያቶችን፣ ከማቀድ ባሻገር ለውጤቱ ምን መደረግ እንዳለበት እና መሰል ጥቄዎችን በማንሳት ሙያዊ ሐሳባቸውን ሰጥተውናል፡፡
“ዕቅድ የሌለው ጉዞ፣ መድረሻው ውድቀት ብቻ ነው” የሚሉት አቶ ገብሬ በየዓመቱ በግለሰቦች፣ ግዙፍ ኮርፖሬሽኖችን ጨምሮ በሌሎች ተቋማት፣ በክልሎች እና በሀገር ደረጃ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዓታትና የፋይናንስ ግብዓቶች ለዕቅድ ዝግጅት እንደሚባክኑ ያነሳሉ። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ከዕቅድነት የተሻገሩ አይደሉም፡፡
የአቶ ገብሬን ሐሳብ የሚጋሩት ዶክተር ሙሉቀን ዕቅድ ማለት አንድ ማሕበረሰብ፣ መንግሥት ወይም ግለሰብ የወደፊቱን በተሻለ መንገድ የሚያይበት ስትራቴጂካዊ መሣሪያ ነው ይላሉ። ይህም ዛሬ ላይ ሆኖ ወደ ፊት ሊደረስባቸው የሚታሰቡ ግቦችን ከአሁኑ በማየት፣ ወደዚያ ለመድረስ የሚያስችል ፍኖተ-ካርታ (road map) የሚቀየስበት እንዲሁም አስፈላጊውን ሀብት በመመደብ ወደ ተግባር የሚለወጥበት የተቀናጀ ሂደት ስለመሆኑ ነው ያስገነዘቡት።
የዓለም አቀፉ የስትራቴጂክ ማኔጅመንት ተቋም (Balanced Scorecard Institute) እና የሃርቫርድ ቢዝነስ ሪቪው (Harvard Business Review) የረጅም ጊዜ የምርምር መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት በዓለም ላይ ከሚታቀዱ ስልታዊ ዕቅዶች ውስጥ እስከ 67 በመቶ የሚሆኑት የትግበራ (Execution) መሬት ሳይረግጡ በወረቀት ላይ ይከሽፋሉ። ይህ አሃዛዊ እውነት የሚያሳየው ትልቁ ክፍተት ዕቅድ የማቀድ ሳይሆን፣ ዕቅድን የመተግበርና በሳይንሳዊ ሥርዓት የመምራት መዋቅራዊ ስንፈት (The Execution Gap) መኖሩን ነው።
ዕቅዶች ለምን ስኬት ይርቃቸዋል?
ለባለሙያዎቹ ዕቅዶች ለምን ስኬት እንደሚርቃቸው ጥያቄ አንስተንላቸዋል። የአሚኮ ስትራቴጂክ ልማት ዳይሬክተሩ እንዳሉት ዕቅድ ሲዘጋጅ ከእውነታው ይልቅ ከፍላጎት መነሳት፣ ግብ እና ተግባር መለያየታቸው አለመታወቁ፣ በዕቅዱ ውስጥ የተቀመጠው ግብ ከሚፈልገው የገንዘብ፣ የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ አቅም ጋር አለመጣጣም፣ የተጠያቂነት ክፍተት እና ክትትል በዓመቱ መጨረሻ ላይ ብቻ መሆን ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው። በርካታ እቅዶች በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት ሳይሳኩ የሚቀሩባቸው ምክንያቶች በዋነኝነት ከዕቅድ ዝግጅት፣ ከሀብት ድልድል እና ከአፈጻጸም ክፍተቶች ጋር የተያያዙ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የክልሉ ፕላን እና ልማት ቢሮ አማካሪው ዶ/ር ሙሉቀን ከላይ የተነሱትን መሠረታዊ ነጥቦች ዕቅድ ከስኬት እንዲርቅ እንደሚያደርጉ እርሳቸውም ይስማማሉ፣ ሁኔታዎችን አለመገምገም ፣ ተጨባጭ ያልሆነ የግብ ቀረጻ፣ የሀብት እጥረትና አለመሟላት እንዲሁም የክትትል፣ የድጋፍና የአፈጻጸም ክፍተቶች ዋና ዋናዎቹ ስለመሆናቸው ነው ያስገነዘቡት።
ለዕቅዶች ስኬት ምን ይደረግ?
