ነጩ መርዝ ለካንሠር

0
44

በየእለቱ ቢያንስ አንድ በስኳር የጣፈጠ መጠጥ የሚጠጡ ሰዎች አልፎ አልፎ ከሚጐነጩት  በጨጓራ ካንሰር የመያዝ እድላቸው ከእጥፍ በላይ ከፍ ያለ መሆኑን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡

በአሜሪካ የጀነራል ብሪንግሀም የጤና ማእከል ከመቶ ሺህ በላይ በሆኑ የናሙና ጥናት ተሳታፊዎች ለበርካታ ዓመታት ባደረገው ምርምር በቀን አንድ በስኳር የጣፈጠ መጠጥ የሚጠጡ ሰዎች አዘውትረው ከማይጠጡት በሁለት ነጥብ 45 እጥፍ በጨጓራ ካንሰር የመያዝ እድላቸው ከፍ ያለ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

የምርምር ውጤቱ በስኳር የጣፈጠ መጠጥ ከጨጓራ ካንሰር ጋር ያለውን ግንኙነት በግልፅ አመላክቷል፡፡ የ“ጋስትሪክ ካንሰር” ወይም የጨጓራ ነቀርሳ በዓለም በሞት መንስኤነቱ በአምስተኛ ደረጃ ላይ መገኘቱን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

ቀደም ብሎ በስኳር የጣፈጡ መጠጦች ከኮሊስትሮል፣ ከጡት ካንሰር እና ከጉበት ካንሰር ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ነበር የሚታወቀው፡፡ አሁን ላይ ግን የምርምር ማእከሉ ግኝት ጣፋጭ መጠጦችን በየእለቱ መውሰድ የካንሰር ተጋላጭነትን ከእጥፍ በላይ እንደሚጨምር ነው ያመላከተው፡፡

በተቋሙ ከፍተኛ ተመራማሪው (ዶ/ር) አንድሪው ቲቻን  እንደገለጹት በየእለቱ በስኳር የጣፈጠ መጠጥ የሚጠጡት አለፎ አልፎ ከሚጠጡት በጨጓራ ካንሰር የመያዝ እድላቸው በሁለት ነጥብ 45 እጥፍ ከፍ ያለ ነው፡፡ ለዚህም “ፍራክቶስ” የተሰኘው ለመጠጥ ማጣፈጫነት የሚውለው ግብዓት ከጨጓራ ካንሰር ጋር በቀጥታ የሚገናኝ መሆኑን ነው ያሰመሩበት- ተመራማሪው፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here