የሃውቲ ጥቃቶች እና የዓለም ስጋት

0
134

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕዝብ ቁጥር ፈንድ እንዳስታወቀው 36 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ የሚኖርባት የመን ኢኮኖሚዋ በግጭት ምክንያት ከመፈተኑ በፊት በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ በተለይም ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ የመንግሥት ዋና የገቢ ምንጭ እና ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ዘርፍ ነበር፡፡ አብዛኛው የሀገሪቱ ሕዝብ በሚኖርበት የገጠር ክፍል ደግሞ ግብርና በተለይም ጫት፣ ቡና፣ ሰብል ልማት፣ ፍራፍሬ እና የእንስሳት እርባታ ዋና የኑሮ መሠረት ነበሩ፡፡

የመን ረጅም የባሕር ጠረፍ ያላት እንደመሆኗ መጠን የዓሣ ሀብትም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እና ለውጭ ገበያ (ኤክስፖርት) ይውል ነበር፡፡ የኤደን ወደብም (Port of Aden) በዓለም አቀፍ የባሕር ንግድ መስመር ላይ በመገኘቱ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ በተጨማሪም በሳዑዲ አረቢያ እና በሌሎች የባሕረ ሰላጤው ሀገራት የሚኖሩ የመናዊያን ወደ ሀገር የሚልኩት ገንዘብ በርካታ ቤተሰቦችን ይደጉም ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን በሀገሪቱ ባለው የርስ በእርስ ጦርነት እና አለመረጋጋት ምክንያት ይህ ኢኮኖሚ በእጅጉ ተዳክሟል፤ በርካታ ሕዝቧም በሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊ እና የሰው እጅ ጠባቂ ሆኗል፡፡

የመን እንዴት ቀውስ ውስጥ ገባች?

ዓለም አቀፉ የቀውስ አጥኝ ኮሚቴ እንደዘገበው የየመን የርስ በእርስ ግጭት አሁን ላለበት ደረጃ የደረሰው ለዘመናት በተከማቹ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሃይማኖታዊ ውጥረቶች ምክንያት ነው፡፡

እ.አ.አ 2011 የተካሄደው የዓረብ ጸደይ (Arab Spring) አቢዮት ዋና ምክንያት ነበር፡፡ ይህ አቢዮት ለ30 ዓመታት ያህል ሀገሪቱን በፕሬዝዳንትነት የመሩትን አሊ አብደላ ሳሌህ ላይ ሕዝባዊ ተቃውሞ አስነሳ፡፡ ተቃውሞውም ሳሌህን ስልጣን እንዲለቁ በማድረግ በምትካቸው አብድ ረቦ መንሱር ሀዲ እንዲተኩ ምክንያት ሆነ፡፡

ሆኖም አዲሱ የፕሬዝዳንት ሀዲ አስተዳደር የኢኮኖሚ ውድቀቱን፣ ሙስናን፣ የምግብ እጥረትን እና የደኅንነት ስጋቶችን ማስወገድ አልቻለም፡፡ ይህም ሕዝባዊ ቅሬታውን የበለጠ አባባሰው፡፡ ከሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የተነሱት እና የሺአ እስልምና እምነት ተከታይ የሆኑት የሃውቲ ታጣቂዎች የመንግሥትን ድክመት በመጠቀም እና የቀድሞውን ፕሬዝዳንት አሊ አብደላ ሳሌህን ታማኝ ኃይሎችን በመቀላቀል እ.አ.አ በ2014 ዋና ከተማዋን ሰንዓን ተቆጣጠሩ፡፡

ሃውቲዎች ሰንዓን ከተቆጣጠሩ በኋላ ፕሬዝዳንት ሀዲ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተሰደዱ፡፡ ይህን ተከትሎም ጉዳዩን ወትሮውንም ሲከታተሉ የነበሩት እና ለቀውሱ መባባስ ምክንያት የነበሩት የቀጣናው ኃይሎች ጣልቃ በመግባት የየመንን ቀውስ ከድጡ ወደ ማጡ አደረጉት፡፡

በኢራን የሚደገፉት ሃውቲዎች መጠናከር እና የኢራን ተፅዕኖ ማደግ ያሰጋት ሳዑዲ ዓረቢያ ሌሎች የዓረብ ሀገራትን አስተባብራ የሀዲን መንግሥት ወደ ስልጣን ለመመለስ ወታደራዊ ዘመቻ ጀመረች፡፡ ይህ በሀገር ውስጥ ባሉ ኃይሎች መካከል የተጀመረ ግጭት የመንን የቀጣናው ኃይሎች (የሳዑዲ ዓረቢያ እና የኢራን) የውክልና ጦርነት ማሳለጫ አደረጋት፡፡ ይህም ሀገሪቱን ወደ ተወሳሰበና የከፋ ሰብዓዊ ውድቀት ውስጥ ከተታት፡፡