ሐሳባቸውን የሰጡን የዘርፉ ባለሙያዎች እንዳስገነዘቡት ዕቅዶች እንዳይሳኩ የሚያደርጉ ምክንያቶችን በአግባቡ መለየት እና መረዳት በጣም ወሳኝ ነው። ምክንያቶቹ ከተለዩ በኋላ ደግሞ ክፍተቶቹን ማረም ይገባል።
“ዕቅድ ስኬታማና ፍጹም ውጤታማ እንዲሆን ሳይንሳዊ ሂደቶችን በመከተል ሦስት መሠረታዊ ሂደቶችን ማሟላት ይገባዋል” ይላሉ አቶ ገብሬ ታረቀኝ፤ እነዚህም እንዴት መታቀድ አለበት? የኪሳራ ቁጥጥር እና የትግበራ ሥርዓት እንዲሁም የክትትል፣ የግምገማ እና የምዘና ሥርዓት ናቸው፡፡
ዕቅድ ከላይ ወደ ታች የሚጫን ትዕዛዝ መሆን እንደሌለበት የሚያነሱት ዳይሬክተሩ ፈጻሚው፣ በየደረጃው ያለው መሪ እና ውጫዊ ባለድርሻ አካላት ከመነሻው የተሳታፊነት ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል። እያንዳንዱ ግብ በምኞት ቃላት ሳይሆን ሊለካ በሚችል የቁጥር ዓላማ (SMART Metrices) መቀመጥና ከተቋሙ የሰው ኃይል ብቃት እና ከሃብት አቅርቦት ጋር መቶ በመቶ መናበብ እንዳለበትም ጠቁመዋል። በተመሳሳይ ዕቅድ በታቀደ ማግስት ወደ መደበኛ የተለመደው የሥራ ጫና የመመለስ ድክመትን ለማስቀረት ስልታዊ ግቦችን ወደ እያንዳንዱ ሠራተኛ ዕለታዊ የውጤት ተኮር ውል (BSC) እና የሥራ ዝርዝር ማውረድ ግድ ይላል።
የአሚኮ ስትራቴጂክ ልማት ዳይሬክተሩ አቶ ገብሬ ታረቀኝ እንዳብራሩት ዕቅዶች በዓመት አንድ ጊዜ ለውዴታ ማሳያ የሚገመገሙ መሆን የለባቸውም። ሊያጋጥሙ የሚችሉ መዋቅራዊ መዛባቶችን ቀድሞ ለመለየት በየሳምንቱ እና በየወሩ የሚለኩ ማዕከላዊ የቴክኖሎጂ የክትትል ቼክ ሊስቶች እና ግልጽ የሆኑ ድርጅታዊ ተጠያቂነትና የማበረታቻ ሥርዓቶች በሥራ ቦታ ላይ በተግባር መዘርጋት አለባቸው። ከላይ የተጠቀሱትን መሠረታዊ ነጥቦች በአግባቡ ወደ መሬት በማውረድ መተግበር ደግሞ ዕቅድን ለስኬት እንደሚያበቁ ነው የጠቆሙት፡፡
በአጠቃላይ ዕቅድ የሕብረተሰብን ኑሮ ለማሻሻል፣ ፍትሐዊነትንና ማሕበራዊ ትስስርን ለማጠናከር እንዲሁም ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም የሚቀየስ ሂደት ነው። በሂደቱ ውስጥ የሚያጋጥሙ ምቹ ዕድሎችንና እንቅፋቶችን አስቀድሞ በመመርመርና ሀገራዊ ቀጣይነትን በማረጋገጥ መሥራት ሁሌም ውጤታማ ያደርጋል።
ችግርን በትክክል የመለየት እና ቅደም ተከተል የማስያዝ (Prioritization) ፋይዳን መገንዘብ እንደሚገባ በመጠቆም ተጨባጭ ውጤት አንደሚያስኝ ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ ሊፈታ የሚችለውን ችግር መለየት ወሳኝ ነው። ከዚያም ችግሮችን በቅደም ተከተል በማስቀመጥ የሚፈቱበትን ስልት ማስቀመጥ ይገባል። ከዚህ ላይ ደግሞ በተለይ መሪዎች (ውሳኔ ሲጪዎች) ሚናቸው ከፍተኛ ነው።
የኢትዮጵያ የዕቅድ ታሪክና ተደጋጋሚው ‘ከዜሮ የመጀመር’ ተግዳሮት
የአማራ ክልል ፕላን ኢትዮጵያእና ልማት ቢሮ አማካሪ ሙሉቀን አዳነ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን ዘመናት የተሻገረ የዕቅድ ልምድ እና ያጋጠሙ ፈተናዎችን አንስተዋል። በአጼ ኃይለ ስላሴ ዘመን የተጀመሩት ዕቅዶች (የመሠረተ ልማት፣ የአግሮ ኢንዱስትሪ፣ የንግድ ግብርና እንዲሁም የትምህርት ዘርፎች) ማሳያ ናቸው። ዕቅዶቹ ቀጣይነት ኖሯቸው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ሀገሪቱ የተበታተነና የዕለት ጉርስ እርሻን አልፋ ወደ ከባድ ኢንዱስትሪዎች ትሸጋገር ነበር።
በደርግ ዘመንም የመንግሥት እርሻዎችን፣ መንደር ምሥረታንና ገበያ ማረጋጋትን ማዕከል ያደረገ የዐሥር ዓመት ዕቅድ ተነድፎ ነበር። በኢሕአዴግ ጊዜም መንግሥት መር የገበያ ኢኮኖሚን መነሻ ያደረጉ የድህነት ቅነሳ ማዕቀፎች እና ሁለት ተከታታይ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ተተግብረዋል።
በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅትም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን መሠረት ያደረገ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ እየተሠራበት ይገኛል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ በታሪካችን ውስጥ ትልቁ ሀገራዊ ፈተና መንግሥት በተቀየረ ቁጥር የቀደመውን በጎ ሥራ አፍርሶ ሁልጊዜ ከዜሮ የመጀመር አባዜ ነው። በመሆኑም ይህን አካሄድ በመተው መልካም ተግባራትን ማስቀጠል እና መሻሻል የሚገባቸውን ደግሞ ማረም ይገባል።
ከዓለም ምን እንማር?