የሃውቲዎች አመሠራረት፣ ቀጣናዊ ተፅዕኖ እና የቀይ ባሕር ስጋት

በየመን ሰሜናዊ ክፍል እ.አ.አ በ1990ዎቹ መጀመሪያ በሃይማኖታዊ ንቅናቄ የተጀመረው በይፋ አንሳር አላህ ተብሎ የሚጠራው የሃውቲ ታጣቂ ቡድን ዛሬ ላይ የየመንን ዋና ከተማ ሰንዓን ጨምሮ ሰፊ ግዛቶችን በመቆጣጠር ቀጣናውን የሚያናውጥ ትልቅ ጂኦ-ፖለቲካዊ ኃይል ሆኖ ወጥቷል፡፡ በመጀመሪያ በዘይዲ-ሺአ ሃይማኖታዊ መሪ ሁሴን ባደር አድ-ዲን አል-ሃውቲ የተመሠረተው ይህ ቡድን ዓላማው በየመን ይስፋፋ የነበረውን የሳዑዲ ዓረቢያን ዋሃቢያ መመከት እና የሺአ ተከታዮችን ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ማንነት ማስጠበቅ ነበር፡፡

ሆኖም እ.አ.አ በ2004 ከየመን መንግሥት ጋር የትጥቅ ግጭት በመጀመሩ ንቅናቄው፣ የመሪያቸውን መገደል ተከተሎ በአብዱል-ማሊክ አል-ሃውቲ መሪነት ወደ ተደራጀ የአማፅያን ኃይልነት ተቀየረ፡፡

የቡድኑ ፈጣን ዕድገት እና ወታደራዊ አቅም ማደግ ከጀርባው ካለው ቀጣናዊ ድጋፍ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተንታኞች ይስማማሉ፡፡ እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የባለሙያዎች ሪፖርት ኢራን የሃውቲዎች ዋና ወታደራዊ፣ የገንዘብ እና የተራቀቁ የድሮንና ሚሳኤል ቴክኖሎጂዎች ምንጭ ናት፤ የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ደግሞ ስልጠና እና የምክር አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም ቡድኑ በቁጥጥሩ ስር ባሉ ግዛቶችና በሁደይዳ ወደብ ላይ በሚጥለው ታክስና ሕገ-ወጥ ንግድ የገቢ አቅሙን ያጠናክራል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሃውቲዎች በየመን የፖለቲካ ምህዳር ላይ ያላቸውን የበላይነት ከማረጋገጣቸውም በላይ ትኩረታቸውን ወደ ዓለም አቀፍ የባሕር ንግድ መስመር መልሰዋል፡፡ ከእስራኤል-ሃማስ ጦርነት በኋላ በቀይ ባሕር እና በባብ አል-መንደብ ማለፊያ ላይ ባሉ የንግድ መርከቦች ላይ ተደጋጋሚ የድሮንና የሚሳኤል ጥቃቶችን መሰንዘራቸው የዓለም አቀፍ ንግድ ፍሰትን አስተጓጉሏል፡፡

ስጋቱን ለመቀነስ አሜሪካ እና እንግሊዝ በሃውቲዎች የጦር ካምፖች ላይ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃት ሰንዝረዋል፤ በአሜሪካ የሽብርተኞች መዝገብ ውስጥ እንዲካተትም ተደርጓል፡፡

ቢሆንም ግን የሳዑዲ ዓረቢያ እና የኢራን የውክልና ጦርነት ማረፊያ የሆነችው የመን እና የሃውቲዎች እንቅስቃሴ አሁንም ድረስ ለመካከለኛው ምሥራቅና ለቀይ ባሕር ቀጣና ዋና የደኅንነት ስጋት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡

የሃውቲ ታጣቂ ቡድን እና ተጽዕኖዎቹ

የየሃውቲ አማጽያን በተለይም በቅርብ ዓመታት በዓለም አቀፍ የባሕር ንግድ ላይ፣ በክልላዊ ኢኮኖሚ፣ በወታደራዊ ሀብትና በሰብዓዊ ሕይወት ላይ ያደረሳቸው ጉዳቶች በርካታ ናቸው፡፡ ሃውቲዎች ባሏቸው የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችና ድሮኖች ሳዑዲ ዓረቢያን እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬትስን የነዳጅ ማጣሪያዎችንና አየር ማረፊያዎችን ማጥቃታቸው የደኅንነት ስጋቱን አጉልቶታል፡፡

እስካሁን ድረስ ከ170 በላይ የንግድና የጦር መርከቦች ላይ በድሮንና በሚሳኤል ጥቃት ፈጽመዋል፤ በዚህም ቢያንስ አራት መርከቦችን ሙሉ በሙሉ ባሕር ውስጥ አስጥመዋል፡፡ በተጨማሪም እንደ ጋላክሲ ሊደር ያሉ ግዙፍ የመኪና ማጓጓዣ መርከቦችን እና ሠራተኞቻቸውን በኃይል ጠልፈው በቁጥጥራቸው ስር አውለው ነበር፡፡

በጥቃቶቹ ሳቢያ ቢያንስ ዘጠኝ መርከበኞች ሕይወታቸው አልፏል፤ በርካቶችም ቆስለዋል፡፡

የባብል-አል-መንደብ እና የቀይ ባሕር መስመር በመዘጋቱ ወይም ስጋት ላይ በመውደቁ በርካታ ግዙፍ የመርከብ ኩባንያዎች መንገዳቸውን በደቡብ አፍሪካ በኩል አድርገዋል፡፡ ይህ መንገድም ረዥም በመሆኑ የወጪ እና የመድን ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል፡፡ የጉዞ ጊዜውም ከ10 እስከ 14 ቀናት በመራዘሙ የነዳጅ፣ የመርከብ ኪራይ እና የባሕር ላይ የዋስትና ወጪዎች በከፍተኛ መጠን እንዲጨምሩ በማድረግ በዓለም አቀፍ የሸቀጦች እና የነዳጅ ዋጋ እንዲንር ምክንያት ሆኗል፡፡

ሃውቲዎች በጎረቤት ሀገራት እና በክልላዊ መሠረተ ልማቶች ላይ ያደረሱት ጉዳትም ቀላል አይደለም፡፡ ድንበር ተሻጋሪ የባሊስቲክ ሚሳኤሎች እና ድሮኖችን በመተኮስ በሳዑዲ ዓረቢያ የነዳጅ መሠረተ ልማቶችን፣ ወታደራዊ ካምፖችን እና ሲቪል አካባቢዎች ላይ ጉዳትና የመሠረተ ልማት ውድመት አድርሰዋል፡፡

በቅርቡ በቀይ ባሕር ዳርቻ በተለይም በሞካ ወደብ አካባቢ ባካሄዱት አዲስ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ምክንያት ከአንድ መቶ ሺህ በላይ የመናዊያን ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የቀይ ባሕር ወደቦች ባልተረጋጉበት ሁኔታ የእርዳታ ዕቃዎችና አስፈላጊ ሸቀጦች ወደ የመን የሚገቡበት መስመር በመስተጓጎሉ የየመን ሕዝብ ለከፋ ረሃብና የምግብ እጥረት ቀውስ መዳረጉን ልብ ይሏል፡፡

የሃውቲ ታጣቂ ቡድን በቀይ ባሕር እና በባብል-አል-መንደብ በግንባር ቀደምትነት የሚያካሂዳቸው የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶች በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚ እና ጂኦፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ላይ ያደረሰው ተጽዕኖ

ኢትዮጵያ አብዛኛውን የባሕር ንግዷን በጅቡቲ ወደብ በኩል በባብል-አል-መንደብ የሚያልፍ ነው፤ በዚህ ቀጣና ያለው ጥቃት ታዲያ የመርከቦች የመድን እና የትራንስፖርት ታሪፍ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ከውጭ የሚገቡ አስፈላጊ ሸቀጦች፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ የነዳጅ እና የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎች የማጓጓዣ ወጪ በመጨመሩ በሀገር ውስጥ ገበያ ላይ የዋጋ ንረትን አስከትሏል፡፡ ምክንያቱም በርካታ የንግድ መርከቦች አደጋ ይደርስብናል በሚል ስጋት ውስጥ በመግባታቸው ለማለፍ በደቡብ አፍሪካ በኩል (Cape of Good Hope) ለመዞር በመገደዳቸው ዕቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡበት ጊዜ በመራዘሙ ነው፡፡

በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ላይ ያደረሰው ተጽዕኖም ከባድ ነው፡፡ ለአብነትም የጅቡቲ ወደብ የቀይ ባሕር ቀውስ ከተከሰተ ወዲህ የመርከቦች እንቅስቃሴ በመቀነሱ ከፍተኛ የወደብ አገልግሎት ገቢ አጥታለች፡፡ በቀይ ባሕር ዳርቻ የሚገኙት ኤርትራና ሱዳንም የባሕር ላይ ደኅንነታቸው በመታወኩ የቀጣናዊ አለመረጋጋት ተጋላጭነታቸው ጨምሯል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ እና የሌሎች ሀገራት የባሕር ኃይል ጥበቃ በቀይ ባሕር አካባቢ በመጨመሩ አካባቢው የጂኦፖለቲካዊ ኃይሎች መፎካከሪያ እንዲሆን በር ከፍቷል፡፡ የሃውቲ እንቅስቃሴ በቀይ ባሕር መስመር ላይ የደቀነው ስጋት ቀጣናው ተጨማሪ የኢኮኖሚ እና የደኅንነት ጫና እንዲሸከም ማድረጉንም ነው ቢቢሲ በዘገባው ያመላከተው፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here