አቶ ገብሬ ታረቀኝ በበኩላቸው የዓለም ሀገራን ተሞክሮ ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚቀራረቡ እና ተሞክሯቸውም ቢወሰድ ውጤታማ ሊያደርጉ ይችላሉ ያሏቸውን የሀገራት ተሞክሮዎች አካፍለውናል፡፡
የሲንጋፖር የ25 ዓመት ድርጅታዊ ጽናት፦
ሲንጋፖር ከድህነት ማጥ ወጥታ የዓለም የፋይናንስ ማማ ላይ ለመውጣት የቻለችው በየአምስት ዓመቱ የምታድሳቸውን የ25 ዓመት ስልታዊ ፍኖተ-ካርታዎችን በጥብቅ በመከተሏ ነው። እነዚህ ዕቅዶች በሕግ የተጠበቁ ድርጅታዊ ሥርዓቶች በመሆናቸው የመሪዎች እና የአመራር መለዋወጥ በዕቅዱ አፈጻጸም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይኖረው በማድረግ የተቋማት ጽናትን ገንብተዋል፡፡
የደቡብ ኮሪያ የ100 በመቶ የዲጂታል አውቶሜሽን ስኬት፦
ኮሪያውያን ዕቅዶቻቸውን በሙሉ በዲጂታል የኢንተርፕራይዝ ሀብት አመራር፣ በግዙፍ ዳታ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ትንተና ይደግፋሉ። በአሁኑ ወቅት የኤ አይ ቴክኖሎጂዎች በሚዲያና በልማት ሂደቶች ላይ እስከ 80 በመቶ የሚደርስ የሥራ ድጋፍ እያበረከቱ በመሆኑ፣ የወጪና የሀብት ብክነትን ወደ ዜሮ ዝቅ አድርገውታል።
የደቡብ ኮሪያ የመቶ በመቶ የዲጂታል አውቶሜሽን ተሞክሮ፦
ኮሪያውያን እቅዶቻቸውን በሙሉ በዲጂታል የኢንተርፕራይዝ ሀብት አመራር (ERP)፣ በቢግ ዳታ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ትንተና ይደግፋሉ። በአሁኑ ወቅት የኤአይ ቴክኖሎጂዎች በሚዲያና በልማት ሂደቶች ላይ እስከ 80 በመቶ የሚደርስ የሥራ አውቶሜሽን ድጋፍ (80% Workflow Lift) እያበረከቱ በመሆኑ የወጪና የሀብት ብክነትን ወደ ዜሮ ዝቅ አድርገውታል።
በመሆኑም ዕቅዶቻችን በውጤት እንዲታጀቡ ግልጽ ዓላማ፣ የሚለካ እና ተደራሽ ግብ፣ እያንዳንዱ ዓላማ እና ግብ ጊዜ የተቆረጠለት፣ ተጠያቂነት የሰፈነበት እና የክትትል እና ግምገማ ሥርዓቱም በወቅቱ መሆን እንዳለበት ባለሙያዎቹ አስገንዝበዋል። ለዚህ ደግሞ መንግሥትና አመራሩ፣ ባለሙያዎች፣ ፈጻሚ ተቋማት፣ ሠራተኞች እና ዜጎች ቁርጠኛ መሆን ይገባቸዋል።
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር የጳጉሜ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


